THE BIG INTERVIEW WITH DANIEL DEMISSE
በዮሴፍ ከፈለኝ
- ማሰታውቂያ -
ለአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ፍቅርና አክብሮት አለው፡፡ የጎፈረውን ፀጉሩን በመቀስ ቆርጦበት እንዲያስተካክል ሲያደርግው በእሺታ የመቀበል ፍቅር፡፡ ይህን አንድ አሰልጣኝ አሁን ቢያደረግስ…?…መልሱን ለተጨዋቾቹ…ተወልዶ ያደገው በተለምዶ ቃሊቲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፤ባለፉት 5 አመታት ለወልዲያ ከተማ፣ ለኢትዮጵያ መድን፣ ለባህርዳር ከተማና ለኢትዮጵያ ቡና ተጫውቶ በ2ዐ12 የገ/መድህን ሃይሌውን መቐለ 7ዐ አንደርታን ለማገልገል ፊርማውን አኑሯል፡፡ የልጅነት ህልሙ ከነበረው ኢትዮጵያ ቡና ለምን ለቀቀ? ለመቐለ 70 አንደርታስ ምን ለማድረግ አቅዷል? በሚሉና ሌሎች እግር ኳሳዊ ጉዳዮች ዙርያ የመሃል ሜዳው ታጋይ ዳንኤል ደምሴ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ያደረገው ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡
ሀትሪክ፡-ወደ መቐለ ያደረከው ዝውውር በሠላም ተጠናቀቀ?
ዳንኤል፡- አዎ በሠላም ተጠናቋል፡፡ የምፈልገውን አግኝቻለው፡፡ የ1 አመት ኮንትራት ነበረኝ ነገር ግን አልፈልግም ብዬ ከቡና ተሰናብቻለው እንድመለስ ፈልገው ነበር ነገር ግን መልቀቂያውን በፍጥነት በማግኘቴ ዝውውሬ ተጠናቋል፡፡ መቶ አለቃ ፈቃደ ጋር ሄጄ ሳናግረው ለማስቀረት ሞክሮ ነበር እኔ ግን አልፈለኩም፡፡
ሀትሪክ፡- …አልመለስክልኝም… በአጨዋወት ልዩነት ብቻ ነው ከቡና የለቀከው…?
ዳንኤል፡- …ለቡና ያለኝ ፍቅር ከፍተኛ ነው፤ቡናንን የማገልገል ፍላጎቴም አስገራሚ ነበር፡፡ የለቀኩት በሌላ ሰው ግፊት እንጂ ፍላጎቱ አልነበረኝም፡፡ በቡና የተደረገብኝ ነገር ደስ የማይል ነው እንደተጨዋች ይሄ ሊደረግ አይገባም፡፡ ዝግጅት ሲጀመር 8ቱ የሚሰናበቱ ልጆች ሲጠሩ እኔ አልተጠራሁም…ነገር ግን ዝግጅት እንደምሄድ ብቻ ነው የማውቀው፤ለዝግጅት ለመነሳት እያሰብኩና እየተዘጋጀሁ ሳለ የቡድን መሪው ደወለና የምንፈልገው የሆነ ልጅ አለ ካልፈረመ አንተ ትመጣለህ አለኝ ደነገጥኩ ቡና ከልቤ ያገለገልኩት ቡድን ነው እንዴት ይሄን ያደርጋሉ ብዬ ተከፋሁ፡፡ የምንፈልገው ልጅ ካልፈረመ እንጠራሃለን እስከዚያ ድረስ ቤትህ ቁጭ ብል የሚባልበት ሃገር ላይ ነው ያለነው…እኔ የማውቀው አሰልጣኙ እንደሚፈልገኝ ነው ግን ያ አልሆነም አሰልጣኙ ቡናን እየመራ ነው? አይመስለኝም ካልፈለጋችሁኝ ሌላ የሚፈልገኝ ክለብ ጋር ልሄድ ስል ጠብቅ አሉኝ፡፡ ሲመረኝ መቶ አለቃ ጋር ስሄድ እስካሁን ዝግጅት አልገባህም እንዴ? አለኝ እርሱ ይህን ሁሉ አያውቅም፡፡ በሌላ ጊዜ ስደውል ባንተ ጉዳይ ብዬ ብዬ አቃተኝ አለኝ ስራ አስኪያጁ አቶ ስንታየሁ ጋር ስሄድ ያንተ ነገር ግራ ገባን አሉኝ ታዲያ ምን ላድርግ… መረረኝ ከእኔ የተሻለ አቋም ያሳዩት የቡድን ጓደኞቼ እነ አቡኪና እነ ኢያሱ የሚያውቁት እንደምቀጥል ነበር ነገር ግን አልሆነም ይሄ በጣም አስከፍቶኛል፡፡ ተጨዋቾቹ አሁን ድረስ ይደውላሉ እንድመለስ ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርተዋል፡፡ በቡና ጭንቅላቴ ተጎዳ እንዴትስ ልመለስ? እንደ ሰው የሆነ ሰዓት ላይ ጥሩ አልነበርኩም በኋላ ግን ወደ ምርጥ አቋሜ ተመልሼ ቡድኑን በደንብ አገልግያለው…… ወደ 7 እና 8 ጨዋታ ላይ ደግሞ የተቃራኒ ቡድኖችም ይሁኑ የቡና ደጋፊዎች አጨብጭበውልኛል፡፡ ለታላላቆቹ ለነመስኡድ አልተመለሱም በኳስ ተጨዋች ላይ አይደረግም… ከዚህ በኋላ ቡና መቼም አልመለስም ገድለውኛል… አስከፍተውኛል፡፡ ቢሮኮ እኛ አናውቅም ይላሉ..ማነው የሚያዘው….? ስለኔ ከቡድኑ አመራሮችና ከክለቡ በላይ ከአንድ ደጋፊ እሰማለው ይሄ አሳዝኖኛል…ነገር ግን ቡናን ከልቤ ስለምወድ መልካሙን ነው የምመኘው…..አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በደንብ ይፈልገኝ ነበር ዳንኤል ኳስ ስለሚችልና ከኋላ የመጀመር አቅም ስላለው ወደ ኋላ መልሼ ላጫውተው ብሎ አስቦም ነበር እኔ ግን ወደ ኋላ መመለስ አልፈለኩም ለማንኛውም ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ መልካም የውድድር አመት እመኛለው……
ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ገ/መድህን ፈለገህ ወይስ አንተ…?
ዳንኤል፡- ተፈላልገን ነው /ሳቅ/ በእርግጥ ከገ/መድህን ጋር የመስራት እድል ሳገኝ ደስ ብሎኝ ልፈርም ችያለው ኮንትራቴ ለ2012 ነው ጥሩ ጊዜ እንደሚኖረኝ ተስፋ አደርጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- …የመቐለ ደጋፊዎችን እንዴት አገኘሃቸው…?
ዳንኤል፡- …በርግጥ ፈርቼ ነበር ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ ነው የተቀበሉኝ ቡና ከመቀለ ሲጫወት አግሬሲቭ ሆኜ ተፋልሜያለው ያንን ሁሉ ረስተው በደስታ ተቀብለውኛል አመቱን ሙሉ በሠላም ባለቀ ብዬ ተመኘሁ፡፡ ቡና መቀለ መጥቶ በሠላም ተቀብለውት እኛም እዚያ ሄደን በደንብ ተቀብለውን በሠላም ሲያልቅ እንዳይ ተመኘሁ፡፡ በኳስ ውስጥ ያለ ነገር ስለሆነ ሠላሙ እንዲመለስ ተመኘሁ፡፡ ከአንድም ሁለቴ ከነርሱ ጋር ስጫወት በጣም አሪፍ ነበርኩ፡፡ መፋለሜን ሁሉ ረስተው ተቀብለውኛል ኳስ እንደዚህ ሲሆን ነው የሚያምረው፡፡ በመቀለ የተካሁት ሻይቡ ጅብሪልን ነው ከርሱ የተሻልክ ነህ ብለው አበረታተውኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …በሁለቱ ክለቦች መሀል ሠላም እንዲሰፍን የአምሳደርነት ሚና ለመወጣት ተዘጋጅተሃል…?
ዳንኤል፡- …በጣም…የሁለቱም አርማ በጋራ አሰርቼ ስታዲየሙን ብዞር ደስ ይለኛል፡፡ ወቅታዊው ነገር አስፈሪ በመሆኑ ሠላም ማስፈን የግድ ይሆንብናል፡፡ በዚያ ላይ ለብሔራዊ ቡድናችንም ማሰብ አለብን፡፡ በኛ ተግባር ነው ብሔራዊ ቡድኑ ጎል አላገባም ደጋግሞ ተሸነፈ የምንለው…ይው ከቻን ውጪ ሆንን በጣም ነው ቅር ያለኝ እኛ ምንም ሳናደርግ ብሔራዊ ቡድኑ እንዴት ጎል ያግባ? እንዴትስ ውጤት ያምጣ? ደጋፊው ሲፋቀርና አንድነት ሲኖር ውጤት ይመጣል… በቃ የቡና ደጋፊ ጋር ሠላም እፈልጋለው የወጣና ለፀብ የሚያነሳሳ ነገር ሳላሳይ ቡናን መግጠም እፈልጋለው ለዚህም ቃል ገብቻለው በፍፁም ኢትዮጵያ ቡና ላይ ቂም አልያዝኩም.. የኳስ ህይወት መሆኑን ማመን አለብኝ፡፡ እግዚአብሔር ከኔ ጋር ሆኖ ያሰብኩትን ፍቅር ባሳይ ደስ ይለኛል፡፡ ታውቃለህ ምን እንደተመኘሁ? የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ሆኖ ራሴ አበባ ይዤ ወርውሬ ሠላማዊ አየር ቢነፍስ….ማርያምን በጣም ደስ ይለኛል ሰላም ይሰፍናል ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- …ቤተሰቦችህን በውሳኔህ ዙሪያ አማክርክ…?
ዳንኤል፡- …አባቴ አልፈራም እናቴ ግን እንድርቅባት ስለማትፈልግ ቅር ብሏታል ቡናን ሁሉ አማረረች…አባቴ ምንም ችግር የለም ብሎ ነው የሚያስበው…ኳስ ተጫውቶ ስላሳለፈ አልሰጋም…በደንብ ይቀበሉሃል ብሎ ነው የሸኘኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ትዳር…ትዳር ሸተተኝ…አገባህ እንዴ…?
ዳንኤል፡- …ጉዳዩንኮ የያዘው ፌዴሬሽኑ ነው…/ሳቅ በሳቅ/…ስብሰባና ምርጫ ሲያራዝሙ የኔን ሠርግንም አራዘሙብኝ…ውድድሩንም ሆነ እኔንም የሚመራው ፌዴሬሽኑ አይደል…?…(ሳቅ በሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …የቡና ደጋፊ ይከፋብኛል ብለህ አልሰጋህም…?
ዳንኤል፡- …በጣም ፈርቼ ነበር…በቡና እንድቆይ የፈለጉ በርካታ የቡና ደጋፊዎች አሉ… በመሄዴ በጣም ተከፍተዋል…፤…ቡናን ጠልቼ አላውቅም ክብሬ ተነክቶ ነው የተሰናበትኩት እንጂ አልወጣም ነበር በተለይ የአሰልጣኘ ካሳዬ አራጌ ታክቲክን በደንብ ማወቅ እፈልግ ነበር ወደ መቐለ ስመጣ መገፋቴ እየተሰማኝ ነው አሁንም ያለኝን አውጥቼ ጥሩ መሆኔን ማሳየት እፈልጋለው…… ደጋፊው ከኔ በላይ ስለኔ የሚያውቅበት ክለብ በመሆኑና የነበረውን ሁኔታ ስለሚያውቁ ሲያፅናኑኝ ከርመዋል፡፡ ደፍሮ መጥቶ የተናገረኝ የለም…. የእነሱ ስሜት ግን ተጎድቷል በዚህም አዝኛለው፡፡
ሀትሪክ፡-መቐለ ከተማን እንዴት አገኘሃት?
ዳንኤል፡- ፌስቡክ ላይ ስለመቐለ የነገረውን አላየህም እንዴ? አንዱ የመቐለ ዩኒቨርስቲ ደረሰውና.. ጓደኞቹ የት ደረሰህ? ሲሉት መቐለ አላቸው…… ምን ቢሉ ጥሩ ነው እንዴ? ዲቪ ወጣልኝ አትልም እንዴ ብለው መለሱለት… መቐለ አሪፍ ከተማ ነች በርግጥ አሁንም ያለሁት ካምፕ ውስጥ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-የዳንኤል ምርጥ ጊዜ ቀጣዩ ዘመን ነው?
ዳንኤል፡- /ሳቅ/ አሰልጣኝ ገ/መድህን የሚፈልገው ነገር እኔ አለኝ አጠገቤ ያሉት ተጨዋቾችም ለእኔ አጨዋወት የሚሆኑ ናቸውና በዚህ አመት የተሻለ ለመሆን እጥራለሁ በዚህ አመት ጥሩ ሆኜም ወደ ብሔራዊ ቡድን መመለስ እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡-ለብሔራዊ ባለመመረጥህ ቅሬታ አለብህ እንዴ?
ዳንኤል፡- ዳዊት እስጢፋኖስ አንዴ የተናገረው ነገር ልክ ነው፡፡ ለብሔራዊ ቡድን ባለመመረጡ ዙሪያ ሲናገር “ምርጫ ሲደረግ ቤት ቶሎ እገባና ኢትዮጵያዊ ነኝ ወይስ የሚለውን ለማወቅ ፓስፖርቴን አያለው” ብሏል ይሄ እውነት ነው…. በብሔራዊ ቡድን ምርጫ ላይ መዘለሌ አልተዋጣልኝም በቦታዬ ምርጥ ሆኜ ብጫወትም ሳልመረጥ ቀርቻለው የስሁል ሸረ፣ የአዳማና የጅማ አባጅፋር ደጋፊዎችኮ አጨብጭበውልኛል… ጥሩ ነበርኩ አሁንም ጠንክሬ ሰርቼ ለአሰልጣኙ ጥሩ ነገር እንዳለኝና እኔን መዝለሉ ልክ እንዳልነበር ማሳየት እፈልጋው፡፡ ወደ ነበርኩበት ምርጥ አቋም ለመመለስ ጠንክሬ እሰራለው ከጎኔ ያሉትም በተቃራኒነት ስጫወት ስላዩኝ በዝውውሩ ተደስተዋል የተሻለ አመት ይሆንልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከወጡት ተጨዋቾች አንፃር ያንተ ኃላፊነት ከበድ አይልም?
ዳንኤል፡- ኃላፊነቱ ከበድ ይላል…. ቡድኑን በነበረበት ደረጃ የማቆየት ኃላፊነት ተጥሎብኛል ትንሽ የቡድኑ አቋም ወረድ ቢል ሪስክ አለው ይሄንንም ኃላፊነት ለመሸከምና ኃላፊነቱን ለመወጣት ተማምኜ ነው የፈረምኩት ስለቦታዬ ሳስብ ቆይቻለው ሁለት ተጨዋቾች ለቀዋል፡፡ የለቀቁት ተጨዋቾች ጥሩ ነበሩ በቦታዬ የነበረውና የለቀቀው ተጨዋች ከእኔ የተሻሉ ነበሩ ነገር ግን በርትቼ ከሰራሁ እንደነርሱ እንደምሆን ርግጠኛ ነኝ የጅብሪልን ቦታና ኃለፊነት ለመተካት እንደምችል ርግጠኛ ነኝ….. ጉራ ሳይሆን የልፋቴን ውጤት እንደማገኝ አምናለው እንደርሱ እንደምሆን ከፍ ሲልም የተሻለ ተጨዋች እንደምሆን አምኜ ነው ለመቐለ የፈረምኩት… ከእግዚአብሔር ጋር ይሳካል፡፡
ሀትሪክ፡- መዝናናት ያበዛል የሚሉ ሰዎች በመቐለ ቆይታህ ስጋት ገብቷቸዋል…..
