በይስሐቅ በላይ
The BIG INTERVIEW : Zersenay Tadese
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- በቅድሚያ ለጉዞ እየተጣደፉክ
ባለህበት ሰዓት ጋዜጣችንንም አንባቢያንንም
አክብረህ ለቃለ-ምልልሱ ስለተባበርከኝ በጣም
አመሰግናለሁ…?
ዘረሠናይ፡-…እኔም… በጣም
አመሰግናለሁ…፤ …በቀጠርኩህ ሰዓት…
ባለመገኘቴና… በማጉላላቴ… በጣም
ይቅርታ… እጠይቃለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- …በዚህ ወቅት… ወደ
ኢትዮጵያ… እመጣለሁ… ብሎ…
አዕምሮህ ያሰበበት አጋጣሚ ነበር..?
ዘረሠናይ፡- …ወደ ኢትዮጵያ…
ያውም… እንደዚህ በፈጠነ ሁኔታ
እመጣለሁ ብዬ ያሰብኩበት ጊዜ
የለም፤ ግን በውስጤ አንድ ትልቅ
እምነት ነበር፤ ቀኑንና ጊዜውን ነው
በትክክል የማላውቀው እንጂ በሁለቱ
ሀገሮች መካከል ያለው የልዩነት ግድግዳ
ፈርሶ ሠላም ይመጣል የሚል እምነት
በውስጤ ነበር፡፡ አሁን እውን እየሆነ ያለው
ያ እምነቴ ነው፤ አሁን የሠላም አየር
በሁለቱም ሀገሮች በመንፈሱ በልዩነት
ቦታ አንድነት በመንገሱ በጣም ደስታ
ተሰምቶኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ስመኘው ሲርበኝ
የነበረውን ደስታ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ
አጣጥሜያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-በታሪክ ለመጀመሪያ
ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ይዞህ በሚበረው
አውሮፕላን ውስጥ ሆነህ በፍጥነት ወደ
አዕምሮህ ሲመላለስ የነበረው ነገር እንደነበር
ታስታውሰዋለህ…?
ዘረሠናይ፡- የሆነ ጉጉት ነገር፤ በቃ
አለ አይደለም የሆነ የናፈቀህን ለማየት፣
የምትጓጓለትን ሰው የማግኘት ትልቅ ጉጉት
በውስጤ ነበር፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ከሁሉም
በላይ ስለታሪክዋ ስለህዝቦችዋ የምሰማውን
ይህቺን ሀገር ከማየትና መሀከላቸው
ከመገኘት በተጨማሪ ቀደም ባሉት አመታት
አብሬያቸው ስሮጥ ከነበሩት የሀገሪቱ ብቻ
ሣይሆን የአለማችን ታላላቅ አትሌቶች
የሆኑት ኢትዮጵያዊያን ጓደኞቼን አግኝቼ
ከእነሱ ጋር የማሳልፈው ጊዜ ነበር በምናቤ
ሲታየኝ የነበረው፡፡ ከመጣሁ በኋላ በሃሳቤ
ስስለው የነበረውን ነገር በተግባር አግኝቼ
የኢትዮጵያ ቆይታዬን አስደሳች ብቻ ሳይሆን
የማይረሣ አድርጎልኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …ወደ አዲስ አበባ…
ለመጀመሪያ ጊዜ… እንደመምጣትህ…
ከተማዋን… ህዝቡን… እንዴት አገኘኸው…?
አዲስ አበባስ… እንዴት ተቀበለችህ…?
ዘረሠናይ፡- …አውነት ለመናገር… የአዲስ
አበባ… ህዝብ… የፍቅር እጆቹን… ዘርግቶ
ነው… የተቀበለኝ…፤ እኔን ብቻ ሣይሆን…
ወደ አዲስ አበባ የመጣውን… የልዑኳን
ቡድን… ደማቅ በሆነ አቀባበል ነው…
የተቀበሉን…፤ በየቦታው… ህዝቡ ስማችንን
እየጠራ…፣ እያሞካሸ… ያሳየን ቤተሰባዊ
ፍቅር… ከውስጥ የማይጠፋና… አብሮ
የሚኖር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አጋጣሚውን…
ፍፁም የተለየ ያደረገው ደግሞ… ትናንት
በውድድር ለመሸናነፍ… አብረን ስንወዳደር…
የነበሩ ታላላቅ አትሌቶች… እንደ ኃይሌ ገ/
ስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለና ገብረእግዚአብሔር ገ/
ማርያምን… የመሰሉ ጀግኖች አትሌቶች
መቀበላቸው… ከመነሻው… በአዲስ አበባ ጥሩ
ስሜት እንዲኖረን አድርጓል፡፡ በዚህም በቃላት
ለመግለፅ የሚከብድ… የደስታ ስሜት ነው…
በውስጤ የተፈጠረው፡፡
ሀትሪክ፡- …ወደ ሌሎች ጉዳዮች…
ከመግባታችን በፊት… ዘረሰናይ ማነው…?…
ከየት ተነስቶ የት ደረሰ…? …የሚለውን
ለማየት ስለቤተሰቦችህ፣ ስለትውልድና
ዕድገትህ አጫውተኝ እስቲ…?
