በ 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ 2ኛ ጨዋታ የተከናወነ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና በአማካዩ መስዑድ መሀመድ ብቸኛ ጎል አሸናፊ በመሆን ለእሁዱ ፍፃሜ ማለፉን አረጋግጧል።
እንደትናንትናው ጨዋታ ሁሉ በድንቅ የደጋፊዎች ዝማሬና ጭፈራ እና ዝናብ ታጅቦ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 73ኛው ደቂቃ ድረስ ጎል ሳይስተናገድበት ቆይቷል።
3ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ እያሱ ታምሩ ከበረኛው ጋር ተገናኝቶ የሞከረውን ኳስ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 12ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ እንዲሁም 15ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም ቅብብል ወደ ጎል መድረስ ችለው መስዑድ መሀመድ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመቷቸው ኳሶች በግቡ አናት ላይ ወጥቷል።
ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል መድረስ በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ 18ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ካሉሻ አልሀሰን የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ከክልሉ መውጣቱን ተመልክቶ ከርቀት የመታውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው ቤኒናዊ ግብ ጠባቂ ሀሪትሰን በቀላሉ ይዞታል። ከ1 ደቂቃ በኀላ የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ ሾልኮ ወጥቶ ያገኘውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ መቶት በረኛው በቀላሉ አድኖታል። 40ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ካሉሻ አልሀሰን ከመሀል ሜዳ ጀምሮ ከዲዲየር ሊብሬ ጋር 1-2 ተጫውቶ የሞከረውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪትሰን በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 1ደቂቃ ሲቀረው ሳሙኤል ሳኑሚ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ቶማስ ስምረቱ አሻግሮት ሳሙኤል ሳኑሚ በግንባሩ ገጭቶት በረኛው በቀላሉ ይዞታል
በስታዲየሙ ታድሞ ለጨዋታው ድምቀት የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ በጥቂቱ
አንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በፈጣን እንቅስቃሴ እና የኢትዮጵያ ቡና የበላይነት የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽም 53ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ እያሱ ታምሩ የመታው ግሩም ቅጣት ምት ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። 71ኛው ደቂቃ ላይ እያሱ ታምሩ የመታውን ኳስ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ሲመልሰው ሳሙኤል ሳኑሚ አግኝቶ የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሙ ለትሞ ተመልሷል። ከ2 ደቂቃዎች በኀላ 73ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ድንቅ አማካይ መስዑድ መሀመድ ከቀኝ በኩል ያገኘውን ኳስ አክርሮ መቶ ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ለእሁዱ ፍፃሜ ማድረስ ችሏል።
በጨዋታው በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ብቃት ያሳየው የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ መስዑድ መሀመድ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ከአ/አ እግርኳስ ፌደሬሽን ጊዜያዊ ሰብሳቢ አቶ በለጠ ዘውዴ እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል።
- ማሰታውቂያ -
መርሃ ግብሩ እሁድ ፍፃሜውን ሲያደርግ 8:00 ላይ የደረጃ ተፋላሚዎቹ ጅማ አባጅፋር እና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ሲገናኙ 10:00 ላይ ቅ/ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና ለፍፃሜ የሚጫወቱ ይሆናል።