የ2018ቱ አፍሪካ ሻምፒዬንስ ሊግ የመጨረሻ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት የሚደረጉ የመልስ ጨዋታዎች በተለያዩ ከተሞች በ16 ስታዲዬሞች ዛሬ እና ነገ ተካሂደው ወደ ምድብ ድልድል የሚያልፉ ክለቦች ተለይተው የሚታወቁ ሲሆን የኮንጎው ቲፒ ማዘንቤ ፡የግብፁ አልሃሊይ፡እና የሞሮከው ዋክ ካዛብላንካ ተጋጣሚዎቻቸውን በሜዳቸው በሰፊ የጎል ልዩነት በማሸነፋቸው ከወዲሁ ወደ ምድብ ድልድሉ አላፊ ስለመሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡
በቶታል ካፍ ሻምፒዬንስ ሊግ የመጨረሻ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ፡ሀገራችን በመወከል ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ዩጋንዳ ካምፓላ ያቀናው ቅዱስ ጊዬርጊስ ከካምፓላ ሲቲ (ኬሲሲኤ) ጋር ዛሬ ከቀኑ 10፡00 በስታር ታይምስ,ሉጎጎ, ስታዲዬም የሚያደርጉት ጨዋታ ከወዲሁ የሚጠበቅ ነው፡፡
ከጨዋታው አስቀድሞ የቃላት ጦርነቶች የተከፈቱበት ይህ ጨዋታ በመገናኛ ብዙሃን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከፍተኛ ሽፋን አግኝተዋል ፡፡የቅዱስ ጊዬርጊስ አሰልጣኝ ፖርቹጋላዊ ” ቫዝ ፒንቶ “ወደ ካምፓላ ከማቅናታቸው በፊት ወደ ዩጋንዳ የምንሄደው ተጋጣሚያችን ኬሲሲኤን በማሸነፍ ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት ነው በማለት የመጨረሻ አማራጭ የሌለውን አስተያየታቸውን ሲናገሩ፡የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ዩጋንዳዊው ኦዶንካራ የሀገሩን አፈር በረገጠበት ሰዓት “ዴይሊ ሞኒተር” ከተባለው የሀገሪቱ ተነባቢ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቆይታ የትውልድ ሀገሩ ክለብ የሆነውን ኬሲሲኤ ያስጠነቀቀበትን ቃለ ምልልስ ጋዜጣው ለንባብ ይዞ መውጣቱ አነጋጋሪ ሁኗል፡፡
የባለሜዳዎቹ ኬሲሲኤ አሰልጣኝ “ማይክ ሙቴቢ” በበኩላቸው አዲስ አበባ በነበረን ጨዋታ ግብ ባናስቆጥርም አሁን ጨዋታው በሜዳችን እንደመሆኑ ምን ማድረግ እንዳለብን ስለምናውቅ ቅዱስ ጊዬርጊስን ለማሸነፍ ዝግጁ ነን፡፡ተጋጣሚያችን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ምድብ ድልድል እንገባለን ሲሉ ምላሽ የሰጡበትን አሰተያየት ተናግረዋል፡፡
የዩጋንዳው ኬሲሲኤ በአፍሪካ ሻምፒዬንስ ሊግ ወደ ምድብ ድልድል በመግባት አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ዚዘጋጁ በሌላ በኩል ተጋጣማያቸው የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዬርጊስ በተከታታይ ለ2ኛ ጊዜ ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት በሜዳቸው የሚፋለማቸው ይሆናል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ቅዱስ ጊዬርጊስ ባለፈው ዓመት በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ኮትዲዬርና ኤሲ ሊዬፓርድን በማሸነፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ምድብ ድልደሉ በመግባት ምድብ ” C ” ከማሚሎዲ ሰንዳዎንስ ፡ኤስፒራንስ ደ ቱኒስ እና ቪታ ጋር ተደልድሎ መጫዎታቸው የሚታወስ ሲሆን በዚህ ዓመት የሱዳኑን አልሰላም ዋኡ በፎርፌ በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው ቅድመ ማጣሪያ ሲያልፉ ከኬሲሲኤ ጋር በመገናኘት በሜዳቸው የመጀመሪያውን ጨዋታ ያለ ግብ የተለያዩት ፈረኞቹ ከሜዳቸው ውጭ ተጋጣሚያቸውን አሸንፈው ወደ ሚፈልጉት እና በዕቅድ ከያዙት ወደ ምድብ ድልድል የማለፍ ህልማቸው እውን እንዲሆን የዛሬውን 90 ደቂቃ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የዩጋንዳው ኬሲሲኤ በበኩሉ ባለፈው ዓመት ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት በሚያደርገው ጉዞ በሁለተኛው ዙር ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ በማሚሎ ሰንዳዎንስ 2ለ1 ተሸንፎ ከውድድሩ መሰናበታቸው የሚታወስ ሲሆን በዚህኛው ዓመት በመጀመሪያው ቅድመ ማጣሪያ የማዳጋስካሩን ስናኘስ ስፖርትን ከሜዳቸው ውጭ ባስቆጠሩት ግብ በማሸነፍ ከፈረሰኞቹ ጋር ያገናኛቸውን ውጤት ሲያስመዘግቡ ኬሲሲኤዎች የባለፈው ዓመት ታሪካቸውን ላለመድገም ዛሬ ተጋጣሚያቸውን ቅዱስ ጊዬርጊስ አሸንፈው ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመግባት በሜዳቸውና በደጋፊዎቻቸው ፊት የሚጫዎቱ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዬርጊስ 27 የልዑካን ቡድን አባላትን በመያዝ ሀሙስ ረፋዱ 4:05 ከቦሌ አየር መንገድ በቀጥታ ወደ ዩጋንዳ ኢንቴቤ አየር መንገድ ያቀኑ ሲሆን ከኢንቴቤ አየር መንገድ ከደረሱ በሇላ 40 ኪ.ሜ የሚሸፍን መንገድ ተጋጣሚያቸው ኬሲሲኤ ባዘጋጀው መኪና ጨዋታው ወደ ሚካሄድበት ስፍራ አቅንተው ማረፊያቸውን በባለ 5ቱ ኮኮብ ጎልደን ቱሊፕ ሆቴል አድርገዋል፡፡በዚህ ልዑክ የፊት መስመር አጥቂው ሳላዲን ሰኢድ ፡ኢብራሂም ፎፋና እና ሰይዴ ኬታ በጉዳት ምክንያት አብረው አልተጓዙም፡፡ፈረሰኞቹ በዚያው ቀን አመሻሹን ቀለል ያለ ልምምድ የሰሩ ሲሆን ትናንት ጧት ከቁርስ በሇላ ጨዋታውን አስመልክቶ አጠቃላይ የቡድኑ አባላት ውይይት አድርገዋል፡፡
ፈረሰኞቹ ትናንት አመሻሽ ጨዋታው በሚካሄድበት ስታር ታይምስ,ሉጎጎ, ስታዲዬም 10:00 የመጨረሻ ልምምዳቸውን የሰሩ ሲሆን ሁሉም የቡድኑ አባላት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል ቁጥራቸው 30 የሚሆኑ የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች ክለባቸውን ለመደገፍ ትናንት ምሳ ሰዓትና ምሽት 12:00 ከአዲስ አበባ ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡
ጨዋታው በዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ዛሬ ከቀኑ 10:00 በስታር ታይምስ,ሉጎጎ,ስታዲዬም የሚደረግ ሲሆን ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት ሶማሊያዊው ኮሚሽነር አሚር ሀሰን ይመሩታል።