ዘረሠናይ፡- …ዘረሠናይ… ከገበሬ
ቤተሰብ የተገኘ… የገበሬ ልጅ ነው…፤ …
ዘረሠናይን… ያበቀለችው… ምድር…
ኤርትራ ውስጥ የምትገኘው… ለመንደፈራ…
በጣም ቅርብ… የሆነችው… አዲ አላ…
ከተማ ናት፤ …ቤተሰቦቼ… ሰባት ልጆች…
ሲኖራቸው… አምስተኛው እኔ ነኝ…፤ …
ወላጅ አባቴ አሁን በህይወት የለም…፤…
ከሁለት አመት በፊት… በገጠመው…
የመኪና አደጋ በሞት ተነጥቀናል…፡፡ ይሄ
ለቤተሰባችን የከፋው የሐዘን አጋጣሚ ነው፤
አሁን ግን… ወላጅ እናቴን… ወደ አስመራ
አምጥቼያት… መልካም የሚባል… የህይወት
ጊዜን እያሳለፈች ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ቤተሰቦችህ… ጥሩ አትሌት…
እንድትሆን የነበራቸው ድጋፍን… እንዴት…
ትገልፀዋለህ…?
ዘረሠናይ፡- …መጀመሪያ አካባቢ…
ብዙም ድጋፍ አልነበራቸውም…፤ …በኋላ
ላይ… ግን… በውጤቴና… ስሜን የሀገሬን
ስም ከፍ የሚያደርግ… ስራን እየሠራሁ
መምጣቴን ሲያዩ… ድጋፍ መስጠት ጀመሩ…
እንጂ… መጀመሪያ ላይ… በዚህ በኩል…
ብዙም አልነበሩም…፡፡
ሀትሪክ፡- …ብስክሌተኛ ለመሆን…
ተመኝተህ ነው…አትሌት… የሆንከው…?
ዘረሠናይ፡- …ብስክሌት አዘወትር…
ነበር… ነገር ግን… የሙሉ ጊዜ (ፕሮፈሽናል)…
ብስክሌተኛ ግን አልነበርኩም…፤ በዞን ደረጃ
በማውንቴን ባይክ የተሻለ ነገር አሣይ ነበር፤
ውጤቴም የሚያስከፋ አልነበረም፡፡ ይሄ ነገር
ግን እዛው በዞን ላይ የሚቀርና ወደ ላይ አድጎ
ወደ አለም አቀፍ መድረክ የማሸጋገር እድሉ እምብዛም በመሆኑ ብዙ አልገፋሁበትም፤
ትቼው ወደ ሩጫው አለም ገባሁ፡፡
ሀትሪክ፡- “…ብስክሌቱ የትም አያደር
ስህም፤ ይልቁንም ሩጫውን ብትገፋበት
ይሻላል…” …በሚል ጫና ተደርጎብህ ነው…
ወደ አትሌቲክሱ የገባኸው… የሚል ነገር
ሰምቻለሁ፤ ምን ያህል እውነት ነው…?
ዘረሠናይ፡- …መምህር ሀብቶም የሚባሉ
አስተማሪ ነበሩ…፤ …እሳቸው… በሩጫው
ላይ ለትምህርት ቤት ስሮጥ ያዩኝ ነበር…
በወቅቱ እኔ ስሮጥ… ለእኔ ያልታየኝ…
ለእሣቸው ግልፅ የሆነላቸው ነገር ነበር
መሠለኝ… አንድ ቀን በብስክሌት በዞን
ደረጃ ተወዳድሬ ስመለስ መምህር ሀብቶም
አግኝተውኝ “ብስክሌቱን ትተኸው ወደ
ሩጫው ብትገባ ውጤታማ ትሆናለህ?
ብለው መከሩኝ፤ በጣምም ይገፋፉኝ ጀመር፡፡
እሳቸውም እንዳሉት ያለሁበትን ትምህር ቤት
ወክዬ ተወዳድሬ አንደኛ ወጣሁ ደስ አለኝ፤
አጠቃላይ ዙኑን ወክዩ ስወዳደር በተመሳሳይ
አንደኛ ወጣሁ፤ በመጨረሻም በሀገር አቀፍ
ውድድር 3ኛ ወጥቼ በሩጫው ተስፋ እንዳለኝ
የመምህር ሀብቶም ግምትና ግፊት ልክ
መሆኑን የሚያሳይ ፍንጭ አየሁበት፤ከዚያ
በኃላ ገፋሁበት ማለት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ለመጀመሪያ ጊዜ…
ኤርትራን ወክለህ… ተወዳድረህ 30ኛ ነው
የወጣኸው… ?
ዘረሠናይ፡- …ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሬን
ወክዬ በኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ
የተካፈልኩት በ2002 አየርላንድ (ደብሊን)
በ12 ኪ.ሜትር ውድድር ነው፤ እንዳልከውም
በውድድሩ 30ኛ ነው የወጣሁት፤ በዚህን
መሠል ውድድር ስወዳደር የመጀመሪያዬ
በመሆኑ 30ኛ መውጣቴን እንደ ትልቅ ድል
ነው የቆጠርኩት፡፡ ምክንያቱም ከውጤቱ
በላይ እስከ 50ኛ ደረጃ ከወጣሁ ማናጀር
የማግኘት እድሉ አለ ተብሎ ተነግሮኛል፡፡
በወቅቱ ስፔን የነበሩት ዮናስ ክፍሌና ነቢያት
ሀ/ማርያም የሚባሉ አትሌቶች ማናጀር
ይዘው ስለነበር እኔንም “እስከ 50ኛ ከወጣህ
ማናጀር ትይዛለህ” ብለውኝ ስለነበር 30ኛ
በመውጣቴ እኔም ከእነሱ ጋር ተደመርኩ፤
ጁሊያን ጋርሺያ የተባለች ማናጀር ለመያዝም
በቃሁኝ። አትሌቲክስም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ
ነው በሯን ወለል አድርጋ ከፍታ የተቀበለችኝ።
ሀትሪክ፡- …የአንተ የምንዜውም…
የሩጫ ጀግናህ ማነው…?
