በተቀዛቀዘ የደጋፊዎች ድባብ በተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የስምንተኛ ሳምንት መርሀ ግብር መስኡድ መሀመድ የቀድሞው ክለቡን ለመጀመሪያ ጊዜ ገጠሟል ::
ሰበታዎች አጥቅተው በመጫወት የመጀመሪያውን አስር ደቂቃዎች ወደ ጅማ የግብ ክልል ሲደርሱ የተስተዋሉት ሰበታዎች በግራ መስመር ወንዲፍራው ጌታሁን ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ በጅማ ተከላካዮች ተጠልፎ ፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ችለዋል ::
የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ፍፁም ገብረ ማርያም ሲያስቆጥር ባለፉት አራት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ያስቆጠራቸውን የጎል መጠን ወደ አራት ከፍ ማድረግ ችሏል ::
- ማሰታውቂያ -
ከግቡ መቆጠር በኋላ መሀል ሜዳውን በቁጥር በመብለጥ ኳስን ይዘው መጫወት የፈለጉት ሰበታዎች አልፎ አልፎ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ከግራ መስመር ተሻምቶ ባኑ ዲያዋራ የሞከራት ኳስ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች ::
ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጅማ አባ ጅፋሮች የጎል እድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም የተሳካ ሙከራን ማድረግ ተስኗቸው ተስተውሏል ::
በተለይም በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ጀሚል ያቆብ ለመሀመድ ያኩቡ አሻግሮሎት ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ በጅማዎች በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነበር ::
በሰበታ በኩል ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሲፈልጉ በአንድ አጋጣሚ ባኑ ዲያዋራ ከቅጣት ምት አክርሮ መቶ በጎሉ አግዳሚ ልትወጣበት ችላለች :: በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በቀኝ መስመር ላይ ይገኝ የነበረው ሳሙኤል ታዬ በጨዋታው ሂደት ላይ ሲባክን ታይቷል ::
የመጀመሪያው አጋማሽም ብዙም ሙከራዎች ሳይታዩበት ሊጠናቀቅ ችሏል ::
በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የገቡት ሰበታዎች ጨዋታው በተጀመረ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ባኑ ዲያዋራ ከመስመር ይዞ በመግባት ለመስኡድ አሻግሮለት መስኡድ መሀመድ ለሰበታ ሁለተኛውን ጎል ሊያስቆጥር ችሏል ::
ከጎሉ መቆጠር በኋላ የቀድሞው ክለቡ ላይ ግብ ያስቆጠረው መስኡድ ደስታውን ሳይገልፅ ተስተውሏል ::
ጅማ አባ ጅፋሮች ጎል ካስተናገዱ በኋላ ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመሄድ ቢችሉም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል ::
በተለይም ቅጣት ምት አግኝተው መሀመድ ያኩቡ አክርሮ መቶት የግቡ አግዳሚ የመለሰችበት ሙከራ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች ::
ከደቂቃዎች በኋላ ጅማ አባ ጅፋር ተደጋጋሚ ሙከራዎቻቸው ፍሬ ሊያፈራላቸው ችሏል ::
በቀኝ መስመር በኩል አመረላ ደልታታ ያሻማውን ኳስ መሀመድ ያኩቡ ከተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ ጅማዎችን ሊያንሰራሩ የሚችሉበትን ጎል አስቆጥሯል ::
ከጎሉ መቆጠር በኋላ ሰበታዎች ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ መሪነታቸውን ያጠናከሩበትን ጎል በአሊ ባድራ አስቆጥረዋል ::
ጨዋታው በሰበታ የበላይነት ሲጠናቀቅ በደረጃ ሰንጠረዡ ሌሎች ቡድኖች እስኪጫወቱ ድረስ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል ::