THE BIG INTERVIEW WITH ENDALE DEBALEKE
“ታገሱን … ለኢትዮጲያ ቡና ብቻ ሳይሆን ለሃገር የሚጠቅም አጨዋወት ይዘን መጥተናል”
- ማሰታውቂያ -
“በኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ የደርቢ ፍልሚያ ላይ መጫወቴ ለኔ ክብሬ ነው”
“ኢትዮጲያ ቡና ህዝባዊ ከመሆኑ አንፃር ማሊያውን ማድረግ የማይፈልግ ተጨዋች አለ ብዬ አላምንም”
እንዳለ ደባልቄ/ኢትዮጲያ ቡና/
በዮሴፍ ከፈለኝ
ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቄራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ በአለም ላይ ያለ ወይም የኢትዮጵያ ኮከብ ተጨዋች ሳይሆን ተምሳሌቴ የኛ ቤት ጎረቤት የነበረው ጉልላት ነው፡፡ በክለብ ደረጃ ሳይጫወት ቢቀርም በሰፈራችን ምርጥ አጥቂ ስለነበር ቦርሳውን ይዤ እከተለውም ነበር ሲል ጅማሮውን ያወጋል፡፡ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ስር የኢትዮጲያ ቡና የአጥቂውን መስመር እየመራ ያለው እንግዳችን እንዳለ ደባልቄ የተጨዋችነት ህይወቱ የጀመረው በደደቢት ሲ ቡድን ውስጥ ነው፡፡ ወደ ዋናው ቡድን አድጎ 2005 የፕሪሚየር ሊጉ ባለድል ሲሆኑ የቡድኑ አባል ነበር፡፡ ከኢትዮጲያ ቡና በፊት ለደደቢት፣ ለሃዲያ ሆሳዕና ፣ ለጅማ አባጂፋር ፣ ለባህርዳር ከተማ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ እንዳለ ስለ አዲሱ የኢትዮጲያ ቡና አጨዋወት፣ ስለካሳዬ አራጌና የቡና ደጋፊዎች፣ ስለ 2005 የደደቢት ድሉ፣ ለዋሊያዎቹ ለመሰለፍ ስላለው ህልም፣ ስለ ስፖርታዊ ጨዋታ፣ አዲሱ የቡና የጨዋታ ፍልስፍና ትዕግስት እንደሚያስፈልገው፣ ስለ ቡና ተፋላሚዎችና ሌሎች ጉዳዮች ከዮሴፍ ከፈለኝ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ሀትሪክ፡- ከመቐለ 70 እንደ ርታ ጋር 1ለ1 ተለያያችሁ ጨዋ ታውን እንዴት አገኘ ኸው?
እንዳለ፡- ጥሩ ነበር…አሁን የግብ አካውንቴን ከፍቼያለሁ፤ የግብ አካውንቴ ከተከፈተ በኋላ ወደፊት በርካታ ግቦች ይመጣሉ፡፡ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ነበረው፤የመጀመሪያው 35 ደቂቃ እኛ በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃ ደግም እነሱ የተሻሉ ነበሩ። እኛ ግብ የሚሆኑ እድሎችን አሁንም አምክነናል ፤ጥሩ መግባባቶች እየታዩብን በመሆኑ በቀጣይ የሚስተካከል ይሆናል፤እንደ ቡድን ደስተኞች ነን፡፡ ዳኝነቱም የተሻለ ነበር፤ምንም ውጤት ለዋጭ የሆነ ስህተት አላየሁም፡፡
ሀትሪክ፡- …የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎችን የድጋፍ ሁኔታስ እንዴት አገኘኸው?
እንዳለ፡- በጣም የተደሰትኩት በደጋፊዎቹ የስፖርታዊ ጨዋነት አከባበር ነው፤የመቐለ ደጋፊዎች ፍፁም ኢትዮጵያዊነት በተላበሰ መልኩ ለክለባችን ደጋፊዎች ያደረጉት አቀባበል ማርኮኛል፡፡ የእራት ግብዣ ሁሉ አድርገውልናል፤ በቃ ታሪክ ተቀይሯል በሁለቱም ተደስቻለሁ፤የሚያምርብን እንዲህ ስንሆን ነው፡፡
ሀትሪክ፡-2005 ከደደቢት ጋር የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አንስተሃልና እስቲ ስለ ቡድኑ የምታስታውሰውን ንገረኝ?
እንዳለ፡- በወቅቱ የነበረው ስብስብ የሀገሪቱ ምርጥ የሚባል ነው፡፡ ሁሉንም ማለት በሚያስችል መልኩ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ነበሩ፡፡ በጣም ልምድና አቅም ያላቸው ተጨዋቾች የተሰባሰቡበት ቡድን ነበር፡፡ እኔ ከ ሲ በቀጥታ ነው ወደ ዋናው ቡድን ያደኩት….. በአጥቂ መስመር እነ ጌታነህ ከበደ፣ ከኋላ እነ ሲሳይ ባንጫ፣ መሃል ላይ እነ አዲስ ህንፃና ምን ያህል ተሾመ የመሰሉ ተጨዋቾች ነበሩና ከነርሱ ምርጥ ልምድ አግኝቻለው…..በዚያ ላይ ጥቂት ጨዋታ የመጫወት እድል ገጥሞኛል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ምርጥ ጊዜ የሚባለው ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፍንበት ወቅት እንደመሆኑ የቡድኑ ስብስብ አስተዋጽዖ ልዩ ስለነበር ጊዜው ጥሩ ትውስታ ፈጥሮልኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ደደቢት መውረዱስ ምን ስሜት ፈጠረብህ?
እንዳለ፡- በጣም ቅር ያሰኛል፡፡ በኳስ ያደኩበት ራሴን ያወኩበት ቡድን እንደመሆኑ ያለበት ደረጃ አሳዝኖኛል….እስከ አምና ድረስ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደነበር አይረሳም አሁን ወደ ከፍተኛ ሊግ ቢወርድም ተመልሶ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለው…. በፊት የመጣውም ከስር ስለነበር ያንን ድጋሚ ከስተውት በፕሪሚየር ሊጉ ዳግም እናያቸዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- በደደቢትና ጂማ አባጂፋር ተጨዋችነት ሁለት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ አንስተሃል…..የቱ ነው ያንተ ትልቁ ደስታ?
እንዳለ፡- በሁለቱም ድሌ ደስተኛ ነኝ አወዳድር ካልከኝ ግን ተሰልፌ በደምብ የተጫወትኩበት የበኩሌን አስተዋጽኦ ያደረኩት በጂማ አባጂፋር ማሊያ በመሆኑ የ2010 ድል ይበልጥብኛል….ነገር ግን በሀዲያ ሆሳዕና ማሊያ የቆየሁባቸው 2 አመታቶችም የማይረሱ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡-ቄራ አካባቢ ተጨዋቾችና አርቲስቶች በዙኮ?
እንዳለ፡- ከበፊት ጀምሮ አንዱ በአንዱ እየተሳበ የኳስ ተጨዋችና የአርቲስቶች መፍለቂያ ሰፈር ሆኗል፡፡ በአካባቢያችን እግር ኳስ ተጨዋቾችን የሚበዙ ይመስለኛል በተለያዩ ሊጎች የሚጫወቱ ተጨዋቾች በብዛት ፈርተውበታል፡፡
ሀትሪክ፡- ሰውነትህ የወፈረ ይመስላል….. ኪሎ ጨመርክ እንዴ?
እንዳለ፡- ኧረ በፍፁም……በፊት ከነበረው ከስቼ ወደ 6 ኪሎ ቀንሻለው፡፡ ስወፍር ይታወቀኛል አሁን በደንብ እየሮጥኩ እየንቀሳቀስኩ እገኛለው፡፡ በቀጣይም ጥሩ ሰርቼ የተሻለ አቋም ለመያዝ ኪሎዬን መጠበቅ እንዳለብኝ ተረድቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና የገጠመህ እንግዳ ነገር አለ?
እንዳለ፡- እግር ኳስን ከዜሮ መጀመር እንዳለብኝ ተረድቻለው፡፡ ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል፡፡ በፊት ኳስ በረጅም ይጣላል የግል አቅሜን ተጠቅሜ ለጎል እሞክራለው፡፡ ሁሉም ቦታ ተመሳሳይ አካሄድ ነበር….. አሁን ግን እንደ ቡድን ነው የምንንቀሳቀሰው እንደ ቡድን ነው የምንሰራው….ያም ሆኖ ግን የራስ ክህሎት ይጠይቃል ኳስ ስንቀባበልም ሆነ ለጓደኞቻችን ስንሰጥ ቡድኑን ባማከለ መልኩ ነው ይሄን አካሄድ እስክላመድ ከብዶኝ ነበር አሁን ግን በጣም ቀሎኛል፡፡ ያ ነው አዲስ የሆነብኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በ2005 ከነበረበው የደደቢት ቡድንና የአሁኑ የኢትዮጵያ ቡና መሀል ጫና ያለው በየትኛው ነው?
እንዳለ፡- የዘንድሮው የኢትዮጲያ ቡና ኃላፊነቴ ከባድ የሚባልና ጫናም ያለው ነው፡፡ በ2005 በደደቢት ተሰላፊነቴ ምንም ጫና የለብኝም ከሲ ቡድን ስላደኩ ብዙም ከኔ የሚጠበቅ ነገር አልነበረም፡፡ ገብቼ ያለኝን አቅም ማሳየት ብቻ ነበር ኃላፊነቴ…. አሁን ግን ትልቅ ኃላፊነት አለብኝ፡፡ ብዙ ደጋፊ ያለው ቡድን እንደ መሆኑ የደጋፊውን ስሜት ማዳመጥና ለፍላጎቱ ምላሽ መስጠት የግድ ይላልና በቡና ማሊያ ከባድ ኃላፊነት አለብኝ፡፡ ደደቢት በወቅቱ ደጋፊዎች ቢኖሩትም ከቡና ደጋፊ ጋር አይገናኝም፡፡
ሀትሪክ፡-የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የጨዋታ ፍልስፍና ለዋንጫ ያበቃናል ብለህ ታምናለህ?
እንዳለ፡- እንደ አረዳዳችን ነው…. ተጨዋቾቹ ሳይቀር ጅማሮውን አክብደነው ነበር በወሬ ብቻ ነበር የምንሰማው…. አሁን ግን ቀላል ሆኖልናል አጨዋወቱ ለዋንጫ ያደርሳል ነገር ግን እኛ ተጨዋቾቹ ነን ለውጤት ማብቃት የሚጠበቅብን….. ካሳዬ የሚለንን ሰምተን የምንተገብረው ከሆነ ከዋንጫ በላይ በሀገር ደረጃ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብዬ አምናለው፡፡
ሀትሪክ፡- ውጤት መጥፋቱ በ2 ጨዋታ ያላችሁ ነጥብ 1 ብቻ መሆኑ ቅር አያሰኝም? /ቃለ ምልልሱ የተሰራው ባለፈው አርብ ነው/
እንዳለ፡- ውጤት መምጣቱ አይቀርም አብዛኛዎቻችን የምናስበው እንደድሮው ነው 3 ነጥብ ለማግኘት ሲባል በማይጠቅም አጨዋወት እንድንጫወት ነው የሚፈለገው…. ይሄ አብዛኞቹ ክለቦች የሚያደርጉት ነው፡፡ በፊት 3 ነጥብ ለማግኘት የምናደርገው አካሄድ አለ፡፡ 1 ጎል አስቆጥረን 90 ደቂቃ መዝጋት አሁን በኢትዮጲያ ቡና አይታሰብም፡፡ መሰረት ያለው ለውጥ የሚያመጣ ነገር ለማድረግ ጥረት ላይ ነን፡፡ በፊትኮ ቡድኑን ካየህ ወደ ጎልም አንደርስም ነበር ያንን ለመቅረፍ ብዙ ስራዎችን ሠርተን አሁን ጎል ጋር መድረስ ችለናል አሁን ደግሞ ግብ ማስቆጠር ነው የከበደን….. ያንን በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ቀርፈን ማራኪ ጨዋታ ከውጤት ጋር እናመጣለን ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከጅማ አባጅፋር ጋር የነበረው ጨዋታ 0ለ0 ተጠናቆ ስትወጡ ተበሳጭተህ ነበር….. የተፈጠረ ችግር ነበር?
እንዳለ፡- በእርግጥ የተናደድ ኩት ኳስ ስላመከንኩ አይደለም መሳትና ማስቆጠር በመላው አለምም የተለመደኮ ነው ከጨዋታው በፊት አሰልጣኛችን ከመጀመሪያው ጨዋታ በተሻለ የግብ እድሎች እንደምንፈጥር ነግሮን ነበር የገባነው የግብ እድሎችን እንደማገኝም ርግጠኛ ነበርኩ……. የተናደድኩት እድሎችን አግኝተን አለመጠቀማችን ነው……. የተሻለ ነገር አለመስራቴም አበሳጨኝ፡፡ ግብ ለመሳቱማ አለም ላይ ያሉ ታላላቅ አጥቂዎችም ይስታሉ፡፡ እየነገረኝ ከበፊቱ በተሻለ ጎል ላይ እንደርሳለን አጋጣሚው መጠቀም አለብን እያለ ተግባራዊ አለማድረጌ ግን ስሜታዊ አድርጎኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ችግሩ ግብ ለማግባት መጓጓታ ችሁ አይመስልህም?
እንዳለ፡- አዎ! ሁላችንም ጓጉተናል፡፡ የዝግጅት ግጥሚያዎች ላይ የገጠሙንን ቡድኖች ላይ ከ3 በላይ እያገባን ነው ያሸነፍነው፡፡ ሲቲ ካፑ ላይና በፕሪሚየር ሊጉ ወደፊት ሄደን ግብ የማግባት ጉጉት አደረብን…..በተለይ በኔ ላይ ያለው ጉጉት ጨመረ፡፡ ቀላልና ግብ የሚሆኑ ኳሶችን እያገኘሁ መጠቀም አለመቻሌ አበሳጨኝ፡፡
ሀትሪክ፡-ደጋፊው አሁኑኑ ውጤት ይምጣ ማለቱ የቸኮለ አይመስልህም?