ዘረሠናይ፡- …ብዙ ኢትዮጵያዊያን
ጀግኖች አትሌቶች አሉ…፤ …በጣም
ጠንካሮች… ጎበዝ አትሌቶች አሉ…፤…
ከእነዚህ ውስጥ አንዱን መለየት ለእኔ በጣም
ከባድ ፈተና ነው የሚሆንብኝ… ያም ብሆን
ግን… ምረጥ ካልከኝና ካስጨነከኝ… አሁንም
ከኃይሌ ገ/ስላሴ… ውጪ አልጠራም…፤
ከእሱ ሌላ ጨምር ካልከኝ… ኬንያዊውን
ፖል ቴርጋርትን ጨምሮ የአትሌቴክሱ አለም
የምንግዜውም ጀግኖቼ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- …ወደ ሩጫው አለም
እንድትሳብ ማን ተፅዕኖ ፈጥሮብሃል…?
…ማንን እንደ ሮል ሞዴል እያየህ…፣ …
እያደንክ ነው… ያደከው…?
ዘረሠናይ፡- …ኃይሌ ገ/ስላሴ በእኔ የሩጫ
ህይወት ውስጥ ትልቁን ተፅዕኖ ያሳረፈ
ሰው ነው፤ …ኃይሌን ሞዴሌ የሚለው ቃል
ሣይሆን… የሩጫው አለም መምህር የሚለው
ነው የሚገልፀው… ኃይሌ ከአትሌትም
በላይ… የሆነ አትሌት ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …ስለ ግል ህይወትህ አውራኝ
እስቲ…! …በተለይ የትዳር ህይወትህ ምን
ይመስላል… ?
ዘረሠናይ፡- …ባለ ትዳር ነኝ…፤ …
ባለቤቴ ሣሮን ትባላለች…፤ …ባለቤቴ
የአራት ምርጥ ልጆች አባት አድርጋኛለች…፡
፡ የመጀመሪያዋ ሠሚራ ዘረሠናይ ትባላለች
ዘጠኝ አመት ሞልቷታል፤ ሁለተኛዋ ራኬብ
ዘረሠናይ ትባላለች እሷ ደግሞ ስድስት
አመት፤ ክብረወሰን ዘረሠናይ ሶስተኛው ልጄ
ሶስት አመት አሁን በቅርቡ ይህቺን አለም
የተቀላቀለችው ዘሳኒ ዘረሠናይ የምትባለዋ
ልጄ ደግሞ ገና 6 ወሯን ይዛለች፡፡ በአጠቃላይ
የአራት ልጆች አባት ነኝ፤ በዚህም አምላኬን
አመሰግነዋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ባለቤትህ… እንደ አንተው…
የአትሌቲክስ ሰው ናት…?
ዘረሠናይ፡- …የአትሌት ባለቤትና
ናት እንጂ… የስፖርት ሰው እንኳን
አይደለችም…፤ …በጓደኝነት ተግባብተን ነው
እስከ ጋብቻ የደረስነው…፡፡ በጣም ጥሩና
ደስተኛ ህይወትም… በጋራ እየመራን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …የሁለታችሁ የጋብቻ ስነ-
ስርዓት ሲፈፀም… ከ2500 በላይ ሰዎች
የታደሙበት…፣ …በኤርትራ ቴሌቪዥን
ሳይቀር የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን ያገኘ…
ቅልጥ ያለ ሠርግ ነበር… የሚል መረጃ
ደርሶኝ ነበር… ትክክል ነኝ… ?
ዘረሠናይ፡- …በኤሪቲቪ የቀጥታ
ሥርጭት አግኝቷል… የሚለው እንኳን
የተሳሳተ መረጃ ነው…፤ ሰርጉ የቀጥታ
ሥርጭት ሽፋን አላገኘም። መጡ የተባሉትን
የሠርጉ ታዳሚዎች ቁጥርም እንዳልከው
2500 ይሁን 2000 በትክክል ባላውቀውም
ብዙ ሰው ለመብላት ሣይሆን ደስታዬን
ለመካፈል፣ የወንድማችን ሰርግ ነው ብለው
ደስታዬን ለመጋራት መጥተዋል፡፡ በዚህ ሁሉ
ህዝብ መሃል ሆኖ መዳር፣ ጋብቻ መፈፀም
መታደል ነው፤ በወቅቱ በነበረው ነገር
እጅግ በጣም ደስተኛ መሆኔን ነው መግለፅ
የምፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡- በአቴንስ ኦሎምፒክ ከቀነኒሳ፣
ከስለሺና ከኃይሌ ገ/ስላሴ ጋር ብርቱ ትንቅንቅ
በማድረግ 3ኛ በመውጣት የነሀስ ሜዳልያ
ባለቤት ሆነሀል፤ በወቅቱ የነበረህን ስሜት
መለስ ብለህ አስታውሰኝ እስቲ … ?