ስጋቱ ልክ ነው?
ዳንኤል፡- ምን ማለት ነው መዝናናት ያበዛል? አልገባኝም እንዴት ነው ትርጉሙ? አዲስ አበባ ቃሊቲ ተወልጄ ነው ያደኩት.. ብዝናናኮ ብዙ ነገር አውቅ ነበር… ስለ ቦሌ ብትጠይቀኝ በቦታው ሳልፍ ነው የማውቀው… ይሄ ነገር ተጋኗልኮ፡፡ የሚሻለው በነበርኩባቸው ክለቦች አሳይ ስለነበረው ባህሪይ ክለቦቹን መጠየቅ ነው፡፡ አንድ ቡድን ላይ ብቻ ተወርቶ ሌሎቹ ጋር ከሌለ ማጣራት የናንተ ፈንታ ይሆናል፡፡ ወልዲያ 2 አመት ስጫወኮ አንድ ቀን ክለብ ውስጥ ልዝናና ገብቼ አላውቅም… የዳንኤል ቦታ ተብሎ ከካምፕ አጠገብ የማይጠፋ ድንጋይ ነበር /ሳቅ/ አንድ ቀን መዝናኛ ክለብ ውስጥ ገብቼ አላውቅም ለባህርዳር ከተማ ተጫውቻለው….እመቤቴን በባህር ዳር አንድም ክለብ አላውቅም… በወሬ የተባዛ ስለሆነ መታረም አለበት፡፡ የወጣ ባህሪይ የለኝም እንደማንኛውም ሰው በአል ሲኖር ቀመስ ላደርግ እችላለው እንጂ ሌላ ባህሪይ የለኝም ይቺን አመት በመቐለ ከተማ ስቆይ ስላለኝ ባህሪይ ህዝቡ የሚፈርደው ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡- በ2ዐ12 ዘረኝነቱና የፖለቲካ ሰዎች ጣልቃ ገብነት አያሰጋም?
ዳንኤል፡- ይሄማ ዋና አስፈሪ ነገር ነው…. በ24 ክለቦች መሀል ይደረግ የሚለው ቢፀና ህዝቦችን ስለሚያራራቅ ጥሩ አልነበረም፡፡ አሁን ግን በ16 ክለቦች መሀል መደረጉ፣ አሪፍ አሪፍ ሰዎች ውድድሩን እንዲመሩ መመረጣቸው….. የፍትህ አካላቱ በገለልተኝነት እንዲሰሩ ይደረጋል መባሉ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ስታዲየም በሚገባ ሰው 1ዐዐ ሺህ ብር ከሚሰበሰብ የደጋፊ ባህሪይ ታይቶ በትንሽ ደጋፊ ወደ ሠላም ቢመጣ ደስ ይለኛል በኳስ ሰበብ የሚጠፋው ነገር መቆም አለበት….. 1ዐዐ ሺህ ብር አግኝተን የሰው ነፍስ ከሚጠፋ 1ዐ ሺህ ብር አግኝተን ሠላም ቢመጣ ደስ ይለኛል ይሄ ነው መፍትሔ ኳሱ ብዙ ህዝብ ገብቶበትም አላደገም እስኪ ህዝቡ አንሶ ደግሞ ይታይ፡፡ በኛ በኢትዮጵያዊን ጭንቅላት ላይ ገና አልተሰራም ከታች ጀምረን አላደግንምና ብዙ ደጋፊ ፊት ስንጫወት ደግሞ ኳሱ ጠፍቶብን