በይስሀቅ በላይ
* ጠዋት ጠዋት ገበያ ከሰዓት ጉሊት አስነስተህ
እያጫወትክ [ፕሪምየር ሊግ] ብሎ መጥራት ያሳፍራል”
* “ፕሪሚየር ሊጉ ለእኔ የሀገር እግር ኳስን ከመጉዳቱ ውጪ
ባለመጥቀሙ ፎርማቱ መቀየሩን ነው የምደግፈው”
* “አሰልጣኙ ሲያሰለጥን ስንት ፐርሰንቱ ነው ወደ ጭንቅላታቸው
የሚገባው የሚለውን እግዚአብሔር ይወቀው”
አቶ አብነት ገ/መስቀል (የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ)
ሸራተን አዲስ የሚገኘው ቢዝነስ ሴንተር ከቀጠሮአችን 15 ደቂቃ ቀደም ብዬ
ተገኝቼያለሁ፤ የመቅረፀ ድምፄን ዝግጁነት እየፈተሽኩና ከእንግዳዬ ጋር በሚኖረኝ ቆይታ
በማነሳቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ብቻዬን እያወራሁ ሳለ ድንገት የሰማሁት የጥሪ ድምፅ
ከሰጠምኩበት የሃሳብ ባህር አነቃኝ፡፡
ወዲያውኑ የሞባይል ስልኬን ሰዓት ስመለከት የዛሬው እንግዳዬ አቶ አብነት ገ/መስቀል
ለእኔና ለጋዜጣችን አንባቢዎች ክብር በመስጠት ከቀጠሮ ሰዓታችን ቀድመው
መገኘታቸው ግርምትን አጫረብኝ፤ ወዲያውኑ “ለካስ ሰውዬው ለጊዜና ለቀጠሮ
የሚሰጡት ዋጋ አንደኛ የስኬታቸው ምክንያት ነው” ስል ወደ ውስጤ አወራሁ፡፡
በአንገትና በቃላት በታጀበ ግብዣ ቢዝነስ ሴንተር ወደሚገኘው ቢሮአቸው እንድገባ
የጋበዙኝ የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ ምቹና የተደላደለውን ወንበር
ስቤ ገና ጎኔን ሳላሳርፍ “ምን ይምጣልህ? ሻይ ቡና ወይስ ሌላ?” በሚሉ የአክብሮት
ግብዣዎች ቀድመው ተቀበሉኝ፡፡ ሆቴሉ ደረጃውን የጠበቀው ሸራተን አዲስ ሆቴል በመሆኑ
ግብዣቸውን ለመግፋት አቅም ስላልነበረኝ እሳቸው ከደረደሩልኝ ግብዣ ርቄ በመውጣት
በሎሚ የፈላ ሻይን አዘዝኩ፡፡
በስብርባሪ ሰከንዶች የጥሪ ናዳ የሚያወርደው ደረጃውን የጠበቀው የእጅ ስልካቸው ፋታ
እንዳገኘ ለሰጡኝ ክብርና ለጊዜያቸው በድጋሚ በማመስገን በመካከላችን የነበረውን
ፀጥታ የሰበረ ቃል ሰነዘርኩ፡፡ እሳቸውም አመዝግነውኝ “በርካታ ስብሰባዎች ስላሉኝ
ከይቅርታ ጋር ብዙ ጊዜ አልሰጥህም” የሚሉ ጨዋነት የተሞላበት ግን ማስጠንቀቂያ
በመሰንዘራቸው ሻይ በሎሚዬን እየተጎነጨሁ በመሀል ጥያቄዎቼን እያዥጎደጎድኩ
ከቅ/ጊዮርጊስ የቦርድ ሰብሳቢ ጋር በነበረኝ ዋጋ ያላቸው የ48 ደቂቃ ቆይታዬ በክለቡ
ውጤት ዙሪያ፣ የፕሪሚየር ሊጉ ፎርማት መቀየርን በተመለከተ፣ ስለ አሳሳቢው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግርና ስለ ሸራተኑ የውይይት መድረክ ዙሪያ ተናግሬ ያናገርኳቸውን
ከዚህ በታች ባለው መልኩ አጠናክሬ አቅርቢያዋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ አመት ባልተለመደ ሁኔታ ተደጋጋሚ ሽንፈት
እያስተናገደ ማሸነፍ እየተሳነው ይገኛል፤ ከዚህ በመነሣት የቅዱስ ጊዮርጊስ የውጤታማነት
ባቡር ነዳጅ ጨረሰ፣ ዳገት ላይ ቆመ ብሎ መናገር ይቻላል…?
- ማሰታውቂያ -
አቶ አብነት፡- …ነዳጅም አልጨረስም፤ ዳገት ላይም አልቆመም፤ ሊቆምም
አይችልም፡፡ በስፖርት አለም እንደምታየው የውጤት ከፍታና ዝቅታ ያለ ነው፤ ያ ነው
ቅ/ጊዮርጊስን የገጠመው፡፡ ባለፉት አንድና ሁለት አመታት የክለባችን ፍላጎትና ህልም
ይሄ ባለመሆኑ ክለባችን በውጤታነት እንዲቀጥል፤ ደጋፊዎቻችንን የሚያረካ ቡድን
እንዲኖረን ቦርዱ የሚጠበቅበትን በማድረግ እንደተለመደው አሉ የተባሉ ጥሩ ጥሩ
ተጫዋቾችን ሰብስበን ነበር፡፡ ብዙ ይሠራሉ ብለን የጠበቅናቸው በተለይ ትላልቆቹ በጉዳት
ምክንያት እንደፍላጎታችን ሊያገለግሉን አልቻለም፡፡ ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌላው የጊዜው
ሁኔታ የእግር ኳሱ ያልተለመደ ባህሪ በተጫዋቾቻችን ላይ ትልቅ የስነ ልቦና ጫና
በማሳደሩ በውጤታችን ላይ መቀዛቀዝ የበኩሉን አድርጓል፡፡ አሁን በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን
ለሁሉም ክለቦች እንኳን ውጤት ደርሶ መመለስ በራሱ ሥጋት እየሆነ ነው፡፡ ከራሳችን
ድክመት በተጨማሪ እነዚህ ነገሮች ተደምረው ለጊዜው በውጤት ከፍታ እንዳንበር
አድርገውናል፡፡
ሀትሪክ፡- …ግን እኮ እርስዎ ከዘረዘሩት ውጪ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግርማ ሞገስ፣ አስፈሪነቱ
አሁን አብሮ የለም፤ በማይጠበቁ ቡድኖች ሁሉ ሣይቀር የሚሸነፍ ቡድን ሆኗል የሚሉ አሉ፡፡
በእርስዎ እይታ የክለቡ ግርማ ሞገስና አስፈሪነት አብሮት አለ…?