ዘረሠናይ፡- …የአቴንስ ኦሎምፒክ ለእኔ
በጣም የተለየ ቦታ አለው…፤ …አሁንም
ቢሆን ከአገኘኋቸው ድሎች ሁሉ በትልቅነት
የማነሣው… ዛሬም ድረስ… እንደ አዲስ ድል
የምደሰትበት ድሌ ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- … ይሄን ያህል…? …
የወጣኸው እኮ… 3ኛ ነው…?
ዘረሠናይ፡- …እንዴ…! …ምን.. ማለትህ
… ነው….? …ከእነማን ጋር ተወዳድሬ…
ሜዳልያውን እንዳገኘሁ… ታውቃለህ…? …
በታላላቅና በጠንካራ አትሌቶች መሃል ገብተህ
ሜዲልያ ማግኘትንስ ምን ቃል ይገልፀዋል…?
…ውድድሩን መለስ ብለህ ካየኸው ከሶስት
አንበሶች መሃል የተገኘ… ከወርቅም በላይ
የሆነ የነሐስ ሜዳልያ ነው ለእኔ…፡፡ …
ደግሞም የእኔም የሀገሬ ኤርትራ ስምም…
በኦሎምፒክ… የነሐስ ሜዳልያ ባለቤት ሆነን
ስማችን በታሪክ እንዲነሣ ያደረገ ትልቅ
ውጤት በመሆኑ… ዛሬም ስለዚህ ድል
ሲነሣ… የተለየ ስሜት ነው የሚሰማኝ…፤…
በቃላት ግለፅ ብትለኝ… ድሉ ከቃላት በላይ
ነው የሚሆነብኝ…፡፡
ሀትሪክ፡- …ለዚህ ነው… ከውድድሩ
በፊት… 6ኛ ብወጣም እንዳሸነፍኩ…
ሜዳልያ… ውስጥ እንደገባሁ ነው
የምቆጥረው… ያልከው…?
ዘረሠናይ፡- …ትክክል…! …
የምትወዳደረው ከእነማን ጋር እንደሆነ
ስታውቅ ባገኘኸው ውጤት ይበልጥ
ትፅናናለህ፣ ትደሰታለህ…፤ ለእኔ ከእነዚህ
ጀግኖች ጋር ሮጦ… ሜዳልያ ውስጥ መግባት
ቀላል ነገር አይደለም…፡፡ …6ኛ ብወጣም…
አንደኛ የወጣሁ ያህል ነው የምቆጥረው…
ያልኩት ከእነማንን ጋር እንደምሮጥ ስለማውቅ
ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ይሄ ድልህ… ከአንተም
አልፎ… የኤርትራትን ህዝብና መንግሥት…
አስደስቶ የጀግና አቀባበል ተደርጎልሃል…፤ …
እስቲ የነበረውን አቀባበል… 14 አመት ወደ
ኋላ ተመልሰህ …አስታውሰህ አጫውተኝ…?
ዘረሠናይ፡- …እውነት ለመናገር
ያልጠበኩት ነገር በመሆኑ ነው መሰል…
በአስመራ የተደረገልኝ የጀግና አቀባበል…
በውስጤ የተዘበራረቀ ስሜትን ነው
የፈጠረብኝ…፤ …የሚያስደስት…፣ …
የሚያስደነግጥ…፣ ደግሞም የሚያስፈራ…
ዝብርቅርቅ… ያለ ስሜት ነበር…
የፈጠረብኝ…፡፡ …ምናልባት… በህዝብም…
በመንግሥትም እንዲህ አይነት የተለየ
ስሜትን በውስጥ የሚፈጥር… አቀባበል
ይጠብቀኛል ብዬ አለመገመቴ ይሆናል…
እዚህ ስሜት ውስጥ የከተተኝ…፡፡ …
የህዝቡን ሁኔታ ሣይ… እውነት ይሄ ሁሉ
ለእኔ ነው…? …እንደዚህ አይነት… የጀግና
አቀባበልስ ይገባኛል…?… ብዬ ራሴን
እስከመጠየቅ ሁሉ… የደረስኩበት ሁኔታ
ነበር…ከሁሉም በላይ ክቡር ፕሬዚዳንታችን
አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ያበረታቱኝ የሰጡኝ
ሞራል ከውስጤ የማይጠፋ ነው፤በአጠቃላይ
የነበረው አቀባበል… ውስጥህ ታትሞ
የሚቀር… መቼም የማይረሣ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-በርሊን ላይ ስትመራ ቆይተህ
መጨረሻ ላይ በቀነኒሳ በቀለ ተቀድመሃል
ስለተፈጠረው አጋጣሚና ስለቀነኒሳ አጫውተኝ
እስቲ…?
ዘረሠናይ፡- እ…!…የበርሊን ኦሎም
ፒክ ሌላው የማይረሳው አጋጣሚዬ
ነው፤ውድድሩን ታስታውስ እንደሆነ ረዘም
ያለውን ዙር ስመራ ቆይቼ ነው መጨረሻ ላይ
ቀነኒሳ በቀለ የአጨራረስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ
ቀድሞኝ አንደኛ የወጣው፤ብዙ ሰው ቀድሜ
መርቼ እንደመራሬ ባለመጨረሴ በብስጭትም
ይሁን በግርምት ይጠይቁኛል እኔ ያለኝን
የማውቀው እኔ ነኝ፤አጨራረስ ላይ ፍጥነት
የለኝም ለዚህም ነው በጀመርኩበት መንገድ
ስጨርስ የማልታየው፤ቀነኒሳ ቀድሞኝ
ሁለተኛ በመውጣቴ አልተከፋሁም አንደኛ
የወጣሁ ያህል ነው የተደሰትኩት፤በወቅቱ
የነበረው የቀነኒሳ ፍጥነትና አጨራረስ የሚረሳ
አይደለም።
ሀትሪክ፡-ሁለተኛ ከወጣህ በኃላ ከቀነኒሳ
በቀለ ጋር ስትተቃቀፉ የተመለከቱ በሁለቱ
አገሮች መካከል ያለውን ችግር ምክንያት
በማድረግ “በቃ ዘረሠናይ ወደ አገሩ ሲገባ
አለቀለት” በማለት የሰጉ ነበሩ አጋጣሚው
በኤርትራስ ምን ስሜት ፈጠረ?
