ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ በተደረገው የዕድሜ ማጣራት 65 በመቶ ምርመራውን ማለፍ አልቻሉም።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው ይህን ያስታወቀው።
በዚህ ዓመት ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች በሚገኙ በ2 ሺህ 10 የእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ የዕድሜ ምርመራ ተደርጓል።
በምርመራው በትክክለኛ ዕድሜ የተገኙትና ምርመራውን ማለፍ የቻሉት 702 ተጫዋቾች ብቻ ሲሆኑ፥ 1 ሺህ 308ቱ ደግሞ ምርመራውን ማለፍ አልቻሉም።
- ማሰታውቂያ -
982ቱ የመጀመሪያውን የተክለ ሰውነት ምርመራ ማለፍ ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን 326ቱ የኤም አር አይ ምርመራ ማለፍ እንዳልቻሉ ተነግሯል።
ባለፉት ዓመታት በዕድሜ ማጭበርበር ምክንያት ብሄራዊ ቡድኑን የሚተኩ ተጫዋቾች ማግኘት አዳጋች እንደነበር የብሄራዊ ቡድን ሐኪምና በፌዴሬሽኑ የህክምና ኮሚቴ አባል ዶክተር አያሌው ጥላሁን ተናግረዋል።
አሁን ግን በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘ ምርመራ መደረጉ ለብሄራዊ ቡድን ተተኪ ወጣቶች በትክክለኛ ዕድሜ መገኘታቸውን ነው የገለጹት።
በዕድሜ ማጣራት ስራው አብዛኞቹ ተጫዋቾች የልደት ሰርተፍኬት ማጭበርበር፣ መታወቂያ በሌላ ሰው ማሰራት እና የምርመራ ውጤትን ያለመቀበል ችግሮች መታየታቸውን ገልጸዋል።
አብዛኛዎቹ አሰልጣኞች ውጤት ከመፈለግ የተነሳ የዕድሜ ምርመራ እንዲደርግ እንዳማይፈልጉም ነው ዶክተር አያሌው የገለጹት።
የዕድሜ ማጣራት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ደግሞ በፌዴሬሽኑ የህክምና ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነስረዲን አብዱራሂም ናቸው።
በምርመራው ከ12 በላይ ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች መሳተፋቸውና የምርመራ ስራው አዲስና ዘመናዊ መሆኑንም ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ ቀጣይ በሚደረጉ ከ17ና ከ20 ዓመት በታች የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግና ያልተገባ ተጫዋች በሚያሰልፉ ክለቦች እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል።
ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜሲካሄድ፤ ከ20 ዓመት በታች ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ ነው።