የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀጥሉ ቅዳሜ 2 እንዲሁም እሁድ 5 ጨዋታዎች ሲከናወኑ ሰኞ ደግሞ 1 ጨዋታ የሚደረግ ይሆናል።
ቅዳሜ 09:00 ሰዓት ሲል በሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ላይ በሊጉ እኩል 7 ነጥቦችን የሰበሰቡት ሐዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ የሚገናኙ ይሆናል። ካደረጋቸው 6 ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቶ በሶስቱ የተሸነፈው ሐዋሳ ከተማ ማግኘት ከሚገባው 18 ነጥቦች 7ቱን ብቻ ሰብስቦ በሊጉ 8ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ድሬዳዋ ከተማም 1 ቀሪ ጨዋታ እየቀረው ከሐዋሳ ከተማ ጋር እኩል 7ነጥቦችን ሰብስቦ በ1 ግብ ክፍያ ብቻ በመብለጥ 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ለሴካፋ ውድድር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ወደኬንያ ተጉዘው የነበሩት ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ እና አማካዩ ፍሬው ሰለሞን(ጣቁሩ) ወደ ቡድኑ ተቀላቅለው ለቅዳሜው ጨዋታ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
10:00 ሲል አዲስ አበባ ስታዲየም ደደቢት ሲዳማ ቡናን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በጉጉት ከሚጠበቁ ጨዋታዎች መካከል ተጠቃሽ ነው። ደደቢት በ6ኛው ሳምንት ጨዋታ ወደ መቐለ ተገዞ በጌታነህ ከበደ እና አለምአንተ ካሳ ግቦች ታግዞ መቐለ ከተማን 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ መመለሱ ይታወሳል ይህንንም ተከትሎ ደደቢት በሊጉ 6ጨዋታዎችን አድርጎ በ10 ነጥቦች እና በ3 ንፁህ ግቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ሲዳማ ቡና በአንፃሩ 6ጨዋታዎችን አከናውኖ 5ነጥቦችን ሰብስቦ ከወራጅ ቀጠናው በ2 ነጥቦች ብቻ ከፍ ብሎ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት እና ወጣቱ አጥቂ አቤል ያለው ከሴካፋ መልስ ደደቢትን የተቀላቀሉ ሲሆን ተከላካዩ አበበ ጥላሁን እና አጥቂው አዲስ ግደይ በሲዳማ ቡና በኩል ሜዳ ላይ ይኖራሉ ተብሎ ሲጠበቅ በ6ኛ ሳምንት ከወልዲያ ከተማ ጋር ሲጫወቱ በ2 ቢጫ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ በጨዋታው የማይኖር ነው የሚሆነው።
እሁድ ውድድሩ ሲቀጥል ከሚደረጉት 5 ጨዋታዎች 4ቱ በተመሳሳይ 9፡00 የሚደረጉ ሲሆን አዲስ አበባ ላይ የሚደረገው ብቸኛ ጨዋታ 10:00 ላይ የሚደረግ ይሆናል።
- ማሰታውቂያ -
እሁድ በብቸኛው የአ/አ ስታዲየም ጨዋታ 10:00 ሲሆን ቅ/ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል። በ6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አርባምንጭ በሜዳው ከ ወልዋሎ አ.ዩ እንዲሁም ቅ/ጊዮርጊስ ደግሞ በሸገር ደርቢ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። 2 ቀሪ ጨዋታዎች የሚቀሩት ቅ/ጊዮርጊስ 8 ነጥቦችን ሰብስቦ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ 6ጨዋታዎችን ያደረጉት አዞዎቹ ከቅ/ጊዮርጊስ በ2 ነጥቦች አንሰው በ6 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። አበባው ቡጣቆ እና አቡበከር ሳኒ ከቅ/ጊዮርጊስ እንዲሁም ተከላካዩ ተመስገን ካስትሮ እና አማካዩ እንዳለ ከበደ ከአርባምንጭ ከተማ በኩል ከሴካፋ መልስ ቡድናቸውን የተቀላቀሉ ሲሆን ከቅ/ጊዮርጊስ በኩል ረጅም ጉዳት ላይ የሚገኙት ሳላዲን ሰይድ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ታደለ መንገሻ አሁንም ለቡድናቸው ግልጋሎት የማይሰጡ ሲሆን በሸገር ደርቢ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወቱ ጉዳት ያስተናገደው አሜ መሐመድም የመግባቱ ነገር አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ከአርባምንጭ ከተማ በኩል ቀለል ያለ ልምምድ ማድረግ ጀምረው የነበሩት አምበሉ አማኑኤል ጎበና ና ተሾመ ታደሰ(ክሮች) ጉዳታቸው አገርሽቶባቸው ከቡድኑ ጋር ወደ አ/አ መምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል።
