መቐለ 70 እንደርታ ከፋሲል ከነማ ጋር ያገናኘው የ2011 የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ በጥሎ ማለፍ ሻምፒዮኖቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።በሁለቱም በኩል አዳዲስ ፈራሚዎች በታዩበት ጨዋታ ፋሲል ከነማ በሙጂብ ቃሲም የሁለተኛ አጋማሽ ግብ ታግዘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሻምፒዮኖቹ ላይ ድል መቀዳጀት ችለዋል።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያስተናገደው የመጀመርያ አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ቢታይበትም ግብ ማስተናገድ ሳይችል ቀርቷል።አፄዎቹ ከተጋጣሚያቸው መቐለ 70 እንደርታ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ቀኝ መስመር ላይ ትኩረት አድርገው ፊሊፕ ኦቮኖን የፈተኑ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።ለዚህ ማሳያ ሊሆን ሚችለው ሱራፋኤል ዳኛቸው መሀል ላይ ሁለት የመቐለ ተጨዋቾችን በመቀነስ ፍፁም ቅጣት ሳጥን ላይ በቀኝ በኩል ለነበረው ሽመክት ጉግሳ አቀብሎት የተመታ፤ ጠንካራ ኳስ በኢኳቶሪያላዊ ግብ ጠባቂ ድንቅ ብቃት ወደ ውጭ የወጣው ኳስ የእንቅስቃሴው ተጠቃሽ ሙከራ ነው።ሁለት የአጥቂ አማካኞች ሱራፋኤል ዳኛቸው ና በዛብህ መለዮ ከጋናዊው አዲስ ፈራሚ ጋብሪኤል መሀመድ ጋር በ4-3-3 አሰላለፍ መሀል ላይ ያጣመሩት ፋሲሎች መቐለ 70 እንደርታ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ችለዋል።በተለይ ሱራፋኤል ዳኛቸው፣ እና ሽመክት ጉግሳ የነበራቸው ጥምረት የአፄዎቹ የማጥቃት ሽግግር ፈጣን እንዲሆን ከፍተኛ ድርሻ ተወጥቷል።ሌላኛው ተጠቃሽ የፋሲል ሙከራ ሽመክት ጉግሳ ከመሀል ጋብርኤል የላከለትን ኳስ በመጠቀም ወደ መቐለ መርበብ ቢልከውም ፊሊፕ ኦቮኖ ሊያድንበት ችሏል።የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኖቹ መቐለ 70 እንደርታዎች ሁለቱም መስመሮች እንዲሁም በፊት አጥቂነት በተሰለፈው አማኑኤል ገብረሚካኤል ላይ ትኩረት ባደረጉ ረጃጅም ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም አብዛኞቹ ረጃጅም ኳሶች በፋሲል ተከላካዮች ቁጥጥር ስር ሲውሉ ታይቷል።ጨዋታው ላይ በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የቀኝ መስመር ተመላላሹ አሸናፊ ሀፍቱ ከያሬድ ከበደ በጥሩ ቅብብል ሄደው የሞከረው እና በሚካኤል ሳማኬ አማካኝነት የዳነው ኳስ ከመቐለ ሙከራዎች ለግብ የቀረበ ነበር።
ከመጀመርያው አጋማሽ ጋር በተመሳሳይ የፋሲል ኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት ያደረገ አጨዋወት የመቐለ 70 እንደርታ መልሶ ማጥቃት የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ብዙ ሙከራዎች ባይታዩበትም ፋሲልን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ እንዲያነሳ ያደረገ ግብ የተገኘበት ነበር።በ74ኛው ደቂቃ ቀኝ መስመር ላይ ቅጣት ምት ያገኙት ፋሲሎች ቅጣት ምቱን ሱራፋኤል በፍጥነት በማስጀመር መጀመርያ አጋማሽ ላይ ተቀይሮ ለገባው ሰይድ ሀሰን ሰጥቶት የተሻማው ኳስ በሁለት የመቐለ ተከላካዮች መሀል የነበረው ሙጂብ ቃሲም በቀላሉ አስቆጥሮ አፄዎቹን መሪ ማድርግ ችሏል።ከግቡ መቆጠር በኃላ ምዓም አናብስቶቹ የአቻነት ግብ ለማግኘት ከሜዳቸው ወጥተው ለመጫወት ቢሞክሩም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህም መሰረት ፋሲል ከነማ በታሪኩ የመጀመርያ የሆነውን የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ማንሳት ችሏል።