የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅድመ ዳሰሳ ወልድያ ከ ሀዋሳ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር ከ ድሬዳዋ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ሁለተኛ ጨዋታዎች ወይም የውድድር አመቱ 17ኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ በሚደረጉ 8ጨዋታዎች የሚቀጥሉ ይሆናል። ከነዚህ 8ጨዋታዎች 5ቱ ክልል ላይ ሲደረጉ ሶስቱ ደግሞ አ/አ ስታዲየም ላይ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ወልድያ ስፖርት ክለብ ከ ሀዋሳ ከተማ
ይህ ጨዋታ በሁለት የተለያየ ሁኔታ ላይ ባሉ እና በ16ኛው ሳምንት የተለያየ ውጤት ባስመዘገቡ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ጨዋታ ሲሆን ወልድያ እስካሁን በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ጉዞው ሜዳው ላይ ያልተሸነፈ ቡድን ሲሆን ከዚህም ባሻገር በሜዳው ካደረጋቸው 8 የሜዳው ላይ ጨዋታዎች የተቆጠረበት ግብ 1ብቻ መሆኑ ቡድኑ በሜዳው ያለውን ጥንካሬ የሚያሳይ ነው። ሀዋሳ ከተማ በተቃራኒው በዘንድሮው የውድድር አመት ከሜዳው ውጪ ተቸግሮ የሚታይ ቡድን መሆኑ በተደጋጋሚ ተስተውሏል። በ16ኛው ሳምንት ወልድያ ወደ አዳማ ተጉዞ በአዳማ ከተማ 3-1 ተሸንፎ ሲመለስ ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ በሜዳው ጅማ አባጅፋርን አስተናግዶ በሙሉዓለም ረጋሳ ድንቅ ግብ 1-0 በማሸነፍ ለዚህ ጨዋታ ቀርቧል።
- ማሰታውቂያ -
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ውጤት
ወልድያ ስፖርት ክለብ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ካደረጋቸው 16ጨዋታዎች 4ቱን አሸንፎ በ6 አቻ ወጥቶ በ6 ተሸንፎ 11ግቦችን አስቆጥሮ 15ተቆጥሮበት በ18 ነጥቦች እና በ5 የግብ እዳ 11ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ ከ16ጨዋታዎች 5ብቻ አሸንፎ እንደ ወልድያ ስፖርት ክለብ ሁሉ በ6ቱ አቻ ተለያይቶ ቀሪዎቹን 5ጨዋታዎች ተሸንፎ በ21 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ በዳዊት ፈቃዱ ሀትሪክ ታግዞ 4-1 ማሸነፉ ይታወሳል።
በወልድያ በኩል ረጅም ጉዳት ላይ የነበሩት ሰለሞን ገ/መድህንና አዳሙ መሀመድ የዛሬው ጨዋታ የሚያልፋቸው ይሆናል። በሀዋሳ በኩል ደግሞ ሲላ መሀመድ 5ቢጫ በመመልከቱ በቅጣት፣ አብዱልከሪም ሀሰንና ቸርነት አወሽ የወረቀት ስራ ባለመጠናቀቁ እንዲሁም መሳይ ጳውሎስ፣ ፀጋአብ ዬሴፍ እና ዬሃንስ ሴጌቦ ከ20 አመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመመረጣቸው በዚህ ጨዋታ ለቡድናቸው ግልጋሎት የማይሰጡ ይሆናል።
ፌደራል ዳኛ አክሊሉ ድጋፌ የሚመሩት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ልክ 9:00 ሲል በሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።
ጅማ አባጅፋር ከ ድሬዳዋ ከተማ
ዛሬ ከሚደረጉ 5ጨዋታዎች መካከል ጅማ ላይ የሚደረገው ሁለተኛ ጨዋታ ጅማ አባጅፋር ከ ድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉት ነው።
ጅማ አባጅፋር በዘንድሮው የውድድር አመት ከብሔራዊ ሊግ የመጣ ቢሆንም በሊጉ ወጥ አቋም በማሳየት እና ትልልቅ የሚባሉትን ቡድኖች ሳይቀር በማሸነፍ የሊጉ መሪዎች ተርታ መቀመጥ ችሏል። ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ የከዚህ ቀደም ውጤታማነቱን አጥቶ ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ሆኗል።
በ16ኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋር ወደ ወደ ሀዋሳ ተጉዞ በሀዋሳ ከተማ 1-0 ተሸንፎ ሲመለስ ይህንንም ተከትሎ ከመሪዎቹ ደደቢት እና መቐለ ከተማ የነበረውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠብበትን እድል አባክኗል። ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ በሜዳው የአምናውን ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ ያለግብ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታውን በማጠናቀቅ እዛው ወራጅ ቀጠና ውስጥ እንዲዳክር አስገድዶታል።