እንዳለ፡- ደጋፊው ይስማን አይስማን ባላውቅም በኢትዮጵያ ቡና የቲቪ ፕሮግራም ላይ ከጓደኞቼ ጋር የተናገርነው ነገር አለ፡፡ የምንጫወተው አጨዋወት ትዕግስት ይፈልጋል ትዕግስት ከሌለ ለውጥ ማምጣት ይከብዳል፡፡ ደጋፊው ከጎናችን ካልሆነ ልንረበሽ እንችላለንና ሙሉ ደጋፊው ከጎናችን እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ውጤት ከመፈለግ አንፃር እንኳን ደጋፊው ተጨዋቾቹም ሳንቀር ትዕግስት አጥተን ነበር በኋላ ላይ ነው አሰልጣኝ ካሳዬ አስረድቶን የተረጋጋነው እንጂ በጥለዛ የለመድነውን የድሮውን አካሄድ ለመተግበር ኳሱን ወደፊት ላኩ እንል ነበር…. አሁን ላይ ግን በትዕግስት እንድንጫወት አሰልጣኙ በሰጠን የቤት ሥራ መሰረት እየተጫወትን እንገኛለን፡፡ ደጋፊው አጨዋወታችን መልሱልን ሲል ነበር አሁን ያለው ሁኔታ ደግሞ ደጋፊው እንደሚፈልገው ርግጠኛ ነኝ፡፡ በቡና ደረጃ የሚፈለገውን አጨዋወት ለመመለስ በትንሹ ጭላንጭል እያሳየን ነው ብዬ እምናለው፡፡ ደጋፊው ከጎናችን ከቆመ በቡና ማራኪ አጨዋወት በውጤት የምንታጀብበት ደማቅ አመት ይሆናል ብዬ አምናለው፡፡ ቦርዱም ጊዜ ሰጥቶ ትዕግስት ማሳየቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የታየ ተስፋ እንዲጠነክር ድጋፍ ያስፈልገናል በሲቲ ካፑ በሰበታ ብንሸነፍም ያየነው ነገር አለ ደስተኛ ነን ብሎ ደጋፊው እንደወጣ አይተናል፡፡ ይሄ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል፡፡ በአጨዋወት ደረጃኮ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራትና ክለቦች ጋር መጋፊጥ አንችልም በተፈጥሮ ያለንን ነገር አዳብሮ መቀጠል እንደ ክለብ ብቻ ሣይሆን እንደ ሀገርም ለውጥ ያመጣል ብዬ አምናለው፡፡ ታገሱን…… ለኢትዮጲያ ቡና ብቻ ሳይሆን ለሃገር የሚጠቅም አጨዋወት ይዘን መጥተናል
ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን እንዴት አገኘኸው?
እንዳለ፡- ያለምንም ጥርጥር እርሱ አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆን አባትም ነው፡፡ በፊት በነበሩት ሌሎች አሰልጣኞች ጊዜ ግብ ስቼ ስወጣ ጫና ይበረታብኝ ከደጋፊው የሚገጥመኝን ተቃውሞ መቋቋም ይከብደኝ ነበር… አሁን ግን ካሳዬ ነፃነቴን ሰጥቶኛል፡፡
የሚፈጠር ነገር ነው ነገ ይስተካከላል ብሎ ያየብንን ጥሩ ጎን ነግሮ ነው እያበረታን ያለው…. ይሄ የአሪፍ አባት መገለጫ ነው….. ይህን አድርጉ ብያችሁ አድርጋችኋል አሪፍ ነው ይቺን ደግሞ በቤት ስራ እንወጣታለን ብሎ እያበረታን ነው በዚህም ደስተኛ ነን፡፡ ለኔ አባቴ ነው….. እስከዛሬ ያላወኩትን አዲስ ነገር እያሳየኝ ነው ያለሁት፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ለመፈረምህ ዋነኛ ምክንያት ምንድነው?
እንዳለ፡- በፊትም ተናግሬያለው…. 2003 ቡና ሻምፒዮን ሲሆን ሚስማር ተራ ገብቼ ከደጋፊው ጋር ጨፍሬያለው የቡና ደጋፊም ነኝ፡፡ ከደደቢት ሲ ብጀምርም ቡናን ደግፌ ኖሬያለው ቡና ውስጤ ነው /ሳቅ/ አሁን የምወደውን ክለብ ማገልገል በመቻሌ ደስተኛ ነኝ፡፡ እንደ ተጨዋችም ሆነ እንደ ደጋፊ ቡና ዋንጫ ቢበላ ከኔ በላይ ደስተኛ አይኖርም ባይ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ያንተ ምርጡ አጥቂና ምርጡ አሰልጣኝ ማነው?