አቶ አብነት፡- …ሳንደባበቅ የምንነጋገር ከሆነ እውነት ነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግርማ
ሞገስና አስፈሪነት አሁን ከቡድኑ ጋር የለም፤ በግልፅ ቋንቋ የቡድናችን አቋም ወርዷል፡፡
ያሉት ችግሮች እንዳሉ ሆነው እያየን ያለነው ነገር በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ያልተለመደ ነገር
ነው፤ እንደውም እንደዚህ አይነት ነገር ከብዙ አመታት በኋላ የመጣ ነው፡፡ ያም ቢሆን
ግን እኛ ችግራችንን፣ ድክመታችንን የምንፈትሽበት፣ ከዚህ ወጥተን ቶሎ
ወደምንታወቅበት አሸናፊነት የምንመለስበት ባህል አለን፡፡ አሁን ችግራችንን
መርምረነዋል፣ አውቀነዋል፡፡ ከአሰልጣኝ፣ ከተጨዋቾች ከሁሉም በጠቅላላ እንደ
ጊዮርጊስ ቤት ማለት ነው ራሳችንን የምንፈትሽበት የምንቀይርበትን አካሄድ በጥናት
ጨርሰን ወደተግባር ለመግባት የተጀመረውን የውድድር አመት (ሲዝን) መነካካት አሁን
ያለው መረበሽ ነው ብለን ብዙ አልሄድንበትም፤ያም ቢሆን ወደ አስፈሪነታችን
መመለሳችን ግን የማይቀር ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …አሁን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪው መቐለ 70 እንደርታ በ11 ነጥብ አንሶ በ4ተኛ
ደረጃ ላይ ይገኛል፤(የትናንቱን የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ሳይጨምር) ይሄ ሁሉ የነጥብ
ልዩነት እያለ፣ 4ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ አቶ አብነት ስለ ሊጉ ሻምፒዮንነት …ያልማሉ…?
አቶ አብነት፡- …ለምን አላልምም…?…በጊዮርጊስ ቤት ታሪክና ባህል
መጨረሻም ብንሆን ስለለመድነው ሻምፒዮናነታችን ማለማችንን አናቋርጥም፤ ተስፋ
መቁረጥ ውደድሩ ሳያልቅ መሸነፍን አናውቅበትም፡፡ ለዚህም ነው መጨረሻ ሆነን
“ዘንድሮስ አለቀላቸው፤ ሻምፒዮን አይሆኑም” ስንባል ከ16ኛ ደረጃ ተነስተን ሻምፒዮን
የሆንባቸውን ጊዜ መለስ ብሎ ማስታወስ ለአባባሌ ጥሩ ማሳያ ነው፤ስለዚህ ዛሬም ነገም
ስለ ዋንጫ አስባለሁ፣ ማለሜንም አላቋረጥም፡፡ ደግሞም በካልኩሌሽን፣ በወረቀት
ደረጃ ስታየው ዕድላችን ተሟጦ እንዳላላቀ ይነግርሃል፡፡ መሪው ቡድን ከሜዳው ብዙ
ወጥቶ ይጫወታል፤በእጃችን ያለውን ዕድል ከተጠቀምንበት የዋንጫው ነገር የተዘጋ ፋይል
እንዳልሆነ ትረዳለህ፡፡
ሀትሪክ፡- …ቅዱስ ጊዮርጊስ ለተከታታይ አመታት ከዋንጫና ከአፍሪካ የውድድር
መድረክ ርቆ የታየበት ጊዜ እንደ አሁኑ የለም የሚሉ አሉ፤ እርስዎስ እንደ ክለቡ የበላይ ምን
ስሜት ይፈጥርብዎታል…?
አቶ አብነት፡- …ከሚመጥንህ ከምትታወ ቅበት መድረክና ድል ስትርቅ የሚሰማህ
ነገር ይኖራል፤ አሁን እኔንም የሚሰማኝ ይሄው ነው፡፡ ነገር ግን ኳስን እስካወከው ድረስ
መቀበል አለብህ፤ ከዚህ ውጭ አጋጣሚው በወፍራሙ የሚነግርህ ነገርም አለ፤ በጣም
ብዙ ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠብቀን እየነገረን ነው፡፡ በእርግጥ ወደ ለመድነው ቦታችን
፣ክብራችን ለመመለስ የሚጠብቀን ሥራ ቀላል ባይሆንም ወደዚያ እንዴት መመለስ
እንዳለብን ስለምናውቅ በአጭር ጊዜ እንመለሳለን ብዬ አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ክለቡ ከውጤት ጋር የተጣለበትን ምክንያት ወዴት እንግፋው? ወደ
ተጨዋቾች? ወደ አሰልጣኞች…?…ወደ ቦርዱ…?…ወይስ…?
አቶ አብነት፡- …ወዴትም አንገፋውም… ፤… በተናጠልም ተጠያቂ
የምናደርገውም የለም፡፡ ችግሩን መግፋት ካለብን የምንገፋው ወደ ራሳችን ብቻ ነው፤
እንደ ቡድን ችግሩ የቡድን ነው ብለን ነው የምንወስደው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከውጤት ጋር
ሲጣላ፣ የውጤት መንገጫገጭ ሲገጥመው ከዚያ የሚወጣበት የራሱ የውጤት አፈታት
ባህል አለው፤ ከዚህ ወጥቶ እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል እናውቅበታለን፤
በአጭሩ ችግሩን ወዴትም አንገፋውም ወደራሳችን ብቻ ነው የምንገፋው፡፡
ሀትሪክ፡– …ታዲያ…አቋማችሁ ይሄ ከሆነ… እርስዎን ጨምር ቦርዱ… በተለያየ ጊዜ ወደ
ተጨዋቾቹ ሄዶ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ለምን አስተላለፈ…?
አቶ አብነት፡- …የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናዮች ተጨዋቾችና አሰልጣኞች መሆናቸው እየታወቀ
ዝም ብለን መቀመጥ ተገቢ ነው ብለን ስለማናምን የቦርድ አባላቱም በተለያየ ጊዜ
እኔም በቅርቡ ከአንዴም ሁለቴ ችግሩ ምንድነው? የሚለውን ለማየት ሄደን
አነጋግረናቸዋል፤ምክንያቱም ይሄን ማድረግ የሚጠበቅና ተገቢ ስለሆነ። እኔ በሄድኩ ጊዜ
እንዳልከው ተጨዋቾቹን ጠንከር አድርጌ ተናግሬያቸዋለሁ፤ተጨዋች የሚጫወተው
በፍላጎት ነው፤ ፍላጎት የሌለው፣ ለማልያው ክብር የሌለው፣ ለውጤታማነቱ የማይወድቅ
የማይነሣ፣ ራሱን አሣልፌ የማይሰጥ ተጨዋች ክለቡ ውስጥ መቆየት እንደሌለበትና
መሄድ እንደሚችል አስረግጬ ተናግሬያለሁ፤ አሁንም የምደግመው ይሄንኑ ነው።
በአስቸኳይ መሄድ ይችላል፤ ምንም የምናስታምምበት ሁኔታ የለም፤ ምክንያቱም
ከክለቡ አይበልጥምና፡፡ አሁን ሀ-17 (ከ17 አመት በታች) እንዲሁም ተስፋ ቡድን
ውስጥም ጥሩ ጥሩ ልጆች ስላሉ ትኩረት የምናደርገው ወደ እነሱ ነው፡፡ አሁን ለአንተ
ልንገርህ ስለማልችል አዝናለሁ እንጂ በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ላይ ነው የምንገኘው
በሚለው ጥቅል መልስ ውሰደው፡፡
ሀትሪክ፡- አንዳንዶች ለውጤቱ መጥፋት የአሰልጣኙን ብቃት ይጠራጠራሉ፤ ሌሎች
ደግሞ በአሰልጣኙና በተጨዋቾቹ መካከል ክፍተት መኖሩ ለውጤቱ መጥፋት አንደኛው
ችግር ነው በማለት ያነሳሉ፤ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ…?
