የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት የዕለተ ዕሁድ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ቀሪ ስድስት ጨዋታዎች ዛሬ በክልል እና በአ/አ ስታዲየም ላይ የሚደረጉ ይሆናል።
በዚህ ዕለት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ደደቢት ከ ወልዋሎ አ.ዩ. የሚያደረጉት ጨዋታ ብቸኛው በአ/አ ስታዲየም የሚደረግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ነው።
ደደቢት በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ጅማሬው ላይ መዋዠቅ የተስተዋለበት ቢሆንም ከ6ኛው ሳምንት ጀምሮ ያሉትን ጨዋታዎች በተከታታይ ድል ማድረግ በመጀመሩ ወደ ሊጉ አናት መውጣት ችሏል። በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የሚመራው ደደቢት ከግብ ጠባቂው ክሌመንት አዞንቶ እስከ አጥቂዎቹ ጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው ድረስ ሙሉ ቡድኑ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል። በተከላካይ ክፍሉ ላይ አንጋፋው የቡድኑ አምበል ብርሀኑ ቦጋለ(ፋዲጋ) ጉዳት ላይ ቢሆንም በሌላኛው አንጋፋ ተከላካይ ስዩም ተስፋዬ ድንቅ ብቃት እና መሪነት እየተጓዘ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት ችሏል። ለዚህም ማሳያው ከተደረጉት 10ጨዋታዎች 5ግቦችን ብቻ ማስተናገዱ እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል። በአማካይ ስፍራ ላይ በርከት ያሉ እንደ አለምአንተ ካሳ፣ አቤል እንዳለ እና የአብስራ የመሳሰሉ ወጣቶችን የያዘው ደደቢት ወደ ቀድሞ ብቃቱ እየተመለሰ እንደሆነ ፍንጭ እያሳየ ከሚገኘው አስራት መገርሳ ጋር በማጣመር ድንቅ የአማካይ ክፍልን እያሳየን ይገኛል። በአጥቂ ስፍራ ላይም የብዙ ልምድ ባለቤቱ ጌታነህ ከበደ እና ወጣቱ አቤል ያለው ያላቸው ጥምረት የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮችን የሚያስፈራ ነው። ደደቢት በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአብዛኛዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ 4-4-2 የጨዋታ ዘይቤዎችን ሲጠቀም ተስተውሏል። ለዚህ የጨዋታ ዘይቤ መሳካት በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ሚና ማንሳት ተገቢ ነው። በተለይ አስራት እና የአብስራ በመሀል ሜዳ ላይ የሚያሳዩት ብቃት ከአጥቂዎቹ ያገኙትን ኳስ አይምሬነት ጋር ተዳምሮ ቡድኑን ላቅ ወዳለ ደረጃ እያደረሱት ይገኛሉ።
በወልዋሎ አ.ዩ. በኩል ዘንድሮ ከብሔራዊ ሊግ እንደማደጉ ተቀዳሚ አላማው በሊጉ መቆየት እንደሆነ አያጠራጥርም። ቡድኑ በሜዳውም ከሜዳውም ውጪ ሲጫወት በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እና መሀል ሜዳ ላይ ውበት እና ፍሰት ባለው ጨዋታ የሚጫወት ቡድን ነው። ለዚህ ማራኪ አጨዋወቱ አፈወርቅ ኀይሉ እና እዮብ ወ/ማርያም በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። ወልዋሎ አ.ዩ. በ በአብዛኛዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ 4-3-3 የጨዋታ ዘይቤን ሲጠቀም ተስተውሏል። በወልዋሎ በኩል ወደተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ በቁጥር ብልጫ መውሰድ ሲችሉ የቀኝ እና የግራ ተከላካዮቹ በረከት ተሰማ እና ተስፋዬ ዲባባ ለዚህ ቁጥር ብልጫ ትልቁን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ሙሉዓለም ጥላሁንን በጉዳት በማጣቱ ምክንያት የግብ ማግባት ችግር የተስተዋለበት ወልዋሎ ይህን አጥቂ ለዛሬው ጨዋታ ከጉዳቱ አገግሞ ማግኘቱ ለአሰልጣኙም ሆነ ለደጋፊዎቹ እፎይ የሚያሰኝ ዜና ነው።
- ማሰታውቂያ -
በ10ኛው ሳምንት አ/አ ስታዲየም ላይ ወልዋሎ አ.ዩ. ወልድያ ስፖርት ክለብን ገጥሞ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያይ ደደቢት በአንፃሩ ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ጌታነህ ከበደ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ታግዞ አርባምንጭ ከተማን 2-1 አሸንፎ መመለሱ ይታወሳል።
ወልዋሎ አ.ዩ. ካደረጋቸው 10ጨዋታዎች 4ቱን ከሜዳው ውጪ ያደረገ ሲሆን ዛሬ ወደ አ/አ ተጉዞ 5ኛ ከሜዳው ውጪ የሚያደርገው ጨዋታ ይሆናል፡፡ ወልዋሎ አ.ዩ. ካደረጋቸው 4 የሜዳው ውጪ ጨዋታዎች ወደ አ/አ ተጉዞ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን 3-1 ያሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛው ከሜዳው ውጪ ያስመዘገበው ድል ሆኖ ተመዝግቦለታል። አርባምንጭ ላይ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 1-1 እንዲሁም መቐለ ላይ ከመቐለ ከተማ ጋር ያለግብ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቶ ጅማ ላይ በጅማ አባጅፋር 3-0 ተሸንፏል።
ደደቢት በአንፃሩ 5 ጨዋታዎችን በሜዳው አከናውኗል። ካደረጋቸው 5 የሜዳው ላይ ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማን 2-1 ሲዳማ ቡናን 5-2 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ከወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከተማ ጋር በተመሳሳይ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።
በአጠቃላይ በፕሪሚየር ሊጉ ደደቢት 10ጨዋታዎችን አድርጎ 6ጨዋታዎችን አሸንፎ በ4 አቻ ተለያይቶ ያለምንም ሽንፈት 22 ነጥቦችን ሰብስቦ በሊጉ አናት ላይ ሲቀመጥ ወልዋሎ አ.ዩ. በአንፃሩ 10ጨዋታዎችን አድርጎ 2ጨዋታዎችን አሸንፎ 6ጨዋታዎችን አቻ ወጥቶ 2ጨዋታዎችን ተሸንፎ ማግኘት ከሚገባው 30ነጥቦች 12ቱን አሳክቶ ከደደቢት በ10 ነጥቦች አንሶ 10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ከደደቢት በኩል ብርሀኑ ቦጋለ በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ የማይኖር ሲሆን በወልዋሎ አ.ዩ. በኩል ኤፍሬም ጌታቸው እና እዮብ ወ/ማርያም በጉዳት እንዲሁም እንየው ካሳሁን በቅጣት በጨዋታው የማይሳተፉ ይሆናል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አ/አ ስታዲየም ላይ 10፡00 ሲል የሚጀምር ይሆናል።