በዘንድሮው የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር እየተሳተፈ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሁለተኛው ዙር አለፈ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት በሀዋሳ ስታዲየም ከሲሼልሱ ኮት ዲኦር ክለብ ጋር ባደረገው ጨዋታ 3 ለ 0 እየመራ በተከሰተው ከባድ ዝናብ ጨዋታው ሳይጠናቀቅ ቀርቷል።
ጨዋታው ከተቋረበት 54 ደቂቃ ጀምሮ ዛሬ ረፋድ አራት ሰዓት ቀጥሎ የተካሄደ ሲሆን የውጤት ለውጥ ሳይኖር በ3 ለ 0 ተጠናቋል።
ግቦቹን ሳላዲን ሰይድና አስቻለው ታመነ በጨዋታ አዳነ ግርማ ደግሞ በፍጹም ቅጣት ምት ከመረብ ማሳረፍ ችለዋል።
- ማሰታውቂያ -
ባለፈው ሳምንት ከሜዳው ውጪ በሳላዲን ሁለት ግቦች 2 ለ 0 በሆነ ውጤት በመርታት አስቀድሞ የማለፍ ዕድሉን ያሰፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰጠውን ከፍተኛ የማለፍ ዕድል ማሳካት ችሏል።
ፈረሰኞቹ ኮት ዲኦርን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጪው መጋቢት መጀመሪያ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው ኤ.ሲ ሊዮፓርድስ ክለብ ጋር የሁለተኛ ዙር መጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።
በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መከላከያ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ውድድርን ከካሜሮኑ ዮንግ ስፖርትስ አካዳሚ ጋር በማድረግ በደርሶ መልስ ጨዋታ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በመሸነፍ ከውድድር ውጪ መሆኑ ይታወቃል።