9፡00 ሲል ከሚጀመሩት ጨዋታዎች መካከል አዲግራት ላይ የሊጉ መሪ ወልዋሎ አ.ዩ የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘውን መከላከያን የሚገጥምበት ጨዋታ ይጠቀሳል። በሊጉ ጥሩ አቋም እያሳየ የሚገኘው አዲስ አዳጊው ወልዋሎ አ.ዩ ማግኘት ከሚገባው 18 ነጥቦች 10ን አሳክቶ ሊጉን እየመራ ሲሆን መከላከያ በአንፃሩ ከ6 ጨዋታዎች 3 አቻ ተለያይቶ በ3ቱ ተሸንፎ 3 ነጥቦችን ሰብስቦ የሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል። በወልዋሎ በኩል አፈወርቅ በትናንትናው እለት ልምምድ ላይ መጠነኛ ጉዳት በማስተናገዱ በጨዋታው እንደማይኖር ተረጋግጧል። በሌላ የጉዳት ዜና ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበረው የመከላከያው ማራኪ ወርቁ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ከቡድኑ ጋር ወደ አዲግራት አልተጓዘም። በረከት አማረ በወልዋሎ.አ.ዩ በኩል ቴዎድሮስ በቀለ ከመከላከያ በኩል ከሴካፋ በመመለሳቸው በእሁዱ ጨዋታ ለክለባቸው ግልጋሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ 9ሰዓት ሲል አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ፋሲል ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል። ፋሲል ከተማ 5 ጨዋታዎችን አድርጎ 9 ነጥቦችን በመሰብሰብ 6 ጨዋታዎችን አከናውኖ እኩል 9ነጥቦችን መሰብሰብ ከቻለው አዳማ ከተማ በ2 ግብ ክፍያዎች በልጦ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በፋሲል ከተማ በኩል አጥቂው አብዱራህማን ሙባረክ እና ተከላካዩ አምሳሉ ጥላሁን እንዲሁም በአዳማ ከተማ በኩል አጥቂው ዳዋ ሁቴሳ አሸና አማካዩ ከነዓን ማርክነህ ከሴካፋ መልስ ቡድናቸውን ተቀላቅለዋል።
በሌላ የ 9ሰዓት ጨዋታ ሶዶ ላይ 5ነጥቦችን ሰብስቦ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በ6ኛ ሳምንት ሜዳው ላይ በደደቢት የ2-0 አስደንጋጭ ሽንፈት ያስተናገደውን መቐለ ከተማን የሚያስተናግድ ይሆናል። በወላይታ ድቻ በኩል ተክሉ ታፈሰ እና አብዱልሰመድ አሊ በጉዳት ምክንያት በጨዋታው ላይ የማይሳተፉ ሲሆን ፀጋዬ ብርሀኑ ከሴካፋ መልስ እሁድ ይሰለፋል ተብሎ ይጠበቃል። በመቐለ ከተማ በኩል አዲስ ጉዳት የሌለ ሲሆን አጥቂው አማኑኤል ገብረሚካኤል ከሴካፋ መልስ ከቡድኑ ጋር ወደ ሶዶ ተጉዟል።
በሌላ ጨዋታ ሰኞ 9:00 ሲል ጅማ ላይ ጅማ አባጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚጫወቱ ይሆናል። ጅማ አባጅፋር 6 ጨዋታዎችን አድርጎ 5ነጥቦችን ይዞ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ 1 ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከጅማ አባጅፋር በ3 ነጥቦች ከፍ ብሎ 8ነጥቦችን በመያዝ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኄኖክ አዱኛ ከጅማ አባ ጅፋር በኩል አማካዩ ሳምሶን ጥላሁን ከኢትዮጵያ ቡና ከሴካፋ መልስ ቡድናቸውን ተቀላቅለው ለእሁዱ ጨዋታ የሚደርሱ ይሆናል።
ለእሁድ 9:00 ወልድያ ላይ በሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም ሊካሄድ መርሃ ግብር ተይዞለት የነበረው የወልዲያ እና የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ጨዋታ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ እንደተራዘመ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
ሊጉን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ10 ነጥብ እና 3የግብ ክፍያ ሲመራ መከላከያ በ3 ነጥቦች እና በ4 የግብ እዳ የሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል።
[team_standings id=”6559″ title=”ደረጃ ሰንጠረዥ ” number=”16″ columns=”p,gd,pts” show_team_logo=”1″ show_full_table_link=”1″ align=”none”]