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ውጤት
ጅማ አባጅፋር ካደረጋቸው 16ጨዋታዎች 7ቱን አሸንፎ በ4 አቻ ወጥቶ በ5 ተሸንፎ 17ግቦችን አስቆጥሮ 12ተቆጥሮበት በ25 ነጥቦች እና በ5 የግብ ክፍያ 4ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ካደረጋቸው 16ጨዋታዎች 2ቱን ብቻ አሸንፎ በ8 አቻ ወጥቶ በ6 ተሸንፎ 7ግቦችን አስቆጥሮ 12ተቆጥሮበት በ14 ነጥቦች እና በ5 የግብ እዳ 15ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ድሬ ላይ ተገናኝተው ጨዋታቸውን በድሬዳዋ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
ከጅማአባጅፋር በኩል እንዳለ ደባልቄ በጉዳት ምክንያት የዛሬው ጨዋታ የሚያልፈው ሲሆን ከድሬዳዋ ከተማ በኩል ዘነበ ከበደ እና ሳምሶን አሰፋ በጉዳት የማይሰለፉ ይሆናል።
9:00 ሲል ጅማ ስታዲየም ላይ የሚካሄደውን ጨዋታ ኢ/ዳኛ ባምላክ ተሰማ የሚመሩት ይሆናል።
አርባምንጭ ከ ሲዳማ ቡና
በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ መጥፎ አቋም ማለት በሚቻል የውጤት መውረድ ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት የደቡብ ደርቢ ጨዋታ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ፍልሚያ የሚያደርጉበት ጨዋታ ስለሆነ ለተመልካች አጓጊ ይሆናል። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያምን አሰናብቶ በምትካቸው የቀድሞውን የሀድያ ሆሳዕና ዋና አሰልጣኝ የነበረውን እዮብ ማለን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው አርባምንጭ ከተማ በዘንድሮው ውድድር ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖታል። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ከተቀላቀለ በኋላ እስካሁን ያልወረደው አርባምንጭ የዘንድሮ አያያዙ ግን የሚያተርፈው አይመስልም። እንደ አርባምንጭ ከተማ ሁሉ ዋና አሰልጣኙን አለማየሁ አባይነህን ያሰናበተው ሲዳማ ቡና በተጋጣሚዎቹ ላይ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ እየቻለ ግብ በማግባት ችግር እና በተከላካይ ስህተቶች እየተሸነፈ ለመውጣት ተገዷል። አርባምንጭ ከተማ በ16ኛው ሳምንት ወደ መቐለ አምርቶ በመቐለ ከተማ የ4-0 አስደንጋጭ ሽንፈት የደረሰበት ሲሆን ሲዳማ ቡናም በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በኢትዮጵያ ቡና 1-0 ተሸንፏል። ስለሆነም ሁለቱም ቡድኖች ከ16ኛው ሳምንት ሽንፈታቸው ለመውጣት የሚያደርጉት ጨዋታ ስለሆነ አጓጊ ይሆናል።
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ውጤት
አርባምንጭ ከተማ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ካደረጋቸው 16ጨዋታዎች 3ቱን አሸንፎ በ4 አቻ ወጥቶ በ9 ተሸንፎ 10ግቦችን አስቆጥሮ 23ተቆጥሮበት በ13 ነጥቦች እና በ13 የግብ እዳ የሊጉ ግርጌ ላይ ሲገኝ ሲዳማ ቡና በበኩሉ ከ16ጨዋታዎች 3ብቻ አሸንፎ በ9ቱ አቻ ተለያይቶ ቀሪዎቹን 4ጨዋታዎች ተሸንፎ በ18 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ይርጋለም ላይ ተገናኝተው ጨዋታቸውን 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
በአርባምንጭ በኩል እስራኤል ሻጎሌ እና ፅዬን መርዕድ ከ20 አመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመመረጣቸው በዚህ ጨዋታ ለቡድናቸው ግልጋሎት የማይሰጡ ሲሆን ሲዳማ ቡና በኩል አበበ ጥላሁን በ5ቢጫ ካርድ ምክንያት በቅጣት፣ መሳይ አያኖ በጉዳት እንዲሁም ዮናታን ፍስሀ ሙጃይብ መሀመድ እና ሚካኤል አሲስ ደግሞ ከ20 አመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመመረጣቸው የማይሰለፉ ይሆናል።
ይህንን ጨዋታ ኢ/ ዳኛ ለሚ ንጉሴ በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ሲሆን ጨዋታው 9:00 ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።