በይስሐቅ በላይ
2 ሰከንድ ምን ያህል ዋጋ አላት ወይም
ምን ያሳጣል?ብለን ብንጠይቅዎና
መልሰንም 50 ሺህ ዩሮ ወይም 1
ሚሊዮን 609.270 የኢትዮጵያ ብር ብንልዎ
ያምኑ ይሆን? አዎን ይሄ ግን በእርግጥም
ሆኗል፡፡
የአለምን የማራቶን ሪከርድ ለመስበር
ጫፍ የደረሰው ቀነኒሣ በቀለ ከዋናው ሽልማቱ
40 ሺህ ዩሮ ወይም 1 ሚሊዮን ሁለት መቶ
ስልሳ ዘጠኝ ሺህ በተጨማሪ ወደ ካዝናው
ሊከተው የነበረው 50 ሺህ ዩሮ ቦነስ ወይም
1 ሚሊዮን 609 ሺህ 270 የኢትዮጵያ ብር
በሚያስቆጭ መልኩ በሁለት ሰከንድ ምክንያት
አምልጦታል፡፡
ቀደም ሲል ሁሌም ከታላላቅ ውድድሮችና
ከአሽናፊዎች ተርታ ሲነሣ የነበረው ነገር ግን
ከቅርብ ጊዜ በኋላ በአትሌቲክሱ መድረክ
የተረሣ የሚመስለው የአትሌት ቀነኒሣ ስም
ከበርሊኑ የማራቶን ድሉ በኋላ ከፍ ብሎ
መነሣት ጀምሯል፡፡
የቀድሞ የኦሎምፒክ፣የአለም የ5 ሺህ
የ10 ሺ ሜትር አሸናፊና ባለ ሪከርዱ የ37
አመቱ ቀነኒሣ በቀለ በ46ኛው የበርሊን
ማራቶን በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት መመለሱን
ቢያውጅም በኬንያዊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ
ተይዞ የነበረውን የአለም ሪከርድ በመስበር
ሌላ ወርቃማ ታሪክ ለማፃፍ የነበረው እድል
በሁለት ሰከንዶች እንቅፋትነት ከሽፎበታል፡፡
ካለፈው አፕሪል ወር ወዲህ በጉዳትና
በተለያዩ ምክንያቶች ውድድሮችን እያቋረጠ
ሲወጣ፣ በተለያዩ መድረኮች ከመሳተፍ
ርቆ ለነበረው ቀነኒሣ ብቻ ሣይሆን በርካታ
አትሌቲክስ አፍቃሪያን በርቀቱ የተሻለ ተስፋን
እንዲስንቁ አድርጓል፡፡
ቀነኒሳ ለረዥም ጊዜ ሲታገለው
የነበረውን ጉዳት አሸንፎ በበርሊን ማራቶን
ለአለም የማራቶን ሪከርድነት የቀረበ 2፡01፡
42 የሆነ የርቀቱ ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት
በማስመዝገብ ካሸነፈ በኋላ ለሚዲያ ሰዎች
እንደተናገረው “ይሄ ውጤት በተሻለ አቋምና
ብቃት ላይ እንደምገኝ ያሳየ ነው፤ዝግጅቴም
ከምፈልገው በጣም ያነሰ ቢሆንም በድሉ
ደስተኛ ነኝ፤ ከዚህ በላይም በጣም መሮጥ
እችላለሁ፡፡ የአለም የማራቶን ሪከርድ ወደ
ቤቱ (ኢትዮጵያ)በቅርቡ ይመለሳል” ካለ በኋላ
“የሩጫዬና የአሸናፊነቴ ዘመን አሁንም ገና
እንደላበቃ አሳይቼያለሁ” በማለትም
ተናግሯል፡፡
“እውነት ለመናገር በሁለት
ሰከንድ ልዩነት ሪከርዱን ለራሴም
ለሀገሬም ባለማምጣቴ በጣም
አዝኛለሁ፤ እድለኛም አልነበርኩም
ነገር ግን አሁንም ተስፋ
አልቆርጥም”ያለው ቀነኒሳ በቀለ
“ዝግጅቴ ለማራቶን በጣም ትንሽ
ነው፤ ለሪከርድ ደግሞበትንሹ 4
እና 5 ወር ያስፈልጋል የማራቶንን
ሪከርድ ማሳካት እችላለሁ፤ በፍፁም
እጅ አልሰጥም” ብሏል የበርሊን
ማራቶን አሽናፊውና የማራቶን
ሁለተኛው የምርጥ ሰዓት ባለቤት
የሆነው ቀነኒሳ በቀለ፡፡
የ37ቱ አመቱ ቀነኒሣ
በቀለ በበርሊን ማራቶን ስሙ
ከአሸናፊዎች ተርታ ቀድሞ ሲጠራ
የአሁኑ ሁለተኛው ሲሆን አሁን
ያስመዘገበው 2፡01፡41 የሆነው
ሰዓት ደግሞ የአለም የማራቶን
ሪከርድ ባለቤት ከሆነው ኬንያዊው
ኤሊውድ ኪፕቾጌ 2፡01፡39 ቀጥሎ ሁለተኛው
የአለማችን ምርጡም ሰዓት ነው፡፡
ከዚሁ ከበርሊን ማራቶን ዜና ሳንወጣ
ኢተዮጵያዊያን አትሌቶች በጀርመን ዋና
ከተማ ደምቀው ውለዋል፤ ኢትዮጵያዊያን
አትሌቶች በውድድሩ ለቀረቡትና ሪከርድ
ሆነው ከተመዘገቡት ከ43 በላይ ሯጮችን
ቀድመው በመግባት ስማቸውን ከአሸናፊዎች
ተርት አስፍረዋል፡፡ በወንዶች ማራቶን
ከቀነኒሣ በአንድ ደቂቃ ሰባት ሰከንድ ባነሰ
ሰዓት በመግባት ብርሃኑ ለገሰ ሁለተኛ ሲሆን
ሌላው ኢትዮጵያዊ ሲሳይ ለማ 2፡03፡36
በማስመዝገብ በሶስተኝነት አጠናቋል፡፡
የወንዶቹን ያህል የበርሊን የሴቶች
ማራቶንም በኢትዮጵያዊያን ሴት
አትሌቶች ቁጥጥር ሥር ሆኖ ነው
የተጠናቀቀው፤ኢትዮጵያዊያኖች እሸቴ
በከሪ በአንደኝነት ማሬ ዲባባ በሁለተኝነት
እንዲሁም ሄለን ቶላ በአራተኛ ደረጃነት
ውድድራቸው በማጠናቀቅ የኢትዮጵያዊያን
የበላይነትን አረጋግጠዋል፡፡ ኢትዮጵውያን
ከ1-3 ያለውን ደረጃ እንዳይዙ ሳሊ ቺፕዮጌ
ሁለተኛ በመውጣት አጨናግፋባቸዋለች፡፡