እግር ኳሱን የገደልነው ይመስለኛል፡፡ የደጋፊ ባህሪይ እየታየ ለ 9 ሰዓት ጨዋታ 4 ሰዓት ላይ ተከፍቶ የማይገባው ሰው እየተመለሰ ሠላም ቢፈጠር ደስ ይለኛል፡፡ አሁን ዩኒቨርሲቲ ሰው ሲገባ ማስያዣ ከቤት ይፃፋል ተብሏል የዚያ ተማሪ ሁሉ የሚፃፈው፣ ለሠላም አይደል? ኳሱም ለሠላም እስከሆነ ድረስ እየተለየ ቢገባ ደስ ይለኛል ከደጋፊ መሃል እኔን ሳሚ ባሪያው የሚለኝኮ አለ ያን ያህልም ስለ ኳስ የማያውቅ ደጋፊ ነው የሚገባው…. ዳንኤል ሆኜ ሳሚ ባሪያ ይለኛል እመቤቴን /ሳቅ/ እያልኩ ያለሁት የተሻለ ቁጥጥር መደረግ አለበት ባይ ነኝ፡፡ የስታዲየምን ሠላም የሚያረጋጉት የፖለቲካ ሰዎች ሳይሆኑ ተጨዋቹ ደጋፊውና የደጋፊው ማህበር ይመስሉኛል፡፡ ሁለቱ ክለቦች መቀለና ቡና ሲጫወቱ ተረበሸ እንዴ? ትንሽ ሰውኮ ነው የገባው… ሰው ማብዛት ትርጉም የለውም፡፡
ሀትሪክ፡- …5ዐ ሺ ብር የወር ደመወዝ ለዳንኤል ደምሴ አቋም ይመጥናል…?
ዳንኤል፡- …/ሳቅ/…ብሩ ቀንሶ ኳሱ ያድጋል…?…ካደገኮ ይቀጥል…፤…የቅነሳው ደጋፊ እሆናለው…5ዐ ሺህ ብሩ ካሳደገው ይታያል…።…5ዐ ሺህ ብር ደመወዝ መሆኑ ብሔራዊ ቡድኑ ጎል እንዲያገባ ከረዳው ይቀጥል ከዚያም በታች አንሶ ለምን የአለም ዋንጫ አንገባም? ይህን ነው የምፈልገው… እስቲ ስለ እውነት እንናገር የሆነች መኪና ገዝቼ ማንም ሳይሰድበኝ ራይድ ገብቼ 18 ሺ ብር ባገኝ ተጠቃሚ ነኝኮ… የሚሰድበኝ የለም እዚህኮ ትርፋችን ፓስታ ነው የእስካሁኑ ፓስታ ቢቀጣጠልኮ አሜሪካ እንድርስ ነበር /ሳቅ በሳቅ/ ምንም አያጓጓም… ሁሉም አንድ አይነት ደመወዝ ከተከፈለው ትርፉ ምን ሊሆን? እስቲ የኳሱ እድገት ከመጣ እንየው? የዋሊያዎቹ መዳከም ከእንደዚህ አይነት እይታ የተነሣ ሊሆን ይችላል ብለህ አስበህ ታውቃለህ? የሆነ ጊዜኮ በሺህ ብርም ተጫውተናል አሁን ብዙ ነገር ስለለመድን በብዙ ፕሮግራሞች ላይ ስለምናውል እንጂ ኳሱ ቢያድግ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል ሁሉም ይታይ ባይ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …የተጨዋቾች ማህበር አባል ነህ…?