እንዳለ፡- ምርጡ አጥቂ ለኔ ጌታነህ ከበደ ነው…. ከሲ ካደኩበት ጊዜ ጀምሮ እያየሁ ያደኩት እርሱን ነው…. ወደ ክልል ስንወጣ ከርሱ ጋር ሁለት ቀን አብሬው መኝታ የመጋራት እድል አጋጥሞኝ የመከረኝን ምክር አልረሳም….. ለኔ ምርጡ አጥቂ እርሱ ነው፡፡ ምርጡ አሰልጣኝ ላልከኝ ለኔ ከሰፈር ጀምሮ የወሰደኝ ኤፍሬም ደምሴ (ቤቢ) ነው፡፡ ወደ ዋናው ቡድን ያሳደገኝ እርሱ ነው፡፡ ለእስከዛሬው መሰረት የሆነኝ ብዙ ነገር ያሳወቀኝ አሰልጣኜ እርሱ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-የደመወዝ ክፍያ ስኬል ለሁሉም ተጨዋቾች እኩል መሆኑ ለእድገቱ ተገቢ ውሳኔ ይመስልሃል?
እንዳለ፡- አይመስለኝም….. ሰው በስራው ልክ ሊከፈለው ይገባል ብዬ አምናለው፡፡ የኳሳችን ደረጃ ይታወቃል እድገቱ በመጣ ቁጥር ክፍያው ማደግ አለበት ብዬ አምናለው፡፡ በአንዴ እንዲህ አይነት ውሳኔ ላይ መገባቱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በቀጣይ መስተካከል አለበት….. አለበለዚያ ህጉ ለኳሱ እድገት አይበጅም፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና ዋነኛ ተፎካካሪ ማን ይመስልሃል?
እንዳለ፡- እንደ ደርቢም ሆነ እንደ ዋና የዋንጫ ተፎካካሪ የምጠራው ቅዱስ ጊዮርጊስን ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ድባቡ ደስ የሚለው ሁለታችን ስንጫወት ነው፡፡ በጣም ስሜታዊ የሚያደርግ ደርቢ ነው በሲቲ ካፕ እድሉን አግኝቼ ተጫውቻለው በኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ የደርቢ ፍልሚያ ላይ መጫወቴ ለኔ ክብሬ ነው በጣም ተደስቻለው ነገር ግን በሊግ ደረጃ ካየነው አብዛኞቹ ክለቦች የኛ ተፎካካሪ ናቸው፡፡ ሁሉም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚጫወቱ ከሆነ የተለየ አቋም ይዘው ይመጣሉ ይሄ እውነት ነው ኢትዮጲያ ቡና ህዝባዊ ከመሆኑ አንፃር ማሊያውን መልበስ የማይፈልግ ተጨዋች አለ ብዬ አላምንም፡፡ ብዙዎቹ ክለቦች ከኛ ጋር ሲጫወቱ የተለየ አቋም ይዘው መምጣታቸው ግን ይገርመኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ለብሔራዊ ቡድን የመጫወት ህልምህ አለህ?
እንዳለ፡- አዎ….የመጨረሻ ግቤ የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን ማሊያ ማድረግ ነው፤ 2004 ላይ አሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ በያዘው ከ17 አመት በታች ቡድን ውስጥ ተካትቼ ነበር በፓስፖርት ችግር ነበር ወደቱኒዚያ ያልሄድኩት፡፡ የመጨረሻ ህልሜ አገሬ አሁን ካለችበት የተወሰነ ደረጃ ከፍ እንድትል ለማድረግ እመኛለው ሀገሬን ለመጥቀም የምችለው ባለችኝ በትንሿ አቅሜ ነው… ያለኝን አቅም አሻሽዬ ሀገሬን መጥቀም እፈልጋለሁ…. አጋጣሚዎች ከተገኙ በአፍሪካም ይሁን በአውሮፓ ደረጃ የመጫወት ህልም አለኝ….. ለአሁኑ ግን ብቃቴን አሻሽዬ ከቡና ደጋፊ ጋር በመሆን ቡድናችንን ከፍ ማድረግ እፈልጋለሁ ይህን ለማድረግም ተዘጋጅቻለው፡፡
ሀትሪክ፡- በአውሮፓ ሊጎች ከሚገኙ ክለቦች የማን ደጋፊ ነህ?