አቶ አብነት፡- …አሰልጣኙ ማነው…?…ምን ሰርቷል…?…አቅሙ
ምንድነው…?ለሚለው… ምን አይነት አሰልጣኝ ለክለቡ እንዳመጣን የቀደመ የስልጠና
ስራውን እንድትፈትሽ እተውልሃለሁ፡፡ ግን ይሄ አሰልጣኝ በሌላ ሀገርና ክለብ ብዙ የሠራ
ፕሪሚየር ሊግ ውስጥም የገቡ ተጨዋቾችን ያሰለጠነ ነው፤ ከዚህ አንፃር አቅሙን
መዝኖ ይችላል አይችልም ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጭ ከተጨዋቾቹ ጋር ክፍተት
አለ ለሚባለው በእርግጥም የኮሚኒኬሽን (ግንኙነት) ችግር ሊኖር ይችላል፤ እንኳን
አሁን ለብ/ቡድንም አለ የተባለ የውጪ አሰልጣኝ ሲመጣ የምስጋውም ይሄንኑ ነው፡፡
አሰልጣኙ ሲያሰለጥን ወይም የሚሰጣቸው ትምህርት ሣይሸራረፍ ወደ ጭንቅላታቸው
ይደርሳል? አይደርስም? የሚለው ስጋቴ ነው፤ ስንት ፐርሰንቱ ነው ወደ ጭንቅላታቸው
የሚገባው? እግዚአብሔር ይወቀው፡፡
ሀትሪክ፡- እስቲ አሁን ከክለቡ ወቅታዊ ውጤት ዙሪያ ከያዝኳቸው ጥያቄዎች ልውጣና
ስለ አክሲዮን ማህበሩ ላንሣ፤ ቅ/ጊዮርጊስን በሁለት እግሩ ያቆመዋል ተብሎ ተስፋ
የተጣለበት የአክሲዮኑ ጉዳይ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው…?
አቶ አብነት፡– …አክሲዮን ማህበሩን የመመስረቱ ሥራ በችግሮች መካከል ውስጥ
ቢሆንም ጥሩ እየሄደ ነው፤ በዚህ ደረጃ ተሰርቶ አለመታወቁ ችግሮች እንዲገጥሙን
ምክንያት ሆኗል፡፡ሕጉ የወጣው ለሌላ ነው፤ እንዳልኩህ ችግሮች አሉ፤ ችግሮቻችን ግን
ከመንግሥትና ከህግ ጋር ነው፡፡ የሚከለክል እንጂ የሚያበረታታ ሕግ አለማግኘታችን ችግር
ሆኖብናል፡፡ ለእያንዳንዱ ትርጉም እየተሰጠው እያንዳንዱን ነገር ቁልፍ ተቆልፎበት
ስለምናገኘው ተቸግረናል፡፡ ያም ቢሆን በዚህ ውስጥ ሆነን ጥሩ ነው፤ ጥሩ እየሄደ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ከሕግ ጋር በተያያዘ ትልቅ ፈተና ከሆኑባችሁ ነገሮች አንዱ የስያሜ ጉዳይ
እንደሆነ ሰምቻለሁ፤በተለይ “የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አክሲዬን ማህበር” ለማለት
እንደተቸገራችሁ የሰማሁት እውነትነት አለው…?…እስቲ እርስዎ ያረጋግጡልኝ…?
አቶ አብነት፡- …እውነት ነው…? የስም ጉዳይ ብዙ ረብሾናል…፤ ለምሣሌ ቅዱስ
ጊዮርጊስ የሚለውን ሥም መጠቀም አይቻልም፤ ጊዮርጊስ የሚለውን ለብቻው
መውሰድ አትችልም፤ ምክንያቱም ስም ነው፤ የሰው ነው ተብለህ ትገደባለህ፡፡ የቅዱስ
ጊዮርጊስ ስፖርት ሼር ካምፓኒ፣ ሌላው ተወውና ምንጊዜም ጊዮርጊስ ልበል ብትል ራሱ
አትችልም፤በዚህ በስያሜ በኩል ብዙ በጣም ብዙ ተፈትነናል፡፡
ሀትሪክ፡- …ታዲያ መጨረሻው… ምን ሊሆን ነው፤… ?
አቶ አብነት፡- …የሚገርምህ ነገር በጣም አድካሚ አሰልቺ ነገር ነው የገጠመን፤ ግን
አሁን መጨረሻ ላይ ስሙን ሸራርፈን እንደምንም ብለን ለስሜት ለጆሮአችን አንድ ቃል
እንኳን ማስታወሻ እንዲሆነን ብለን በዚያ ዙሪያ ስም ሰጥተን ከመንግሥት ጋር ያለውን
ነገር እየጨረስን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በሌላ በኩል ጥሩ እየተንቀሳቀስን ነው፤ ቢሮ
ሁሉ ተከራይተናል፤ ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ እቃዎችን (ፈርኒቸሮችም) እየገቡ ነው፤
ሲስተሞች ተዘርግተው ወደ አክሲዮን ለመግባት እየተንደረደርን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- አክሲዮን ማህበሩ በአጠቃላይ እስከ 244 ሚሊዮን ብርን አጥብቆ ይፈልጋል፤
ከሚሊዮን ብሩ ብዛት አንፃር አይሰካ ይሆን…?…ብለው የሚሰጉ አሉ…እርስዎስ…?
አቶ አብነት፡- …ድሮ ሚሊዮን ብር ሲባል እንደነግጥ እንፈራ ነበር፤አሁን ግን ሚሊዮን
ብሮች አያስፈሩም…፤…እኔ ራሴ በድሮው ቢሆን ይሄን ነገር በፍፁም አልሞክረውም እል
ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ሚሊዮን ብሮችን
ተለማምዷቸዋል፤ሲጠራ እንኳን እንደ ድሮ ለጆሮ አይከብድም፡፡ ሚሊዮኖች ብዙ ቦታ
እንደዋዛ ሲጠሩ ትሰማለህ፤ አንዳንድ ስብስባዎች ላይ ሶስትና አራት መቶ ሚሊዮን ብሮች
በቀላሉ እየተዋጡ ሲሰበሰቡ ታያለህ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ክለቡን ስለሚወድ፣
ባለሀብቶች ታሪኩን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ፣ ትላልቅ ስፖንሰሮቻችን ከገዙ በቀላሉ
የተቀመጠው የሚሊዮን ብሮች ገደብ ላይ እንደርስለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን ይሄንን ስልህ
በመጀመሪያ አመት ስንጀምር የተቀመጠውን ታርጌት ላንመታ እንችላለን፤ አልመታንም
ማለት ግን ስኬታማ አይደለንም ማለት አይደለም፡፡ ይሄን መጀመር በራሱ ትልቅ ስኬት
ነው፤ ከእግዚአብሔር ድጋፍ፣ከስፖርቱ፣ ከክለቡ ደጋፊዎች ጋር ግን በአንድነት ሆነን
የተቀመጠውን ጣሪያ እንመታለን የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡– አንዳንድ ደጋፊዎች በቂ መረጃ ካለመኖርና ከጥርጣሬ በመነሳት ቅ/ጊዮርጊስን
ገንዘብ ላላቸው ባለሀብቶች አሳልፈው ሊሸጡት ነው፤ ክለቡን ባለሀብቶች ከደጋፊው
ሊነጥቁት ነው የሚል ስጋት አላቸውና ለዚህ ስጋታቸው ምላሽዎት ምንድነው…?