ዘረሠናይ፡- …የሚገርምህ አጋጣሚውን
በስጋት የመነዘሩት ጥቂቶች አልበሩም፤ከቀነኒሳ
በቀለ ጋር መተቃቀፋችን በኤርትራ ከመጥፎ
ጎኑ ይልቅ በበጎ ጎኑ ነው የተወሰደው።የእኛ
መተቃቀፍ ወንድማችነት ጠቋሚ ተደርጎ
በመወሰዱ ይሄንን ተከትሎ የተፈጠረ ነገር
የለም። ስፖርት ሠላምን በማምጣት በኩል
ትልቅ መሣሪያ እንደሆነ ሁሉም የሚረዳውም
ይመስለኛል።
ሀትሪክ፡- …ከ20 አመት በፊት
በተፈጠረው ችግር… ኤርትራና ኢትዮጵያ
በጠላትነት ይተያዩ ነበር…፤ …ይሄንን
ተከትሎ… ዘረሠናይ ታደሠ በአንድ አጋጣሚ
ድልን ከኢትዮጵያውያን ለመንጠቅ ይሮጥ
ነበር…፡፡ …ዛሬ ደግሞ ያ ታሪክ ተቀይሮ…
በፊት ለአሸናፊነት ሲተናነቃቸው ከነበሩ
አትሌቶች ጋር… በሀገራቸው በደስታና በፍቅር
የሚያሣልፍበት እድል ተፈጥሯልና… ይሄንን
አጋጣሚ… እንዴት ነው የምትገልፀው…?
ዘረሠናይ፡- …በወቅቱ በእኛ በአትሌቶች
መካከል በመሸናነፍ ከሚደረግ ፉክክር
በዘለለ በመካከላችን የነበረ ልዩነት ያን ያህል
አልነበረም፤ ይሄ ደግሞ ስፖርት ነው፤
ከወንድምህ ከእናትህ ልጅ ጋርም ብትሮጥ
ለማሸነፍ መተናነቅህ አይቀርም፡፡ ስፖርት
ለሠላም ትልቅ መሳሪያ እንደመሆኑ በዚያን
ጊዜም ቢሆን ልዩነት የሚጠብበትን፣ አንድነት
መፍጠርን ነበር የምናስበው፡፡ አሁን ደግሞ
በበለጠ በተሻለ ሁኔታ ሁለቱ አንድ የሆኑ
ህዝቦች ወደ አንድነት ወደ ፍቅራቸው
መምጣታቸውና መመለሳቸው በጣም
ያስደስታል፡፡ ይሄንን ሠላም ጠብቆ አጠናክሮ
መጓዝ ነው የሚታየኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …የሁለቱ ሀገሮችን ሠላም
በመመለሱ በኩል የአንበሳውን ድርሻ የወሰዱት
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ናቸውና
ለሠላሙ ከአምላክ የተላኩ መሲህ ናቸው ብሎ
መውሰድ ይቻላል…?
ዘረሠናይ፡-…ለሠላሙ መምጣት 20
አመት ሙሉ ተገንብቶ የነበረው የልዩነት
ግምብ ለመፍረሱ በተናጠል ሣይሆን
ለሁለቱም መሪዎች ለክቡር ጠ/ሚኒስትር
ዶ/ር አብይ አህመድና ለክቡር ፕሬዚዳንት
ኢሳያስ አፈወርቂ በአንድነት ነው ምስጋና
ማቅረብ የምፈልገው፡፡ ለሁለቱ ሀገር ህዝቦች
ሠላም ላደረጉት የማያቋርጥ ትግል ማመስገን
የምፈልገው ሁለቱንም መሪዎች እንዲሁም
የሠላሙ ተባባሪ ለሆኑት ለሁለቱም
ህዝቦች ነው፡፡ የሰላምን፣ የፍቅርን ትርጉም
የሚያውቀው ያውቀዋል፡፡ አሁን የተፈጠረው
አጋጣሚ በጣም ትልቅና በጣም አስፈላጊያችን
እንደሆነ ለህዝቡ መግለፅና ይሄንንም በጋራ
ጠብቀን ወደፊት መጓዝ እንዳለብን ነው
ማንሣት የምፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡- …ኢትዮጵያውያን አትሌቶ
ችን… ግለፅልኝ ብልህ እንዴት ነው የምት
ገልፃቸው…?