ዳንኤል፡- አዎ የማህበሩ አባል ነኝ…በተለይ ከኤፍሬም ወንድወሰን ጋር ብዙ እንማከራለን…፤…በቡና ጉዳይ ላይ ብዙ ተመካክረናል፡፡ በቡና አመራሮች በመበሳጨቴ ተከራክሬ የአመት ደመወዜን እቀበላለው እያልኩ አቋሜን ያስቀየረኝ ኤፍሬም ነው… “ዳኒ ለምን ትጓተታለህ…?…መጫወት እየቻልክ እንዴት ውዝግብ ውስጥ ትገባለህ…?…ኳስ አቁመህ እንደገና ስትጀምር ይከብድሃል…”ብሎ መክሮና አበርታቶ ወደ ዝውውሩ በሠላም እንድገባ አድርጎኛል…፤…ማህበሩ በጣም ጠቅሞኛልና ማመስገን እፈልጋለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- …ስለ ብሔራዊ ቡድኑ የምትለው ነገር አለ…?
ዳንኤል፡- …አገሬን እወዳለሁ…ማገልገልም እፈልጋለሁ…፤…ምርጫ ላይ ለሁሉም ግልጽና እውነት ላይ ያተኮረ ተንኮል የሌለበት የምርጫ ሂደት ቢኖር ደስ ይለኛል…።…ማንኛውም ተጨዋች ሀገሩን የማገልገል ህልም አለው…የእኔም ህልሜ ይሄ ነው…፤…በቀጣይ ምርጫ ሲካሄድ በግልፀኝነት ላይ የተመሰረተ ቢሆን ደስ ይለኛል…።…አንዳንድ አካሄዶች አይመቹም…እንደ ግስላ ውጭ ሄጄ ምነው ቃለ-ምልልስ ባደረኩና ሁሉን ጉድ በዘረዘርኩ ብዬ ተመኘሁ…እኔ ባልጫወትም ኳሳችን አድጎ ሜዳ ገብቼ ብመለከት ደስ ይለኛል፡፡ ሀገሬን እወዳለሁ ይሄን ሊረዱ ይገባል፤ ብሔራዊ ቡድን ርስት አይደለም ተብሏል፤በአቋማችን የምንመዘንበት ተመዝነን ደግሞ የምንጠራበት ጊዜ ማየት ናፍቆኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …አሰልጣኙ የመምረጥ…በራሱ እይታ ተጨዋቹ ጥሩ ቢሆንም አለመፈለግ መብቱ አይደለም፡፡ ?
ዳንኤል፡- …ይሄኮ የመብት ጉዳይ አይደለም ስለሀገር አይደል የምናወራው… እንደ ብሔራዊ ቡድን እኔን መርጦ ለራሱ ስትራቴጂ እንድመች ማድረግኮ የአሰልጣኙ ስራ ነው…በክለብ ደረጃ የተሻለ ከሆንኩ ሀገሬን እንዳላገለግል ለምን ይደረጋል? እኔኮ ሀገሬን ማገልገል ግዴታዬ ነው… እንዲህ ነው የሚሰማኝ…፡፡
ሀትሪክ፡- …ባለፉት 5 አመታት ለ4 ክለቦች ተጫውተሃልና በቦታህ ምርጡ ማነው?
ዳንኤል፡- ለዚህ ሁለቴ ማሰብ አይጠበቅብኝም፡፡ በቦታዬ በሀገር ደረጃ ምርጡ ጋቶች ፓኖም ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ከውጪ የማን ደጋፊ ነህ?
ዳንኤል፡- የማን.ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ….ዘንድሮማ ያው እየተቃጠልኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ከአርሰናል ደጋፊ ይልቅ እናንተ የማማ ወተት ወዳጅ ሆናችኋል እየተባለ ነው…ዳኒ ማማ ወተት አበዛህ እንዴ…?
ዳንኤል፡- …ብቻችንንማ አይደለንም ከአርሴናል ደጋፊዎች ጋር አዎ እየጠጣን ነው /ሳቅ በሳቅ/ ከአርሰናል ደጋፊ ጋር በጋራ እየጠጣን ከመሆኑ አንፃር የቀረን እንደ ሙሽራዎች ተጠላልፎ መጠጣት ብቻ ነው /ሳቅ በሳቅ/
ሀትሪክ፡- …አይችልም ቡድኑን አይመጥንም የምትለው ተጨዋች አለ…?