አቶ አብነት፡– …አሁንም አስረግጬ የምናገረው የክለቡ ባለቤት ደጋፊውና ደጋፊው
ብቻ ነው፤ ባለፈው በጠቅላላ ጉባኤያችን ላይ እንደተናገርኩት ደጋፊው በዚህ በኩል ሊሠጋ
አይገባም፡፡ ማንም አክሲዮን ይግዛ ማንም ገንዘብ ይዞ ይምጣ የክለቡን ባለቤትነት
ከደጋፊው የሚነጥቅ እንደሌለ ደግሜ ላረጋግጥልህ እወዳለሁ፡፡ ከመነሻውም ይሄን
አክሲዮን ይዤ ስመጣ የደጋፊውን ባለቤትነት እንዲቀጥል አድርጌ ነው የሠራሁት፡፡
ደግሞም ደጋፊው ሥጋት ውስጥ እንዳይወድቅ ወደ አክሲዮን በሚደረገው ሽግግር
መንገጫገጭ እንዳይኖር እኮ ነው ስፖንሰሮችን ባልተለመደ ሁኔታ ለ15 አመታት
ያስፈርምኩት፤ ይሄ ትልቅ ጋራንቲ ነው። ይልቁንስ ደጋፊው ከሥጋት ባህር ውስጥ ራሱን
አውጥቶ ክለባችን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ክለብ እንዲሆን፣ አፍሪካ ውስጥ ትልቁ
ቡድን እንዲሆን መረባረብ ነው ያለበት፡፡ በቀላል ምሣሌ በጭቃና በሲሚንቶ የተሠራ
ቤት አንድ ነው…? አንድ አይደለም፤ በሚለው ምላሽ ደጋፊው ከሥጋት ሊወጣ ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- …እስቲ አሁን ደግሞ የግል አስተያየትዎን ልጠይቅዎ?…አሁን ያለው
የፕሪሚየር ሊጉ ፎርማት እንዲቀየር ይፈልጋሉ…?
አቶ አብነት፡- …በጣም እፈልጋለሁ…፤…ይህ ፍላጎቴ ደግሞ ዛሬ ጠዋት ወይም በቅርብ
ጊዜ የመጣ አይደለም፤ ገና የፕሪሚየር ሊጉ ፎርማት ሲቀየር ከ1990 ዓ.ም ጀምር ይሄ
ነገር ለእኛ ሀገር አያዋጣም አይጠቅመንም ብዬ በግልፅ ተቃውሚያለሁ፤ ዛሬም በዛው
አቋሜ እንደፀናሁ ነኝ፡፡ በወቅቱ የተቃወምኩት ደግሞ ዝም ብዬ ለመቃወም ብቻ
አልነበረም፤ምክንያታዊ ተቃውሞ ነው ሳሰማ የነበረው፡፡
ሀትሪክ፡- …በወቅቱ… ለመቃወም ያበቃ ዎት ምን ነበር….?
አቶ አብነት፡– …እንዴ ምን ማለትህ ነው…!…ሌሎች ፕሪምዬር ሊግ ብለው
ሲያወዳድሩ አይተህ ወይም ስሙ አምሮህ ነው ፕሪሚየር ሊግ ብለህ
የምታወዳድረው?…እንደዚህ አይነት ፎርማት ከመቅረፅህ በፊት የሀገሪቱን ተጨባጭ
ሁኔታ፣ የክለቦችን አቅም ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ ተዟዙሮ መጫወት
ለክለቦች አይደለም በሀገር ኢኮኖሚ ራሱ ጉዳት የሚያመጣ ክለቦችን እዳ ውስጥ ነው
የምትከቱት፤ ሁለተኛ በየክለሉ ያሉ ክለቦች እንዳይወጡ እንዳያድጉ ከዚህ ይልቅ አንድና
ሁለት ክለቦች ብቻ ተፈጥረው እነሱም የሚከስሙበት እነሱን የሚተኩ ክለቦች
የማይፈጠሩበት ሁኔታ እንዲኖር ነው የሚያደርገው። ለምሣሌ በወቅቱ ትግራይ ሁለት
ክለቦች ብቻ ነው የነበረው እኮ፤ ጉናና ትራንስ፤ ከአማራ ጥቁር አባይ ፡፡ እነዚህ ክለቦች
በአንድ ምክንያት ቢወርዱ ክልላችሁን የሚወክሉ ክለቦች አይኖሩም፤ የመውረድ እጣ
ፈንታ ቢደርስባቸው እንኳን በዚያው ከስመው ይቀራሉ፤ ተመልሰው የሚወጡበት
መሰላል አይኖርም ብዬ ዛሬ ሣይሆን ያኔ ገና ፎርማቱ ሲወጠን በድፍረት ተናግሬ ብዙ
ተዳርሰን ነበር፡፡ በወቅቱ እንደውም ይሄን በመናገሬ ምን እንደተባልኩ ታውቃለህ?
ሀትሪክ፡- … ምን ተባሉ…?
አቶ አብነት፡- …ሃሳቤን እንደ ነፃና እንደ አንድ ጠቃሚ ሃሣብ ከማየት ይልቅ “ይሄ
የትምክህተኛ አስተሳሰብ ነው” ተብዬ ብዙ ነገር ውስጥ የገባንበት፤ ብዙ የተባባልንበት
ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ የተናገርኩት ነገር መሬት አልወደቀም ብዙ ጊዜ ሣይፈጅ በተናገርኩ
በሶስተኛው አመት ያልኩት አውነት ሆኖ ክለቦቹ ወረዱ፤ ተያይዘው ሄዱ፤ የአማራውም
ሄደ። ሁለቱም ክልሎች ያለ አንድ ወኪል ያለ ኳስ ለብዙ አመታት ተቀመጡ፤ በጣም
የሚገርምህ ነገር በወቅቱ ይሄ ነገር ይቅር የሚወክላችሁ ክለቦችን ታጣላችሁ ስላቸው
ሲቃወሙኝ የነበሩ አንድ የክልሉን ሰው ከብዙ አመታት በኋላ አግኝቼ ምን እንዳሉኝ
ታውቃለህ…?
ሀትሪክ፡- …ምን አሉ…?
አቶ አብነት፡- …“በመጀመሪያ ደረጃ ይቅርታ አድርግልኝ፤ ያኔ አንተ ይሄ ነገር ይቅር
አይጠቅምም ብለህ ስትናገር በጣም ተቃውሜሃለሁ፤ለዚህ አሁንም ደግሜ ይቅርታ
እጠይቅሃለሁ” ብለውኝ “ግን አቶ አብነት አንድ ነገር ልጠይቅህ…ያኔ ለሁላችንም ያልታየን
ነገር አንተ በወቅቱ ምን ታይቶህ ነው…?…እንደዚያ በድፍረት የተናገርከው…?”