እንዳለ፡- የግለሰብ አድናቂ አትበለኝ እንጂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ማን.ዩናይትድ እያለ የዩናይትድ ደጋፊ ነበርኩ አሁን ግን እምብዛም ነኝ፡ በግሌ የፖርቱጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አድናቂ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-ሜሲ ከሮናልዶ… ማን ልብህን ወሰደው?
እንዳለ፡- ሁለቱንም የማየት እድል ስላገኘሁ ደስተኛ ነኝ፡፡ የልቤ ንጉስ በኳሱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው…ሮናልዶ ለኔ መምህሬ ነው /ሳቅ/ እርሱ የሚያደርገውን የማድረግ ፍላጎት አለኝ ጥረትም እያደረኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-የዘንድሮ ባሎን ደኦር… ለሜሲ መሰጠቱ ተገቢ ነው ትላለህ?
እንዳለ፡- አዎ! ሜሲ ይገባዋል፡፡ አንዳን ዶች የሊቨርፑሉ ቫንዳክ ይገባዋል ቢሉም የሜሲ ምርጫ ተገቢ ነው ብዬ አምናለው፡፡ ሜሲ ባለው አቋም የሚወዳደረው ከሮናልዶ ጋር እስካልሆነ ድረስ ሁሌም ማሸነፍ ያለበት እርሱ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-የቤተሰቦህን ድጋፍ አግኝተሃል?
እንዳለ፡- አባቴ በልጅነቴ ነው ያረፈው፡፡ ነገር ግን በህይወት ሳለ ባለው አቅም ይደግፈኝ ትጥቅ ያመጣልኝ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ኃላፊነቱ እናቴ ላይ ወደቀ…. እናቴ ደግሞ እንድማር በነበራት ፍላጎት የኔ ልብ ወደ ኳሱ ማዘወተሩ አናዷት ተጋጭተን ነበር መጨረሻ ላይ ደደቢት ሲ ገብቼ ስታየኝ ተወት እያደረገች መጣች….. በነገራችን ላይ የመጀመሪያ ደሞዜ 250 ብር ነበር ለእናቴም በተወሰነ መልኩ ማገዝ ስጀምር እየተቀበለችው መጣች፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን ጥሩ ደመወዝተኛ መሆንህን ሲያዩና ስትደግፋቸው አልተደሰቱም?
እንዳለ፡- እናቴ ከደመወዙ በላይ ልጄ አስጣራኝ ብላ መደሰቷ ይበልጣል፡፡ ሚዲያ ላይ ስታየኝ ስለኔ ሲወራ የእንዳለ እናት ብለው ሲጠሯት ትደሰታለች… በዚህ ደስታዋ እድለኛ ነኝ ብዬ አስባለው….. አባቴን ባገኘው ደስ ይለኝ ነበር አሁንም ቢሆን በእናቴ ተክሻለው በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የእንዳለ መዝናኛው ምንድነው?
እንዳለ፡- ቤት ውስጥ ፊልም ማየት ደስ ይለኛል ግጥም እሞክራለው፡፡ ለባለቤቴ አንድ ግጥም ገጥሜያለው፡፡ ባለ ትዳርና የ1 ልጅ አባት ነኝ፡፡ ባለቤቴ ወ/ሮ ቤተልሄም ከተማ ትባላለች ልጄ እስጢፋኖስ እንዳለ ይባላል የ4 አመት ልጅ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- እስቲ ለባለቤትህ የገጠምከውን ግጥም በልልኝ?
እንዳለ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ርዕሱ የባለቤቴ ስም ነው
እግዚአብሄር በቃሉ
ተገኝቶም ባካሉ
ባርኮ የቀደሳት
ደጋግሞ ያወደሳት
በእንጉርጉሮ ዜማ
ቤተልሄም ከተማ
አሪፍ ነው አይደል?/ሳቅ በሳቅ/
ሀትሪክ፡- ግን የት ተዋወቃችሁ….?