ዘረሠናይ፡- …እኔ ብቻ አይደለሁም
አለም ሁሉ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች
አድናቆትና ክብር አለው፤ ይሄ ደግሞ አሁን
የመጣ ሣይሆን ከድሮም ጀምሮ በእነ ሻምበል
አበበ በቂላ፣ ማሞ ወልዴና ምሩፅ ይፍጠር
በኋላ ደግሞ በእነ ኃይሌ፣ ደራርቱ፣ ቀነኒሳ፣
ስለሺ፣ገ/እግዚአብሄር፣ጥሩነሽና በመሳሰሉት
አትሌቶች ኢትዮጵያ በዓለም ትከበራለች
ትደነቃለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጣም ጠንካሮች
ጎበዞች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያና ኬንያ በዓለም
ተፎካካሪ እንደሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም
ኢትዮጵያ የብዙ ውጤታማ አትሌቶች
መፍለቂያ ሀገር በመሆንዋ ለኢትዮጵያ
አትሌቶች የተለየ ስሜት ነው ያለኝ፡፡ ለዚህም
ይመስለኛል ወደዚህች ሀገርና እነዚህ ጀግኖች
ወዳሉበት ሀገር ስመጣ የተለየ የደስታ ስሜት
የተሰማኝ፡፡
ሀትሪክ፡-ቀደም ሲል ከኢትዮጵያዊያን
አትሌቶች ጋር የነበረህ ግንኙት ምን
ይመስላል? እዚህ መጥተህ ስታገኛቸውስ ምን
ተሰማህ?
ዘረሠናይ፡- …እውነት ለመናገር ቀደም
ሲል የጠነከረ ግንኙነት ነበረን ለማለት
ይቸግረኛል…፤ …ከሠላምታ የዘለለ ግንኙነት
አልነበረንም፡፡ …ከገ/እግዚአብሔር ጋር
ቀደም ብለን እንተዋወቃለን፤ እንዳልኩህ
ግንኙነታችን ከሠላምታ ከፍ ያለ አልነበረም፡
፡ ያም ቢሆን ግን ኃይሌ ቤጂንግ ላይ
መክሮኛል አበረታቶኛል፤ነፍሳቸውን ይማርና
አየርላንድ ላይ 30ኛ ስወጣ በተመሳሳይ
አበረታተውኛል፤ እዚህ ከመጣሁ በኋላ
ያየሁት ግን ልብን የሚነካ ለዘላለም ከውስጤ
የማይጠፋ በትልቅ ደረጃ የምይዘውን ፍቅር
ያለስስት ነው የሰጡኝ፡፡ ከአቀባበሉ ጀምሮ
በየዕለቱ በታላላቅ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች
ተከብቤ ትልቅ እንክብካቤ ተደርጎልኝ ነው
ያሳለፍኩት፡፡ ገ/እግዚብሔር ገ/ማርያም ከእነ
ባለቤቱ ከመጣሁ ቀን ጀምር ከጎኔ በመሆን
ቤተሰባዊነታቸውን አሣይተውኛል፡፡ ኃይሌና
ቀነኒሳም እንዲሁ መግለፅ እስኪከብደኝ ከጎኔ
ሳይለዩ በመኖሪያ ቤታቸው የክብር የእራት
ግብዣም አድርገውልኛል፡፡ የተለያየ ቦታ
በመውሰድም አጋርነታቸዉን ገልፀውልኛል፡
፡ በዚህም ልቤ ክፉኛ ተነክቷል፡፡ ወደ ሀገር
ቤት የምመለሰውም ትልቅ ቁም ነገር ያለው
መልዕክት ይዤ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ኃይሌን፣ ቀነኒሳን፣ ገ/
እግዚአብሔርን በፊት ከሩቅ በውድድር
ለመሸናነፍ በሚደረግ ፉክክር ብቻ ነበር
የምታውቃቸው፤ ዛሬ በቅርበት ስታያቸው
ምን አይነት ሰዎች ሆነው አገኘኻቸው…?
ምንስ ታዘብክ…?
ዘረሠናይ፡- ኡ….! በጣም የተለዩና
የፍቅር ሰው ሆነው ነው ያገኘኋቸው፤ ፍቅርን
የተራበ ሰው ታውቃለህ? እንደዛ አይነት፤
የሰውና የፍቅር ረሃብን ነው ያየሁባቸው፡፡
በጣም መልካምና ደግ ሰዎች ናቸው፡፡ ለሰው
ልጅ ልዩ ፍቅርና ቀና የሚባል አስተሳሰብም
ያላቸው ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ ከእነሱ ጋር
ያሳለፍኩት ጊዜ በደስታና በፍቅር የተሞላ
ነበር፡፡ ከጓደኝነት፣ በአንድ ሙያ ውስጥ
ካለ ትውውቅ በዘለለ ጥልቅ ቤተሰባዊነትን
የመሠረተ ግንኙነት ነው የነበረን፡
፡ አጋጣሚው በቅርበት የምንተዋወቅበት፣
የምንጨዋወትበት፣ ምስጢር የምንካፈልበት፣
ወደፊትም ግንኙነታችንን የምናጠናክርበት
ምቹ የሚባል አጋጣሚ ተፈጥሯል፤ በዚህም
በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ጥሩ ወንድሞቼን መልካም
ሰዎችን በአካል አግኝቼ ነው የምመለሰው፡፡
ስልክም የተለያዩ አድራሻዎችን ስለተለዋወጥን
ከዚህ በኃላ በየጊዜው እንደምንገናኝ ተስፋ
አደርጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-እዚህ የተደረገልህ አቀባበልና
ያገኘኸው የተለየ ፍቅር በውስጥህ ምን
ፈጠረ…?