ሲሉኝ… እኔ የታየኝ ታይቶኝ ነው፤ ኳስ ውስጥ ስለኖርኩ፣ ለአለም እግር ኳስ በጣም
ቅርብ ስለነበርኩና በጎሳ፣ በብሔር፣ በአካባቢ የሚደራጁ ቡድኖች መጨረሻቸውን ቀድሜ
በመረዳቴ ነው ስላቸው ተገርመው በድጋሚ ይቅርታ ጠይቀውኝ ሄዱ። በአጭሩ የፕርምዬር
ሊጉን ፎርማት ስቃወም የነበረው ገና ከመጀመሪያው ነው፤ ዛሬም ለሀገር እግር ኳስ
የሚሰጠውም ሆነ እስከ አሁን የሰጠው ጥቅም ስለሌለ ፎርማቱ መቀየር አለበት የሚል
አቋም ነው ያለኝ፤እዚህ ጋር ግን አንድ ነገር ልንገርህ?
ሀትሪክ፡- …ምን…?
አቶ አብነት፡- …በመጀመሪያ ክለቦ ቻችንም፣ የውድድር ሜዳዎችም፣ የተጫዋቾ
ቻችንም አቅም፣ የመልክዓ ምድሩም ሁኔታም ፕሪሚየር ሊግ ለማካሄድ የሚመች
ነው…? አይደለም…፤ ገና ለገና ሌላ ሀገር ፕርምዬር ሊግ ስላለ ስም ተውሰን ነው እኛም
ፕርምዬር ሊግ የምንለው?…እንዴ…!…አንተ ምን ማለትህ ነው…?…ሽንት
ቤት…፣…የረባ አጥር እንኳን በቅጡ የሌለው ሜዳ ይዘን ነው የፕርምዬር ሊግ ውድድር
የምናካሂደው? ቀን ቀን ገበያ ከሰዓት በኋላ ጉሊት አስነስተህ ኳስ እየተጫወትክ ይሄንን
የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ብሎ መጥራት አይከብድም…?…አያሳፍርም? ዳኛና
ተመልካች፤ ተጨዋችና ተመልካች እየተገፋፋ እያወዳደርክ ፕርምዬር ሊግ ብሎ መጥራት
ለእኔ ያሳፍረኛል፡፡ ዳኛ የሚመታበት የሚቀጠቀጥበት፣ ተጨዋች አሰልጣኝ ሄዶ
የሚደበደብበት ሀገር ቢኖር የእኛ ሀገር ፕርምዬር ሊግ ብቻ ነው፤ህግ የሚባል ነገር
በማይከበርበት አንድ ክለብ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ለመወዳደር የሚያስፈልገው እንኳን
ባልተሟላበት ሁኔታ ፕሪሚየር ሊግ ብሎ መጥራትና ማወዳደር በራሱ ለእኔ ድፍረት ነው፡፡
ከእስከዛሬው ጉዞአችን ፕሪሚየር ሊጉ ለእኔ የሀገር እግር ኳስን ከመጉዳቱ ውጪ
ባለመጥቀሙ የፕሪሚየር ሊጉ ፎርማት መቀየሩን ነው የምደግፈው፡፡
ሀትሪክ፡- …የእርስዎ የፕሪሚየር ሊጉ ፎርማት እንዲቀየር የመፈለግ አቋምን ክለቡ
ካዘጋጀው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ጋር በማያያዝ ጊዮርጊስ ይሄን የውይይት መድረክ
ያዘጋጀው የፕሪሚየር ሊጉ ፎርማት እንዲቀየር ለማስተባበር ነው በሚል ጥያቄ የሚያነሱ
አልጠፉም፤አንድ የውይይቱ ተከፋይም ይሄንን በግልፅ በጥያቄ ለእርስዎ አንስቶ
ነበር፤እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ…?
አቶ አብነት፡- …ይሄ አሁን አንተ ያልከውን ነገር በውይይት መድረኩ ላይ አንዱ አንዲህ
የጠበበ ጥያቄ አንስቶ ምላሽ አልሰጥም ብዬ ነበር፡፡ ተሰብሳቢው የመጠየቅ መብቱን
ባከብርም የእኔ አለማና ሃሣብ እንደሱ የጠበበ አይደለም፤ እኔ አስተሳሰቤ አገራዊ ነው፤
እሱ ሃሳቡንም ጉዳዩንም አጥብቦ ነው የመጣው፤ እኔ ደግሞ ወይም የስብሰባው
አላማም የጠበበ ሣይሆን በጣም ሰፊና አገራዊ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፎርማቱ
እንዲቀየር ይፈልጋል፤ በዚህ ፎርማት ይጠቀማል አይጠቀምም ማለት የክለቡን ታሪክ
በጥልቀት ካለማወቅ ወይም ከመርሣት በሚመነጭ ስህተት የሚመጣ ትንሽ አስተሳሰብ
ነው፡፡ ምክንያቱም የቅዱስ ጊዮርጊስ የአሸናፊነት ምስጢር ከፎርማት መለወጥ
አለመለወጥ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበፊቱ ፎርማት አሸናፊ
ሻምፒዮን ነበር፤ አሁን ባለው ፎርማትም አሸናፊነቱን ሻምፒዮናነቱን የነጠቀው የለም፡፡
በደንብ ለማብራራት ጊዮርጊስ በድሮው ፎርማት አንደኛ ነው፤ በዚህኛው ፎርማትም
አንደኞች ነን፤ነገም ሌላ ፎርማት ቢመጣም አንደኝነታችንን የሚነጥቀን የለም፡፡
ጊዮርጊንስ በየፎርማቱ ሻምፒዮን የሚያደርገው ለሻምፒዮናነት መስራቱ፣ ለአሸናፊነት
መፈጠሩ ነው፡፡ በእለቱ ጉዳዩን ከጊዮርጊስ ጋር ለማገናኘት የሞከረው ኳሱን የማያውቅ
መልዕክተኛ እንደሆነ ጥያቄው ይናገራል፡፡ እንደዚህ አይነት ሰዎች ናቸው መልዕክት ይዘው
እየመጡ ስብሰባዎችን እያመሱ የሚሄዱት፡፡ ለትልቁ ምስል፣ ለአገራዊው ጥቅም እንጂ
ለትንሽ ሃሣብ መልስ መስጠት ስለሌለብኝ ነው በወቅቱ አልመልሰም ያልኩት፤
ምክንያቱም የእኔ ሃሣብ አገራዊ ነው፡፡ ጊዮርጊስ ፎርማቱ ተቀየረ አልተቀየረ በተለይ
የሚያገኘው ጥቅም የለም፤የሀገር እግር ኳስ ግን መጎዳቱንም እያየነው ነው፡፡ ጊዮርጊስ
ይኖራል፣ አንደኛ ይሆናል፤ ግን የሀገር እግር ኳስ መጎዳቱ፣ ክለቦችን እንክት አድርጎ
መብላቱ፣ የተጨዋቾችን ጉልበት መጨረሱ፣ ሊያንገበግበን ይገባል። ዛሬ ክለቦች
አሰልጣኝ የሚቀያይሩት፣ ደሞዝ እስከመቀነስ የደረሱት፣ ከውድድር የሚወጡት (ከጥሎ
ማለፍ)፣ ደሞዝ እስከ አራት አምስት ወር አልከፈሉም ተብሎ ዜና የሚሰራባቸው ወደው
አይደለም፤ ውድድሩ ሀብት ስለሚበላ ነው፤ እግር ኳሱም፣ የመንግሥትና የህዝብ ሀብት
አለአግባብ ከመባከን መዳን አለበት፡፡
ሀትሪክ፡- …ግን ከእርስዎ በተቃራኒ የሊጉ ፎርማት እንዳይቀየር የሚፈልጉ ደግሞ አሉ፤
በውይይት መድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሠላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዋ
ክብር ወ/ሮ አልማዝ መኮንንም ፎርማቱን ለመቀየር ጥናት ይደረግ ብለዋል፤ በዚህ ላይ ምን
ይላሉ…?
