ኢትዮጵያ ቡና እና ካሳዬ አራጌ በይፋ ተፈራረሙ
ከብዙ ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የቀድሞ ክለቡን ኢትዮጵያ ቡናን ለመያዝ በቃል ደረጃ ተስማምቶ የነበረው ካሳዬ አራጌ ዛሬ በይፋ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተፈራርሟል።
በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር ላይ በንቃት እየተሳተፋ ሚገኙት ቡናዎች እስካሁን ድረስ የ10 ተጨዋቾች ዝውውር አጠናቀዋል።ሁሉም ዝውውሮች በካሳዬ አራጌ እውቅና የተከናወኑ መሆናቸውን ካሳዬ ለክለቡ ኦፊሻል ፔጅ መግለጹ ሚታወስ ነው።
የክለቡ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከተናገሩት፦
- ማሰታውቂያ -
“ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከአዲሱ አሰልጣኝ ጋር ኢንፎርማል የሆነ ግንኙነት ስናደርግ ነበር።የውጭ አሰልጣኞችን አምጥተን አንዳንዶቹ ምንም አልጠቀሙንም፤ ስለዚህ ወደ ሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ለመመለስ ወስነናል። ይህን ተከትሎ የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁመን ነበር፤ ኮሚቴውም የተለያዩ መስፈርቶችን አውጥቶ ካሳዬን መርጧል።ይህንን ተከትሎ ከአሰልጣኙ ጋር የተለያዩ ድርድሮች ስናደርግ ከርመን ዛሬ የፊርማ ስነ ስርዓቱን ለማድረግ ችለናል” ብለዋል።
በተጨማሪም አቶ ክፍሌ አማረ፦
“ካሳዬ በክለባችን ለ15 አመታት የተጫወተ እንዲሁም በ1994 እና 1995 ቡድኑን በተጫዋቾች አሰልጣኝነት የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ያገኘ እና ስታዲየሞች ተራቁተው በነበረ ወቅት በራሱ የአጨዋወት ፍልስፍና ሚሊዮኖችን ወደ ስታዲየም የመለሰ ሰው ነው።
ደጋፊው ባለፉት ሶስት አመታት የክለቡ ውጤት አሽቆልቁሎ በነበረበት ወቅት ቡናን መልሱልን የሚል ተቃውሞ ሲያሰማ ነበር፤ ይህንን ተከትሎ ካሳዬን ወደ አሰልጣኝነት ማምጣቱ በደጋፊው ስም እናመሰግናለን” በማለት ደጋፊውን ወክለው ሃሳባቸውን ገልፀዋል።