ኮትዲቫራዊው የመሃል አጥቂ አህመድ ቢን ዋታራ እና ባህርዳር ከነማ በስምምነት ሊለያዩ መሆኑ ታውቋል፡፡
የሊጉ አዲስ አዳጊው ባህርዳር ከነማ በኘሪምየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን በማሰብ በክረምቱ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ካስፈረሟቸው የውጭ ሀገር ተጨዋቾች መሀከል ከመሀል አጥቂው ኮትዲቫራዊው አህመድ ቢን ዋታራ ጋር በስምምነት ለመለያየት ከጫፍ መድረሳቸውን ሀትሪክ ስፖርት አረጋግጣለች፡፡
አጥቂው አህመድ ቢን ዋታራ የሚጠበቅበትን ያህል ለክለቡ ግልጋሎት ባለመስጠቱ ከክለቡ ጋር የሚያቆየው ቀሪ ኮንትራት ውል ቢኖርም ክለቡ የአንድ ወር ደመወዝ እንክፈልህና በስምምነት እንለያይ የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ተጨዋቹ በበኩሉ የአምስት ወር ደመወዝ ክፈሉኝና በስምምነት እንለያይ የሚል አማራጭ ሀሳብ ለክለቡ የበላይ ሀላፊዎች ጥያቄ አቅርቧል፡፡
- ማሰታውቂያ -
በአንድ አመት ኮንትራት ውል በክረምቱ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ባህርዳር ከነማን የተቀላቀለው ዋቴንጋ ብዙም የመሰለፍ ዕድል ሳያገኝ ለመጨረሻ ጊዜ ተሰልፎ የተጫዎተው የጣና ሞገዶቹ ከሜዳቸው ውጭ ሀዋሳ ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ነበር፡