አቶ አብነት፡– …በመጀመሪያ ደረጀ እኔ ጥናት ይደረግ በሚለው ላይ ችግር የለብኝም
ጥናት ይደረግ ግን ትልቁ ጥያቄ ጥናቱን የሚያጠናው ማነው? የሚለው ነው፤ ጥናቱን
የሚያጠናው ጉሮሮው እንዳይዘጋበት የሚፈልግ ከሆነ የጥናቱ ውጤት ጥሩ ይሆናል ብዬ
አላስብም፡፡ ምክንያቱም የሊጉ ፎርማት መቀየር የብዙዎችን ጉሮሮ ይዘጋል፤ ከእግር ኳሱ
ይልቅ ኪሳቸውን ሲያደልቡ የነበሩ ሞራል የሌላቸው ሰዎችን ይጎዳል፤ ብዙ ተጠቃሚዎች
ስላሉ ጉሮሮአችን ሊዘጋ ነው ብለው ሊታገሉ ይችላሉ፡፡ ግን ትልቁን ምስል ካየን
የመጨረሻው ግባችን እግር ኳሱን መታደግ ከሆነ ፎርማቱ መቀየሩ ግድ ሊሆን ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡– …እግር ኳሱ የጎሳና የዘር አመለካከት ባላቸው ወገኖች መጠቃቱን እንዴት
ታዘቡት…? ሁኔታውስ ምን ስሜት ፈጠረብዎት…?
አቶ አብነት፡– …ሰው በዘሩ፤ በማንነቱ ሲሰደብ ሲጠቃ፣ እኔ ክልል አትምጣ ሲባል
ያውም በዚህ በሰለጠነ አለም አንድ በሆነችበት ዘመን ስታይ በጣም ታፍራለህ፡፡ አለም
በተሻለ ነገር ሊያውቁን ሲገባ በጎሣና በዘር ታጥረን ስማችን በዚህመነሣቱ አንገት
የሚያስደፋ ነው፤ ይሄ ትልቅ ጠባብነት ነው፤ ለእኔ ከካንሰር በሽታም ለይቼ አላየውም፤
በአጭሩ የእግር ኳሱ ጉዳዩ ካንሰር ነው፤ እንዴት የአንድ ኢትዮጵያ ልጆች ሆነን በዘር በጎሣ
ተከፋፍለን እንጠቃቃለን? ይሄ በእግር ኳሱ ብቻ ሣይሆን እንደ ሀገርም ትልቅ ጠንቅ
የሆነብን እርስ በእርስ እያጨረስን ያለ ችግር ነው፡፡ ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖት፣ ከዘር የፀዳ
ነው በሚባለው ሰፖርት ያውም በዚህ በሰለጠነ ዘመን እኛ በኋላ ቀር አመለካከት
ተዘፍቀን ስንሰዳደብ፣ ስንፈነካከት፣ ስንገዳደል፣ አትድረሱብን ስንባባል ማየት ልብ
ይሰብራል፡፡ ሁላችንም ጊዜ ሳንሰጥ ልንዋጋው ይገባል፤ ከዚህ ከጎሳ ከዘር ልዩነት ጋር
በተያያዘ አንድ ጥሩ ትምህርት የሚሆን ነገር ልንገርህ…?
ሀትሪክ፡- … ደስ ይለኛል …?
አቶ አብነት፡– …በጣም የሚገርምህ እኛ በዚህ ሰለጠነ በሚባለው ዘመን ያለነውን
ተወው… በአንድ ወቅት የቅዱስ ጊዮርጊስ መስራቾች የሆኑት አየለ አትናሽና ጆርጅ ዱካስ
ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ በዛን ወቅት ያደረጉት ነገር ዛሬ ለብዙዎቻችን ትምህርት የሚሰጥ
ነው፤ በጣሊያን ወረራ ወቅት ጥቁሮች ከነጮች ከክልሶች ጋር አብረው መጫወት
አይችሉም ተብሎ በመከልከሉና ጥቁሮች በመሆናቸው ብቻ በመገለላቸው የተበሳጩት
አየለ አትናሽና ጆርጅ ዱካስ አንድ ጥቁር በግና አንድ ነጭ በግ ይዘው የከለከሏቸው ጋ
ይሄዳሉ፡፡ ከዚያም የከለከላቸውን ሰው ወደ ጥቁሩ በግ በእጃቸው እየጠቆሙ “ይሄ
ምንድነው?” ብለው ይጠይቁታል እሱም “በግ” ብሎ ይመልስላቸዋል፤ በመቀጠል ወደ
ነጩ በግ እያመለከቱ “ይሄኛውስ?” ይሉታል እሱም “ይሄም በግ ነዋ…!” ብሎ
ይመልስላቸዋል፡፡ እነሱም ወዲያውኑ “እንኳን በሰው በእንሰሳት መካከል ልዩነት የለም፡፡
የበጎቹ ከለር ቢለያይ አንደኛው ጥቁር አንደኛው ነጭ ቢሆኑም ሁለቱም ግን በጎች ናቸው”
ብለው በሃሳብ አሸንፈው ተጫወቱ ይባላል፡፡ አሁን ይሄ የሆነው በ1928 ከዛሬ 80
አመት በፊት ማለት ነው፤ የሚገርምህ ነገር እንደዚህ አይነቱ ነገር ለሀገራችን እግር ኳስ
አዲስ አይደለም በ1958 ዓ.ም ክለቦች በጎሣ በፓርቲ ስም ስር መቋቋማቸው ብዙ
ችግሮች ፈጥሮ እንደነበር ማስታወስ ይችላል፡፡ በ1958 ዓ.ም በተለይ የሀማሴን ቡድን
በጣም ብዙ ችግር ፈጥሮ ነበር፡፡ ሌሎች ክለቦችም የሶዶ ምንጭና፣ እምቧሶይራ፣
ማይላኸም የሚባሉ የቡድን ስሞች ነበሩ፡፡ በወቅቱ እግር ኳሱ በዚህ ደረጃ በተቋቋሙ
ክለቦች ሠላሙ ታውኮ ነበር፡፡ ግን በወቅቱ ቆራጥ አመራር ስለነበር ከአለም አቀፉ ሕግ
የሚፃረር በመሆኑ ስማቸው እንዲቀየር የተደረገበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ አሁንም
ወደዚህ ዘመን የሚመልስ ነገር ነው የምታየው፤ እግር ኳሱ በጎሣና በዘር ቫይረስ
ተጠቅቷል፡፡ ክለቦች በጎሣ በዘር ተከፋፍለው በራሣቸው ሜዳና በደጋፊያቸው ፊት
መጫወት እንኳን የማይችሉበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ተደርሶ እያየን ነው፤የሄ በጣም
የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነው፡፡ ክለቦች በአብዛኛው የተያዙት የሚደግፉት በፓርቲዎች
ሥር በመሆኑ ፖለትካው ሲደፈርስ ወይም ሲናጋ የስፖርቱ መንደርም አብሮ ይናጋል፡፡
የአንደንዶቹማ ስማቸው መዝሙራቸው ሣይቀር እግር ኳስ እግር ኳስ የማይሸት ክለቦች
አሉ፡፡ የ19 እና የ20 አመት ተጨዋችን በቡድንህ ውስጥ ይዘህ ለጨዋታ ወደ አንድ ሜዳ
ስትሄድ የባለሜዳው ደጋፊ “ዛሬማ ደም ደም ሸቶናል” እያለ ሲዘምር ሲሰማ ይሄ
ተጨዋች ጎል ማግባትንና ማሸነፍን አሊያስ እንዳይደበደብና እንዳይታረድ ነፍሱን ለማዳን
ጎሉ አፍንጫ ደርሶ ኳሱን ወደ ሠማይ ነው የሚለቀው ? ቢሞት መረብ ውስጥ ለማሳረፍ
አያስብም፡፡ ይሄ ሁሉ ተፅዕኖ ተጨዋቾች ላይ አለ ደጋፊው ከቤቱ ወጥቶ የፈለገው ቦታና
ስታዲየም ሄዶ ጨዋታ ማየት አልቻለም…፤ በፍርሃትና በሥጋት ተሸብቦ ከሜዳ
እንዲርቅ ነው የተፈረደበት፤ ወላጆች ባልተለመደ ሁኔታ ልጆቻችን ወጥተው በሠላም
ይገባሉ ወይ? በሚል ጥያቄ ውሰጥ ከወደቁ ሰነባብተዋል፡፡ በአጭሩ እግር ኳስ
ሜዳዎቻችን ወደ ጦር ሜዳ የተቀየሩ የስጋት ቀጠናዎች ሆነዋል፡፡ እኔ በግሌ የምፈራውም
የምሰጋውም ይሄ ነገር አንድ ቦታ ላይ ካልቆመ ስታዲየሞቻችን እንደ ሩዋንዳው የዘር
እልቂት የደም ገንቦ እንዳይሆኑ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የአዲስ አበባ ክለቦች እየተመ ናመኑ መምጣታቸውን እንዴት ያዩታል…?
አቶ አብነት፡- አምስት ሚሊዮን ህዝብ ባለበት ከተማ ሁለትና ሶስት ቡድኖች
መኖራቸው ለእግር ኳሱ ሌላው አስፈሪ ነገር ነው፤በፊት በሰባትና በስምንት ክለቦች አዲስ
አበባ እንዳልተወከለች አሁን ወርዶ ወርዶ ሶስት ክለቦች ብቻ ናቸው የቀሩት፤ አንደኛውም
በር ላይ እየጠበቀ ነው፤ ይኑር አይኑር አይታወቅም፤ በዚሁ ከቀጠለ መውረዱ ስለማይቀር
አዲስ አበባ በሁለት ቡድኖች የመወከል ግዴታ ውስጥ ነው የምትወድቀው፡፡ የአዲስ አበባ
ክለቦች መመናመን ከእግር ኳሱ አለማደግ ጋር የሚያያዝ ነው፤ በምን አይነት
የተንሸዋረረ መለኪያ ተመዝኖ እግር ኳሱ አደገ እንደሚባል ለእኔ አይገባኝም፡፡ የአዲስ
አበባን መዘን አየን እንጂ በአጠቃላይ እግር ኳሱ አሳሳቢ ደረጀ ላይ ነው፤ በክልል ያሉትም
በጀት ቀነሰን ሲሉ ነው የምትሰማው፤ ይሄንን ያልተናገሩትም የ4 እና የ5 ወር ደሞዝ
በመክፈላቸው ሣይሆን ባለመክፈላቸው የዜና መሸፈኛ ሲሆኑ ነው የምታየው፡፡
ሀትሪክ፡- …የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ለሁለት ቀናት የቆየ የስፖርታዊ ጨዋነት
ምንጮች የሚል የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል…፤… በዚህ ወቅት ይሄን መድረክ ለማዘጋጀት
የተነሣችሁበት የተለየ ምክንያት አላችሁ…?…የሚለው የውይይታችን የመክፈቻ ጥያቄ
ቢሆንስ…?
አቶ አብነት፡– …በነገራችን ላይ ይሄን የተቀደሰ አላማን ያነገበ የውይይት መድረክ
ለማዘጋጀት ካሰብን ቆይተናል…፤… ሃሳቡ ድንገት ሰሞኑን ብቅ ያለ ሳይሆን ከዓመት በፊት
ጀምሮ በተለያየ መንገድ ስንዘጋጅበት ነው የነበረው፡፡ ይሄን በስፖርታዊ ጨዋነት ምንጮች
ላይ ያጠነጠነ የውይይት መድረክ እንድናዘጋጅ የገፋፋን ደግሞ ከዛሬ ነገ ከመሻሻል ይልቅ
እየተባባሰ መሄዱ፣ የስፖርቱ የውድድር ሜዳዎች የጦር ሜዳ እስኪመስሉ ድረስ ዜጎቻችን
እየተደባደቡ፣ እየደሙ፣ መሳ ሪያዎች እየተተኮሱ ፣ጨዋታዎች እየተቋረጡ መሄዳቸው
የፊፋና የካፍ ህግ ከሚያዘው ውጭ የጎሣና የዘር ልዩነት እግር ኳሱ ውስጥ ሥር ሰዶ
ደጋፊው በነፃነት ወደ ስታዲየም መጥቶ እንዳይደግፍ ተጨዋቾች በነፃ አዕምሮው
ጨዋታቸውን ተጫውተው እንዳይወጡ፣ ዳኞች ጨዋታውን በነፃነት መርተው የማይወ
ጡበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ይሄም በአንድ ቦታ ብቻ ሣይሆን በየቦታው ከብርሃን ፍጥነት
በበለጠ እየተዛመተ በመምጣቱ በጣም ስላሳሰ በንና ሠላማችንን ስለነጠቀን ለችግሩ
መፍትሔ ለመፈለግ ይረዳል ከሚል የተቀደሰ ሃሳብ የውይይት መድረኩን ለማዘጋጀት
በቅተናል፡፡
ሀትሪክ፡– …ሃሳቡ የተቀደሰና የሚደገፍ ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ክለብ ይሄን
ለማዘጋጀት ማነው…?…የሚል ጥያቄ ያላቸው አይጠፉምና መልስዎ ምንድነው…?
