በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ እና ሰኞ ሲቀጥሉ እሁድ 5 ጨዋታዎች እንዲሁም ሰኞ 3 ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል።
እሁድ በተመሳሳይ 09:00 ሰዓት ሲል አዲግራት ላይ ካደረጋቸው 4 ጨዋታዎች ሶስቱን በአቻ ውጤት አጠናቆ አንዱን በማሸነፍ 6 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ሊጉን በ7 ነጥብ የሚመራውን ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናግዳል፡፡
በወልዋሎ አዲግራት በኩል ለብሔራዊ ቡድኑ በረከተ አማረን በማስመረጡ በሱ ቦታ ዘውዱ በቀለን ያሰልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡና መስዑድ መሀመድን በጉዳት እንዲሁም ሳምሶን ጥላሁን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በመጓዙ በጨዋታው ላይ የማይኖሩ ይሆናል።
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ ሰለሞን ገ/ሚካኤል
በሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታድየም በ5 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልድያ ከተማ ከ መቐለ ከተማ ይጫወታሉ። በወልዲያ በኩል ሁለት ተጫዋቾች (ተስፋዬ አለባቸው እና ብሩክ ቃልቦሬ) እንዲሁም በመቐለ ከተማ በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል የማይኖሩ ናቸው፡፡
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ ኢሳያስ ታደሰ
አርባምንጭ ላይ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማ እና መከላከያ የሚገናኙ ሲሆን ሁለቱም ማግኘት ከሚገባቸው 12 ነጥብ እኩል 2 ነጥብ በመያዝ 15ኛ እና 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ከአርባምንጭ ከተማ በኩል አማኑኤል ጎበና እና ወንደሰን ሚሊኪያስ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ አሰፋ ደቦጭ
- ማሰታውቂያ -
አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ሀዋሳ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ እሁድ 9፡00 ላይ በአዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን በአዳማ በኩል ደሳለኝ ደባሽ ፤ ቡልቻ ሹራ ፤ታፈሰ ተስፋዬ እንዲሁም ከሀዋሳ ከተማ በኩል ዳንኤል ደርቤ በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆኑ ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጧቸው ልጆች ከአዳማ ከተማ(ከነዓን ማርክነህ፤ዳዋ ሁቴሳ) እንዲሁም ከሀዋሳ ከተማ (ተክለማርያም ሻንቆ እና ፍሬው ሰለሞን) ለቡድናቸው ግልግሎት የማይሰጡ ይሆናሉ፡፡
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ ቴዎድሮስ ምትኩ
ቦዲቲ ላይ የመሳይ ተፈሪው ወላይታ ድቻ በሊጉ በ5 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ድሬዳዋ ከተማን የሚያስተናግድ ሲሆን ከወላይታ ድቻ ተክሉ ታፈሰ እንዲሁም የመድረስ ያለመድረስ ነገሩ ያልተለየለት በዛብህ መለዮ በጨዋታው የማይኖሩ ናቸው፡፡
ከድሬዳዋ ከተማ በኩል አማካዩ ያሬድ ታደሰ ፤ ረመዳን ናስር ፤ ሀብታሙ ወልዴ በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ናቸው፡፡
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ ሚካኤል አርዓያ
በሌላ ጨዋታ እሁድ እንዲደረግ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው አዲስ አዳጊው ጅማ አባጅፋር ከ ሲዳማ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ አዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም ላይ ሰኞ የሚደረግ ይሆናል። ጅማ አባ ጅፋር ከኢ.እ.ፌ የተጣለባቸውን ቅጣት ተከትሎ 150000 ብር እና ከ150 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንዲጫወቱ መወሰኑን ተከትሎ ጨዋታው አዳማ ላይ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። ከሲዳማ ቡና በኩል ትርታይ ደመቀ በቅጣት አዲስ ግደይ እና አበበ ጥላሁን ለብሔራዊ ቡድን በመጠራታቸው እማይኖሩ ሲሆን በተመሣሣይ ከጅማ አባጅፋር በኩል ሄኖክ አዱኛ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በመጓዙ ጨዋታው ላይ የማይኖር ይሆናል።
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ ተካልኝ ለማ
ቅዳሜ እና እሁድ አ/አ ስቴዲየም ላይ ሊካሄዱ እቅድ ተይዞላቸው የነበሩት 2 ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር እሁድ ባለበት ጨዋታ ምክንያት ወደ ሰኞ ተዛውረዋል። በዚህም መሰረት ሰኞ 9፡00 ላይ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ቅ/ጊዮርጊስ በ4ኛው ሳምንት ሜዳው ላይ 3-1 በሆነ አስደንጋጭ ውጤት የተሸነፈውን ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ይገጥማል ከኤሌክትሪክ በኩል አዲስ ነጋሽ በቅጣት ግርማ በቀለ ለሴካፋ ጨዋታ በማምራቱ የማይኖር ሲሆን በተመሳሳይ ከቅ/ጊዮርጊስ በኩል አቡበከር ሳኒ እና አበባው ቡታቆ የማይሰለፉ ይሆናሉ ።
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ እያሱ ፈጠነ
ከዚህ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ 11፡30 ሲል ሁለት ተጫዋቾችን ያስመረጡት ደደቢት ፋሲል ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ የ5ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ይሆናል አቤል ያለው እና አብዱራህማን ሙባሪክ ከደደቢት እና ከፋሲል የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።
ጨዋታውን የሚመሩት ዳኛ፡ ብሩክ የ/ብርሀን