የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት የዕለተ እሁድ የአ/አ ስታዲየም ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት 2 ጨዋታዎች በዕለተ እሁድ በአ/አ ስታዲየም የሚደረጉ ይሆናል።
8፡00 ሲል መከላከያ ከፋሲል ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። በፕሪሚየር ሊጉ ጅማሬ ላይ ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖት የነበረው እና ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ የመጣው በሻ/ም ምንያምር ፀጋዬ የሚመራው መከላከያ ከሜዳው ውጪ ጠንካራ አቋም እያሳየ በሚገኘው እና እስካሁን በሊጉ ሽንፈት ባላስተናገደው ፋሲል ከተማ ይፈተናል ተብሎ ይጠበቃል። መከላከያ ካለፉት 3 ጨዋታዎች 2ቱን በምንይሉ ግቦች በተመሳሳይ 1-0 ሲያሸንፍ አንዱን ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። ፋሲል ከተማ በበኩሉ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ እስካሁን ካልተሸነፉት 3ቡድኖች አንዱ መሆን ችሏል።
ፋሲል ከተማ ካደረጋቸው 8ጨዋታዎች 5ቱን ከሜዳው ውጪ ያደረገ ሲሆን ዛሬ ወደ አ/አ ተጉዞ የሚያደርገው ጨዋታ 6ኛ ከሜዳው ውጪ የሚያደርገው ጨዋታ ይሆናል፡፡ ፋሲል ከተማ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ወደ ጅማ ተጉዞ ጅማ አባጅፋርን ያሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛው ከሜዳው ውጪ ያስመዘገበው ድል ሆኖ ተመዝግቦለታል። ከደደቢት ጋር አ/አ ስታዲየም እና አዳማ ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር በተመሳሳይ ያለ ግብ 0-0 ድሬ ላይ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 1-1 እንዲሁም አዲግራት ላይ ደግሞ ከወልዋሎ አ.ዩ. ጋር 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።
- ማሰታውቂያ -
መከላከያ በአንፃሩ በሜዳው 4 ጨዋታዎችን የተጫወተ ሲሆን ካደረጋቸው 4 የሜዳው ላይ ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማን 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ያሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛው በሜዳው ያስመዘገበው ድል ነው። በወላይታ ድቻ 1-0 ተሸንፎ ከሀዋሳ ከተማ ጋር 1-1 እንዲሁም ከአዳማ ከተማ ጋር 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።
በአጠቃላይ በፕሪሚየር ሊጉ መከላከያ ካደረጋቸው 9ጨዋታዎች 2ጨዋታዎችን አሸንፎ በ4 አቻ ተለያይቶ 3ቱን ተሸንፎ 10 ነጥቦችን ሰብስቦ 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ፋሲል ከተማ በአንፃሩ 8ጨዋታዎችን አድርጎ 2ጨዋታዎችን አሸንፎ 6ጨዋታዎችን አቻ ወጥቶ ያለምንም ሽንፈት ማግኘት ከሚገባው 24ነጥቦች ግማሹን ብቻ (12ቱን) አሳክቶ ከመሪው ደደቢት በ7ነጥቦች ርቆ 4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ከፋሲል ከተማ በኩል ይስሀቅ መኩሪያን እና አይናለም ሀይሉን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን በመከላከያ በኩል አዲሱ ተስፋዬ ሳሙኤል ታዬ እና ከታች ያደገው አብነት በጉዳት አይኖሩም፡፡ በክለቡ ቅጣት የተላለፈበት ቴዎድሮስ በቀለ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ከቅጣት የሚመለሱ ተጫዋቾች ይሆናሉ፡፡
10 ሰዓት ሲል የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታ በብዙ የኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
ይህን ጨዋታ ተጠባቂ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ኢትዮጵያ ቡና 2ተከታታይ ጨዋታዎችን ከተሸነፈ በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ወላይታ ድቻ በአንፃሩ የረጅም ጊዜ አሰልጣኙን መሳይ ተፈሪን ካሰናበተ በኋላ ድል ማድረጉን ተከትሎ ያንን የድል ጉዞ ለማስቀጠል የሚደረግ ጨዋታ መሆኑ ዋንኛ ተጠቃሽ ምክንያት ነው። በ9ኛው ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና አ/አ ስታዲየም ላይ ከሊጉ መሪ ደደቢት ጋር ተጫውቶ በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ 1-0 ሲሸነፍ ወላይታ ድቻ በአንፃሩ ሶዶ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን አስተናግዶ በጃኮ አረፋት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ እና በአብዱልሰመድ አሊ ግብ 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
ወላይታ ድቻ ካደረጋቸው 9ጨዋታዎች 5ቱን ከሜዳው ውጪ ያደረገ ሲሆን ዛሬ ወደ አ/አ ተጉዞ የሚያደርገው ጨዋታ 6ኛ ከሜዳው ውጪ የሚያደርገው ጨዋታ ይሆናል፡፡ ወላይታ ድቻ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ወደ አ/አ ተጉዞ መከላከያን 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ያሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛው ከሜዳው ውጪ ያስመዘገበው ድል ሆኖ ተመዝግቦለታል። በሀዋሳ ከተማ እና በፋሲል ከተማ በተመሳሳይ 1-0 እንዲሁም በሲዳማ ቡና 3-1 ተሸንፎ ከደደቢት ጋር አ/አ ስታዲየም ላይ ያለ ግብ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።
ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በሜዳው 5 ጨዋታዎችን የተጫወተ ሲሆን ካደረጋቸው 5 የሜዳው ላይ ጨዋታዎች መከላከያን 1-0 ወልድያን እና አርባምንጭ ከተማን በተመሳሳይ 2-0 በሆነ ውጤት ያሸነፈ ሲሆን ከሲዳማ ቡና ጋር 1-1 እንዲሁም ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።
በአጠቃላይ በፕሪሚየር ሊጉ ኢትዮጵያ ቡና ካደረጋቸው 9ጨዋታዎች 3ጨዋታዎችን አሸንፎ በ2 አቻ ተለያይቶ 4ቱን ተሸንፎ 11 ነጥቦችን ሰብስቦ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወላይታ ድቻ በአንፃሩ 9ጨዋታዎችን አድርጎ 2ጨዋታዎችን አሸንፎ 2ጨዋታዎችን አቻ ወጥቶ 5ቱን ተሸንፎ ማግኘት ከሚገባው 27ነጥቦች 8ቱን ብቻ አሳክቶ ከወራጅ ቀጠና በ2ነጥቦች ብቻ ርቆ 14ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ከወላይታ ድቻ በኩል ፀጋዬ ብርሀኑ ተመስገን ዱባ እና እርቂሁን ተስፋዬ በጉዳት እንዲሁም ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ ጋር ሲጫወቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው እና የ4 ጨዋታዎች ቅጣት የተላለፈበት ተስፉ ኤልያስ በቅጣት ለዚህ ጨዋታ ለቡድናቸው ግልጋሎት የማይሰጡ ሲሆን ይህ ቅድመ ዳሰሳ እስከተሰራበት ደቂቃ ድረስ በኢትዮጵያ ቡና በኩል የተሰማ አዲስ የጉዳት ዜና የለም።
መልካም ጨዋታ፤ እንዲሁም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለጌታችን ለመድሀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ። መልካም ገና።