አቶ አብነት፡- …“…እናንተ… ማናችሁ…?” የሚል ትንሽ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች
ይኖራሉ ብዬ አላስብም…፤…ምናልባት ቢኖሩ እንኳን… “…እናንተ… እነማን
ናችሁ…?…ይሄን የምታዘጋጁት…?” ብለው ጥያቄ ለሚያነሱ መልሴ እኛማ
ተቆርቋሪዎች፣ አሳቢዎች… ከማንም በላይ… የሚመለከተን…፣… ከማንም በፊት…
ይሄን ማድረግ… የሚጠበቅብን ነን… የሚል ነው… መልሴ፡፡
ሀትሪክ፡– …ከይቅርታ ጋር… መልስዎ ግልፅ አልሆነልኝም …አልገባኝም….?
አቶ አብነት፡- …የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የሀገሪቱን እግር ኳስ ከሚመራው
ፌዴሬሽን ሣይቀር ቀደሞ የተመሠረተ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ክለብ ነው፤ በቅኝ
ገዢዎች፣ በወራሪዎች ሳይቀር የተፈተነ የሀገር ኩራት የሆነ ክለብም ነው፤ ብዙ የእግር
ኳስ መሪዎችን ከሀገር አልፎ ለአህጉራችንና ለዓለም ያበረከተ ታላቅ ክለብ ነው፡፡
ከአህጉራችን ክለቦች ስሙ ከፍ ብሎ የሚጠራ ታላቅ የተሳትፎ ታሪክም ያለው ክለብ
ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሀገር እግር ኳስ በስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ሲታመስ፣ የተጨዋች
የተመልካች፣ የዳኞችና የአሰልጣኝ ደም እየፈሰሰ ዝም ብለን የምናይበት ህሊና የለንም
በማለት እንደ ሁሉም ነገር ፈር ቀዳጅነታችን (Pionner) አንፃር የአንበሳውን ድርሻ
በመውሰድ የድርሻችንን ለመውጣት ፣ያለንን በማካፈልና የውይይት መድረክ በማዘጋጀት
ለለውጡ የሚጠበቅብንን ለመወጣት ሞክረናል፡፡ ስለዚህ እናንተ እነማን ናችሁ? የሚሉ
ካሉ እኛማ ተቆርቋሪዎች፣ አሳቢዎች ነን ነው መልሴ፡፡
ሀትሪክ፡– “የስፖርታዊ ጨዋነት ምንጮች” በሚል የተዘጋጀው የውይይት መድረክ ምን
ያህል የታለመለትን ግብ መቷል ማለት እንችላለን….?
አቶ አብነት፡- …በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙትና ንግግር ያደረጉት የሠላም
ሚኒስቴር ዴኤታዋ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን በጣም ስኬታማ የውይይት መድረክ
እንደነበር መስክረዋል፤ የመድረኩ ተሳታፊዎችም መድረኩ ላይም በግሌም ስለ
ስኬታማነቱ ምስክርነታቸውን ሰጥተውኛል፡፡ እኔም ጋ ያለው ተመሳሳይ ስሜት ነው፤
የውይይት መድረኩ የታለመለትን ግብ በአግባቡ መቷል፡፡ ከ355 በላይ ተሳተፊዎች
አዳራሹን ጢም አድርገውት የጋለ ውይይት አድርገዋል፤ የሃሳብ ፍጥጫ በነፃነት
የተስተዋለበትም ነበር፡፡ ያ ሁሉ ተሳታፊ ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት
ያለመሰልቸት የጋለ ውይይት አድርጓል፤ ያመኑበትን፣ የተሰማቸውን፣ ለችግሩ ይረዳል
ያግዛል ያሉትን በነፃነት ሲያንሸራሽሩ እናንተም ተመልክታችኋል፡፡ ተሳታፊዎች ያለ አንዳች
ገደብ በዚህ መልኩ ሳይሸማቀቁ ሳይታፈኑ መተንፈስ መቻላቸው የውይይት መድረኩ
ትልቅ ስኬታም ነው ለእኔ፡፡ ብዙ ቦታ በተመሳሳይ ተሳትፈናል፣ እናውቀዋለን፤ ጠዋት
የተገኘ ተሳታፊ ከሰዓት የለም ከሰዓት ያለ ጠዋት የማይገኝበትን ሁኔታ ነበር
የምናውቀው፤ ይሄ ግን ፍፁም የተለየ በተሳታፊዎች የተጨናነቀና ሃሳቦች የተነሱበት
የውይይት መድረክ ስለነበር ስኬታማ ነበር ነው የምለው፡፡
ሀትሪክ፡- ይሄን የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት የነበረውን ውጣ ውረድስ እንዴት
ይገልፁታል…?
አቶ አብነት፡-እውነት ለመናገር በጣም አድካሚና ፈታኝ ነበር፡፡ አንግበን የተነሣነውን
አላማ ለማሳካት በግልም እንደአዘጋጅ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስም ብዙ ለፍተናል ደክመናል፡፡
ግን በመጨረሻ ያየነው ድካምና ልፋታችንን የሚያካክስ መድከማችንን መልፋታችን
ተገቢ እንደነበር የሚጠቁም መሆኑ ሁሉን ነገር አስረስቶናል፡፡ ካልደከምክ ምንም አይነት
ጥሩ ውጤት እንደማይገኝም አይተንበታል፡፡ ብዙዎችን ለማሳመን በየቦታው ዞረናል፤
በተለይ በመንግሥት መ/ቤት ዙሪያ ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን በማስረዳቱ በኩል ብዙ
ደክመናል፤ ድካማችንን “የእኛን ስራ እኮ ነው የምትሰሩልን” በማለት ጉልበትየሚሆን
መልስ ነው የሰጡን፡፡ ፌዴሬሽኑ ዋነኛው የጉዳዩ ባለቤት ከመሆኑ አንፃር ፕሬዚዳንቱን አቶ
ኢሳያስ ጅራን እንደምፈልጋቸው ስገልፅላቸው ለአፍታም ሣያመነቱ “ቢሮ ና” ከማለት
ይልቅ “ያለህበት ድረስ ልምጣ” ብለው ከእሣቸው ጋር ከግማሽ ቀን በላይ የፈጀ ውይይት
በማድረግ “የተቀደሰ ሃሣብ ነው፤ ከጎናችሁ ነን ብለውናል፡፡” በአጠቃላይ የሁሉም
ድጋፍና ርብርብ ከጠበቅነው በላይ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡– …መንግሥት ለውይይት መድረኩ ያለውን ድጋፍ በሚኒስቴር ደረጃ ያሉ ከፍተኛ
አመራሮችን በመላክ ተባባሪነቱን አሣይቷል… ይሄን እንዴት ታዘቡት…?
አቶ አብነት፡– የመግሥት ድጋፍና ተባባሪነት የነበረው ገና ከመጀመሪያ ነው፤ “የእኛን
ሥራ እኮ ነው የምትሰሩት” ከማለት ጀምሮ እስከ ተግባራዊ ድጋፍ የመንግሥት ተባባሪነቱና
ምላሹ ከፍተኛ ነበር፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው፣
የሠላም ሚኒስቴር ማኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን የፌዴራል ስፖርት ሚኒስቴር
ዴኤታ አቶ ሀብታሙ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል አቶ ….የውይይቱ
መድረኩ አንግቦት የተነሣውን የተቀደሰ ሃሳብ በመደገፉ በአካል በመገኘት ጭምር
ተባባሪነታቸውን አሣይተዋል፤ በዚህም በግሌም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከልብ ማመስገን
እወዳለሁ፡፡