የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረጉ ሲሆን ዛሬ (ቅዳሜ) አንድ ጨዋታ የተደረገ ሲሆን ነገ (እሁድ) ደግሞ ሰባት ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። በነገው እለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉትን ጨዋታ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
የጨዋታ ቀን: እሁድ ጥር 03/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌደራል አርቢትር ማኑኤ ወ/ጻዲቅ
የጨዋታ ቦታ: አፄ ፋሲለደስ ስታዲየም
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ዙርም በውድድር አመቱ በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ የተለያየ አቋም የሚያሳዩትን ፋሲል ከነማን እና ኢትዮጵያ ቡናን ያገናኛል። የዘንድሮው ፋሲል ከነማ በሜዳው ብዙ ጎል የሚያስቆጥር እና ከሜዳ ውጭ ማሸነፍ የተቸገረ ሆኖ እየተመለከትን ነው። በስዩም ከበደ የሚሰለጥነው ፋሲል ከነማ ከሜዳው ውጭ እስካሁን ምንም አይነት ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። የአሁኑ የፋሲል ከነማ ቡድን ትልቁ ጥንካሬ በሜዳው ብዙ ጎሎችን የሚያስቆጥር ቡድን መሆኑ ሲሆን በአንፃሩ ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከሜዳው ውጪ እጅግ ደካማ ውጤት እያስመዘገበ ያለ መሆኑ የነገው ጨዋታ በምን አይነት ውጤት የሚለው ጥያቄ ጨዋታውን አጓጊ አድርጎታል።
በካሳዬ አራጌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮው የውድድር ዓመት ኳስን ይዞ ለመጫዎት ሲሞክር ተስተውሏል። ይህም በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ውጤት ሲያስገኝለት ታይቷል። በፋሲል ከነማ በኩል ከፊት መስመር ያሉት ተጨዋቾች ሱራፌል ዳኛቸው፣ ሽመክት ጉግሳ፣ በዛብህ መለዮ፣ ሙጅብ ቃሲምና እና ማውሊ በመልሶ የማጥቃት ስልት ያላቸው ብቃት ለኢትዮጵያ ቡና ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት በ7 ግቦች እየመራ የሚገኘው አይምሬው ሙጅብ ቃሲም በነገው ጨዋታ ለኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
- ማሰታውቂያ -
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ፋሲል ከነማ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 3ቱን በሜዳው ያደረገ ሲሆን ከነዚህ 3ጨዋታዎች ድሬደዋ ከተማን፣ ሀዲያ ሆሳዕናን እና ባህርዳር ከተማን ሲያሸንፍ 11 ግቦችን አስቆጥሮ በአንዱም ጨዋታ ግብ ሳያስተናግድ መውጣት ችሏል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 3ቱን ሲያሸንፍ 3 አቻ ወጥቶ በአንድ ጨዋታ ሽንፈት በወልቂጤ ከተማ ሽንፈት በማስተናገድ የሊጉ አናት ላይ ከሚገኘው ከወልዋሎ አ.ዩ. በ2ነጥቦች ብቻ ዝቅ ብሎ በ12ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 4ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ ሲያደርግ በሁለቱ ጨዋታዎች ተሸንፎ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይቶ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች ደግሞ በ2ጨዋታዎች አሸንፎ በ2ጨዋታዎች ተሸንፎ በ3ጨዋታ ደግሞ አቻ ወጥቶ ማግኘት ከሚገባው 21 ነጥቦች 9 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በ3ነጥቦች ብቻ አንሶ በሊጉ 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ነገ በሚካሄደው እና ፌደራል አርቢትር ማኑኤ ወ/ጻዲቅ በሚመሩት ጨዋታ ፋሲል ከነማ የሚያሸንፍ ከሆነ የሌሎቹን ቡድኖች ውጤት ተንተርሶ የሊጉ መሪ መሆን ሲችል በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡና ድል የሚቀናው ከሆነ ከፋሲል ከነማ ጋር በነጥብ መስተካከል ያስችለዋል።
በፋሲል ከነማ በኩል ተከላካዮቹ ያሬድ ባየህ እና እንየው ካሳሁንን በጉዳት ከየገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በባህርዳሩ ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው አቤል ከበደ በቅጣት የማይሰለፍ ይሆናል።