ዘረሠናይ፡- የወንድሞቼን የፍቅር እዳን
ተሸክሜ ነው ወደ ሀገሬ የምሄደው፤ በደስታዬ
ውስጥ የማስበው ይሄንን እዳዬን እንዴት ነው
የምከፍለው? የሚለውን ነው፡፡ አምላክ እድለኛ
አድርጎኝ አቅሙን ሰጥቶኝ እነሱም ወደ
አስመራ መጥተው ያለስስት የሰጡኝን ፍቅር
እኔም በሀገሬ ተቀብዬ ወንድማዊ ፍቅሬን
ለመጠት በክብር ስለመቀበል ነው የማስበው፤
የእነሱን ያህል ይሆናል ባልልም፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ
ጊዜ የመጣኸው የአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ
ሩጫ በሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ
እንድትገኝ ተጋብዘህ ነውና በክብር እንግድነት
ስትጋበዝ ምን ተሰማህ… ?
ዘረሠናይ፡- …በመጀመሪያ ግብዣውን
የሰማሁት በመቀሌ በኩል አድርጎ ወደ
አስመራ በመጣው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ
ዋና ስራ አስኪያጅ በሆነው በአቶ ኤርሚያስ
አየለ በኩል ነው፤ በወቅቱ በዚህ ጉዳይ ላይ
በስፋት ከተወያየን በኋላ አቶ ኤርሚያስ እኔ
በክብር እንግድነት እንድገኝ የአትሌቴክስ
ቡድናችንም በውድድሩ ተሳታፊ እንዲሆን
ለፌዴሬሽኑ ግብዣ አቀረበልን፡፡ ፌዴሬሽኑም
እኔም ደስተኞች ሆነን ግብዣውን ተቀበልን፤
በጥሪው መሠረትም ወደ አዲስ አበባ መጣን፡፡
እዚህ ከመጣን በኋላ ያየሁት ነገር ለማመንና
ለመግለፅ የሚከብድ ነው፡፡ በዚህን መሠል
ከሩጫም በላይ የሆነ መድረክ ላይ በክብር
እንግድነት መጋበዝ ከእድለኝነትም በላይ ነው፡
፡ ለማየት እንደቻለኩትም እንደተረዳሁትም
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሩጫም በላይ ሆኖ
ነው ያገኘሁት፡፡ 44 ሺህ ሰው በሚሮጥበት
የአህጉሪቱ ትልቅ የጎዳና ውድድር ላይ ያውም
በክብር እንግድነት መገኘት ክብርም፣ ትልቅ
የኩራት ስሜትንም ነው በውስጤ የፈጠረው፡፡
ሀትሪክ፡- …44ሺ ሰዎች የሮጡበትን
የአህጉሪቱ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ የነበረውን
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን የህዝቡንና
በአጠቃላይ የነበረውን ድባብ እንዴት
አገኘኸው…?
ዘረሠናይ፡- …ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ
በጣም ትልቅ ውድድር እንደሆነ ብገምትም
በዚህ ደረጃ የደመቀ፤ አንዳች የደስታ
ስሜትን ወይም ድባብን የሚፈጥር ውድድር
እንደሆነ ግን በፍፁም አልጠበኩም፤ ያየሁት
ነገር በሙሉ ከግምቴ በላይ ነው፡፡ በጣም
ደስ የሚል ቀለምና ውበት ያለው ነገር
ነው የተመለከትኩት፡፡ ህዝቡ በጣም ነው
የሚያምረው፣ ለውድድሩ ተጨማሪ ውበቶችም
ነበሩ፡፡ ከሩጫው በዘለለ ትልቅ መልዕክት
የሚተላለፈበት፣ ገቢ የሚሰበሰብበት መሆኑ
ደግሞ ይበልጥ የተለየ ዋጋ እንድትሰጠው
ያስገድድሃል፤ የጀግኖች አትሌቶች መፍለቂያ
የሆነች ሀገር የሆነችውን ኢትዮጵያን ይበልጥ
የማስተዋወቅ ስራን የሚሠራ ከሩጫም በላይ
የሆነ ውድድር ነው፡፡ ይሄን ታሪክ በአይኔ
በማየቴ የክብር እንግዳም ሆኜ በመጋበዜ
የተለየ የደስታ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል፡፡
ሀትሪክ፡-በእለቱ ውድድር ላይ ህዝቡ
ለአንተ ያለውን ክብርና ፍቅር ስምህን እየጠራ
ሲገልፅስ ምን አይነት ስሜት በውስጥህ
ተፈጠረ…?
ዘረሠናይ፡- ህዝቡ ስሜን እየጠራ ፍቅሩን
ሲገልፅልኝ የተስማኝ ስሜት የሆነ አንዳች
የደስታ ስሜት ውርር ሲያደርግህ ታውቃለህ?
ልክ እንደዛ አሁን በቃላት የማልገልፀው ልዩ
የደስታ ስሜት ነው በውስጤ የተፈጠረው፤
በእርግጥ ገና የአዲስ አበባን መሬት
ከረገጥኩባት ቀን ጀምሮ ህዝቡ በየቦታው
ሲያገኘኝ ያሳየኝ የተለየ ፍቅር እንደሆነ
ባውቅም የታላቁ ሩጫ ቀን ሁሉም በዚያ
መንገድ ለእኔ ያላቸውን ክብር በአንድነት
ሲገልፁ ሳይ ስሜቴን መቆጣጠር ነው
ያቃተኝ፤ ከውስጤ የማይጠፋና የማይዘነጋ
ትልቅ ታሪክ ነው ህዝቡ በውስጤ ታትሞ
እንዲቀመጥ ያደረገው፡፡
ሀትሪክ፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን
ስትመለከት አልቀናህም? መንፈሳዊ የቅናት
ስሜት በውስጥህ አልተፈጠረም…?