ዳንኤል፡- …በኛ ስታንዳርድ መፍረድ እከሌ አይችልም ማለትኮ ይከብዳል… እንደ ኳስ ተመልካች ካየን ግን ቡድኑ ልክ አይደለም… ከወቅታዊው አቋሙ አንጻር ማን.ዩናይትድን የሚመሩት የኛ ሀገር ኮሚቴዎች አይመስሉህም?/ሳቅ በሳቅ/ በጣም ትልቅ ክፍተት አለበት ተቀይረው የሚገቡትን እይና የነሊቨርፑል..ማን.ሲቲ ተጠባባቂዎችን ስታይ ልዩነቱ ይሰፋብሃል…ተፅዕኖ ፈጣሪ ጠፋኮ…አንደር ሄሬራ… ሮሜሉ ሉካኩ ለምን ተሸጡ እላለው? የመሃልና የአጥቂ ክፍል መሀል ርቀቱኮ ሰፍቷል እንዴት ይገናኙ…?…ጎል የማይሞከረውም ለዚህኮ ነው…፤…መቼ ነው ራሽፎርድ የጎል እድል የተፈጠረለት…የለም፡፡ ተጨዋቾቹ ደግሞ አላገዙትም ተመላላሾቹም ማጥቃት ላይ ደከም ብለዋል፡፡ ከክሪስታል ፓላስ የተገዛው ሁዋን ቢሳካ ራሱ ሲከላከል እንጂ ሲያጠቃ ብዙም የለበትም…ክሮሶቹም ራሱ ልክ አይደሉም… በቃ…የክለቡ ስብስብ ልክ አይደለም…ማን ዩናይትድ የለበትም…እንደ ኤሲ ሚላን እንዳይጠፋ ስጋት አለኝ…፡፡
ሀትሪክ፡- …ጠ/ሚ ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ የሠላም የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው ስትሰማ ምን አልክ…?
ዳንኤል፡- …እንደ ኢትዮጵያዊ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል…ነገር ግን በኛ በተጨዋቾች ላይ ጨከን ማለታቸው ከፍቶኛል…በክፍያችን ላይ ችግር የተከሰተውና የተቀነሰብን ጠ/ሚኒስትሩ በኳሱ ዙሪያ ከተናገሩ በኋላ በመሆኑ ቅር ብሎናል /ሳቅ/ አሁንም ካገኙት የሽልማት ብር ላይ ቀመስ ሊያደርጉን ይገባል /ሳቅ/ አስኮርፈውናልኮ፡፡
ሀትሪክ፡- …ጨረስኩ…ለኢትዮጵያ ቡናና ለመቐለ 70 አንደርታ ደጋፊዎች የምትለው ነገር አለ…?
ዳንኤል፡- …ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ስመኝ ኖሬያለው…ምኞቴ ተሳክቶ ህልሜን መኖር በመቻሌ ደስተኛ ነበርኩ ግን ሊቀጥል ባለመቻሉ አዝናለው…ጥሩ ሆኜም ሳልሆንም አብራችሁኝ ለነበራችሁ ወደ ጥሩነት እንድመጣ ላደረጋችሁኝ ደጋፊዎች በሙሉ እግዚአብሔር ይስጥልኝ በጣም ነው የማመሰግነው ዳንኤል ራሱን እንዲያገኝ ላደረጋችሁት ደጋፊዎች በሙሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ እላለው፡፡ የልጅነት ህልሜን ስላሳካሁም ደስ ብሎኛል የሠላም አመት ያድርግላችሁ እላለው፡፡ ለመቐለ 7ዐ አንደርታ ደጋፊዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና ማሊያ ያያችሁትን ዳንኤል ከዚያ በተሻለ አቋም ተገኝቼ በ2ዐ12 በድጋሚ የሊጉን ዋንጫ እንድናነሳ እግዚአብሔር ይርዳን እላለው፡፡ ሀትሪክ ለሰጠችኝ እድል ከልብ አመሰግናለሁ እመብርሃን አመቱን የሠላም አመት ታድርግልን፡፡