የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት 7ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ።
የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት 8 ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረጉ ሲሆን 7ጨዋታዎች ነገ (ቅዳሜ) እንዲሁም 1ጨዋታ ደግሞ ከነገ በስትያ (እሁድ) የሚደረግ ይሆናል። ከነዚህ መካከል 6ቱ ጨዋታዎች ክልል ላይ ሲደረጉ ሁለቱ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ይደረጋሉ።
ቅዳሜ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ባህርዳር ላይ ባህርዳር ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ 9:00 ላይ የሚጀምር ይሆናል። ሁለቱ ቡድኖች የዘንድሮውን ውድድር በመልካም ሁኔታ መጀመር ተስኗቸው 4ኛ ሳምንት ውድድር ላይ ደርሰዋል። በ3ኛው ሳምንት ባህርዳር ከተማ ወደ ሀዋሳ አቅንቶ በሀዋሳ ከተማ 1-0 ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ በሪችሞንድ ኦዶንጎ ግብ ታጅቦ አዲስ አዳጊውን ሀድያ ሆሳዕናን 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል። ሁለቱ ክለቦች በደረጃ ሰንጠረዡ በአንድ ነጥብ ተበላልጠው ባህርዳር ከተማ በ4 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ድሬድዋ ከተማ ደግሞ በ3ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ ታፈሰ የምትመራው ይሆናል።
- ማሰታውቂያ -
በሌላ የሊጉ የ9 ሰዓት ጨዋታ ሁለቱን አዲስ አዳጊዎቹን ወልቂጤ ከተማን ከሰበታ ከተማ ጋር የሚያገናኘው ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል። በኢንተርናሽናል አርቢትር ብሩክ የማነብርሃን የሚመራው ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች በጣም ወሳኝ ነው። ጨዋታውን ወሳኝ የሚያደርገው ነገር ወልቂጤ ከተማ በ3ኛው ሳምንት ያገኘውን ድል ለማስቀጠል ሰበታ ከተማ ደግሞ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርገው ጨዋታ መሆኑ ነው። ሰበታ ከተማ በ3ኛው ሳምንት አዳማ ከተማን አስተናግዶ አቻ ሲለያይ ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በክለቡ ታሪክ በፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ 3ነጥቦችን ፋሲል ከተማን በማሸነፍ ማግኘት ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ሰበታ ከተማ በ1ነጥብ የሊጉ ግርጌ ላይ ሲገኝ ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በ4ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።