እንዳለ፡- ተወልዳ ያደገችው ጅማ ነው፡፡ 2004 ላይ የመላው አዲስ አበባ የክፍለ ከተሞች ሻምፒዮና ሲዘጋጅ ንፋስ ስልክን ወክዬ ከኮልፌ ጋር ለዋንጫ ደርሰን ነበር በወቅቱ ኮከብ ተጨዋችም ሆነ ኮከብ ጎል አግቢ የሆንኩት እኔ ነበርኩ፡፡ ያኔ ፎቶ አንስታኝ ፎቶውን ለመውሰድ ስሄድ የነበረው ትውውቅ አድጎ ለትዳር በቅተናል…. እርሷም ንፋስ ስልክን ወክላ በእጅ ኳስ 3ኛ ደረጃ አግኝተው ሜዳሊያ ለመቀበል ሲመጡ ነው የተዋወቅነው፡፡ ትውውቃችን እንዲህ ተጀምሮና ከፍ ወዳለ ፍቅር አድጎ ለትዳር በቅተናል፡፡
ሀትሪክ፡- ቤት ውስጥ አንድ አይነት የስፖርት ቋንቋ መነገሩ አይከብድም?
እንዳለ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ልጄም ወደዚያው ነው፡፡ ኳስ ይወዳል የማን ደጋፊ ነህ ስትለው አሁን የቡና ነኝ ይላል፡፡ ባህር ዳር እያለው የባህር ዳር ከተማ ደጋፊ ነበር /ሳቅ/
ሀትሪክ፡-የዘንድሮ የስፖርታዊ ጨዋነት ሂደትን እንዴት አገኘኸው?
እንዳለ፡- የዘንድሮው አጀማመር ከወት ሮው የተለየና ምርጥ ሆኖብኛል ምናልባት ኮሚቴው አዲስ ስለሆነ ይሁን ወይም ክለቦች በተሻለ ደረጃ ሠላም ስለፈለጉ ባላውቅም ሠላሙ ደስ ይላል፡፡ የተጨዋቾቹ ዲሲፕሊንም ይበል ያሰኛል የደጋፊውም ስነ ምግባር ማራኪ ሆኗል ከስሁል ሽረ ጋር በነበረን ጨዋታ ችግር ሳይፈጠር የአምና ልዩነት ሳይታወስ በሠላም ተቀብለው በሠላም ሸኝተውናል ጥሩ አጨዋወት ስናሳይ አጨብጭበውልናል፡፡ ውጤቱን በፀጋ ተቀብለን ስንወጣ በታላቅ ክብር ሸኝተውናል ይሄ በዚህ መቀጠል አለበት….. ለሀገር እግር ኳስ እድገት ከታሰበ ሠላሙ ወሳኝ ነው ለሁሉም ወገኖች የሠላም ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለው አሁን የተጀመረውን ሰላም ፈጣሪ ያዝልቅልን ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-የመጨረሻ ቃል….?
እንዳለ፡- እናቴን ድንግል ማርያምን አመሰግናለው…. ወላጅ እናቴን፣ ባለቤቴን፣ ለሰፈር ጓደኞቼ፣ ከጎኔ ድጋፋቸው ላልተለየኝ የቡና ደጋፊዎች ምስጋና አቀርባለው፡፡ የቡና ደጋፊዎች እያሳዩ ላለው ፍቅር ምላሽ ፈጣሪ ጤናዬን ሰጥቶኝ እነሱን ለማስደሰት ቃል እገባለው፡፡ አጨዋወቱ ለናንተ ብቻ ሣይሆን ለኛም አዲስ በመሆኑ በትዕግስት ተሞልታችሁ ከጎናችን ቁሙ እንጂ የተሻለ ውጤት ይመጣል ብዬ አምናለው፡፡