የካፍ ኢንስትራክተር አብርሃም ተክለሃይማኖት ሁለተኛ መፅሃፉን ትናንት መቐለ ላይ አስመረቀ። “እግር ኳሳችን እና የኋሊት እርምጃው” በሚል ርዕስ የተፃፈው ይሄ መፅሃፍ ትናንት የክብር እንግዶችና አድናቂዎቹ በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።
የመፅሃፋን ምረቃ አስመልክቶ የሀትሪክ ድረገጽ ፀሀፊ ዳዊት ብርሃነ ከካፍ ኢንስትራክተር አብርሃም ተክለሃይማኖት ጋር ያደረገውን ቆይታ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።
ሃትሪክ: በመጀመርያ ለቃለ መጠይቅ ፍቃደኛ ስለሆንክ አመሰግናለው።
አብርሃም: እኔም አመሰግናለው
- ማሰታውቂያ -
ሃትሪክ፡ የመጀመርያውና ያሁኑ መፅሃፍ ላይ ምን ልዩነት አለ?
አብርሃም: መጀመርያ የፃፍኩት መፅሃፍ ቴክኒካል የሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የአሁኑ መፅሃፍ ደግሞ የአስተዳደር ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ሃገራችን ላይ የሚታዩት የአስተዳደር ችግሮችን እየጠቀሰ መፍትሄን የሚጠቁም መጽሐፍ ነው።
ሃትሪክ፡ መፅሃፉ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ሊያበረክተው የሚችለው አስተዋፅኦ ምን ሊሆን ይችላል?
አብርሃም፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ያሉ ችግሮችን መፍትሄ ትጠቁማለች። እግር ኳሳችን ላይ ችግር የለም ማለት አይቻልም፤ ችግርም ስላለ ነው ክለቦቻችን ሆኑ ብሄራዊ በድናችን ውጤታማ መሆን ያልቻሉት። በፌዴሬሽኑ ውስጥ ሰላም አለመኖር፣ በተመልካችም ሰላም አለመኖር ይህ ሁሉ ሊፈጠር የቻለው ችግሮች ስላሉ ነው። እግር ኳሱን እየመሩ ያሉ ሰዎች የአቅም እጥረት፣ የስራ ዲስፕሊን ችግር እንዲሁም ራእይ ያለመኖር በአጠቃላይ እግር ኳሳችን መሪ የለውም ችግሮች ይፈጠራሉ ተጠያቂ የሚባል አካል የለም። ግልፅ የሆነ አሰራር አይታይም ስለዚህ በእግር ኳሱ ላይ ከ30-40 ዓመታት በተጨዋትነት፣ አሰልጣኝነትና ኢንስታክተርነት በምሰራበት ግዜ ያጋጠሙኝን ነገሮች በመጥቀስ ችግሮችን ለማሳየት የሞከርኩት በዛው አንፃርም መፍትሄ የምላቸውንም ነገሮች መፅሃፌ ላይ ጠቅሻቸዋለሁ። ጥናትና ምርምር ማካሄድ ለሚፈልጉ ሰዎች እንደ ሰነድ ሆኖ ያገለግላል።
ሃትሪክ፡ መፅሃፋን ፅፈህ ለመጨረስ ምንያህል ጊዜ ፈጀብህ?
አብርሃም፡ ሦስት ዓመት ወስዶብኛል ሰዎችን በመጠየቅ በስራ ግዜ ያጋጠሙኝን እና ጥናቶችን አካሂጄ ነው የፃፍኩት።
ሃትሪክ: በመቐለ የእግር ኳስ ትምህርት ቤት ከፍተሃል መፅሃፉ ትምህርት ቤቱ ላይ ምን ሊያበረክት ይችላል?
አብርሃም፡ መፅሃፉ አካዳሚው ላይ ቀጥታ የሆነ ተፅእኖ ሊፈጥር አይችልም ግን መፅሃፉ ላይ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግር ህፃናት ላይ አለመሰራቱ መሆኑን ጠቅሼዋለው። አካዳሚውን የከፈትነው ህፃናት ላይ ሰርተን አዲስ ተጨዋቾችን በማፍራት እግር ኳሳችንን ለመታደግ ነው አሁን የኢትዮጵያ ክለቦች የያዝዋቸው ተጨዋቾች በእድሜ ትላልቅ ናቸው እነዚህ ተጨዋቾች መተካት አለባቸው።
ሃትሪክ፡ እንዳንተ ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው ወደ ፌዴሬሽኑ አመራር እየመጡ ነው እና አብርሃምን ቀጣይ በፌዴሬሽን አመራርነት እንጠብቀው?
አብርሃም፡ ለግዜው እዛ መግባት አልፈልግም ምክንያቱም መሰረታዊ የሆኑ ችግሮች መፈታት አለባቸው ሰዎች ስለተቀያየሩ ብቻ የሚመጣ ለውጥ የለም እኔም ብገባ ለውጥ አይመጣም። ዋናው ስርዓቱን መለወጥ ነው። የእግር ኳሱ ቅርፅ፣ ስርዓት፣ ማናጅመንት መስተካከል ነው ያለበት እንጂ አብርሃም መጣ ሌላ መጣ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም። የኔ የመጀመርያ ፍላጎት እግር ኳሱ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ስራ መስራት ነው እሱም ህፃናት ላይ በመስራት ለሃገሪቱ አዳዲስ ፊቶችን ማስተዋወቅ ነው።
ሃትሪክ፡ መፅሃፉን ፅፈህ እንድትጨርስ ለተባበሩህ ማመስገን የምትፈልጋቸው አካላት ካሉ?
አብርሃም: ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን እና ጆውሃር መፅሃፍት ቤት ላደረጉልኝ ትብብር ከልብ ማመስገን እፈልጋለው።
ኢንስትራክተር አብርሃም ተክለሃይማኖት በመቐለ ስፓርት አካዳሚ በመክፈት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግርን ለመቅረፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።