ዘረሠናይ፡- በእርግጥ የእነ ኃይሌ ገ/
ስላሴ አይነቱን ታላቁ ሩጫን ያህል
ባይሆንም ከዛሬ ስድስት አመት በፊት እኔም
በሀገሬ የጀመርኩትን ተመሳሳይ ውድድር
አካሄዳለሁ፡፡ ግን እንዳልኩህ ከታላቁ ሩጫ
በኢትዮጵያ ጋር የሚነፃፀር አይደለም፡
፡ መዋሸት ካልሆነ 44 ሺህ ሰው እንደዚህ ደምቆ ሲሮጥ ማየት ደስታን ብቻ ሣይሆን
መንፈሳዊ ቅናትም በውስጥህ እንዲፈጠር
ያደርጋል፡፡ እኔም በሀገሬ ብለህ እንድትመኝም
ያስገድድሃል፡፡ እኔ በሀገሬ የጀመርኩትን
እንዴት ወደዚህ ደረጃ ማሳደግ ይቻላል?
የታላቁ ሩጫ አይነት ብዙዎችን የሚያሳትፉ
ውበት ያለው ከሩጫም በላይ አመታዊ
ፌስቲቫል የሚመስል ውድድርን እንዴት
በአስመራ ማካሄድ ይቻላል? የሚለውን ወደ
ሀገሬ ስመለስ ከሀገረ ኤርትራ ፌዴሬሽን ጋር
የምነጋገርበት ነው የሚሆነው፡፡ ግን ትልቁ
ቁም ነገር በውድድሩ ከመደሰቴ በመጋበዜ
ካገኘሁት ክብር ባልተናነሰ እዚህ መጥቼ ይሄን
ውድድር በማየቴ እንዲሁም ከኃይሌ ገ/ስላሴና
ከሌሎቹም ትልቅ ቁም ነገር ያለው ትምህርት
አግኝቼበታለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ዘረሠናይ ከልምምድና
ከውድድር ውጪ ያለውን ትርፍ ጊዜ በምን
ዘና ፈታ እያለ ያሳልፋል…?
ዘረሠናይ፡- …ወደ ባህር ዳርቻ ሄጄ…
ከሠላማዊው ውቅያኖስና ከውሃው ጋር
ማውራት የእነሱን ቋንቋ ፀጥ ረጭ ባለ
ሁኔታ ማደመጥ ስለሚያስደስተኝ ባህር ዳርቻ
አካባቢ ማሳለፉን እመርጣለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ
የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ማለትም ቱር ደ
ፍራንስ (የብስክሌት ውድድርን) እና የእግር
ኳስ ጨዋታን በመከታተል አሣልፋለሁ፤
ከቤተሰቦቼ ጋርም የማሣልፈው ጊዜ በጣም ዘና
ያረገኛል ያስደስተኛል ግን ይሄ ሁሉ ከስንት
አንዴ ነው የሚገኘው፡፡ አትሌት ስትሆን
የተትረፈረፈ ጊዜ የለህም፤ በልምምድና
በውድድር ትጠመዳለህ፡፡
ሀትሪክ፡- …በአጨዋወቱ… ማርኮህ
ደጋፊው ያደረገህ… የአለማችንን ክለብ ጥራ
ብልህ ማንን ትጠራለህ… ?
ዘረሠናይ፡- …እዋይ…! … ሪያል
ማድሪድን ነዋ…! …የሪያል ማድሪድ
የጨዋታቸውና የውጤታቸውም አድናቂ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ለየትኛው… የአለማችን
አሰልጣኝ… ክብር አለህ…?
ዘረሠናይ፡- ከብዙ ስኬቶች በኋላ
ከሰልጠናው ራቅ አለ… እንጂ ለፈረንሣዊው…
የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን
የተለየ ክብር አለኝ፡፡ ዚዳንን ሲያሰለጥን ብቻ
ሳይሆን ሲጫወትም የድንቅ ችሎታው አድናቂ
ነበርኩ፡፡
ሀትሪክ፡- …የትኛው የአለማኝ ጥበበኛ
ተጨዋችስ በድንቅ ችሎታውና አጨዋወቱ
ማርኮሃል… ?
ዘረሠናይ፡- …አሁንም ከነጩ ቤት (ሪያል
ማድሪድ) አልወጣም አሁን ወደ ጁቬንቱስ
ቢሔድም የፖርቹጋላዊው ክርስትያኖ ሮናልዶ
ችሎታ አድናቂ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …አትሌቴክስ… ሀብታም…
አድርጎሃል…?
ዘረሠናይ፡- …እስከአሁን ምንም
አላጣሁም…፤ ተመስገን ማለትን ነው
የማስቀድመው፤ የተሻለ ኑሮ እየኖርኩ ነው፤
ያጣሁት ነገር የለም…፡፡
ሀትሪክ፡- …እዚህ በሀገራችን ያሉ ታላላቅ
አትሌቶች የራሣቸው የቢዝነስ ፎቅና የተለያዩ
ቢዝነሶች አሏቸው፤ አንተም በአስመራ
ሜዴያን ሆቴልን በ194 ሚሊዮን ናቅፋ
ገዝተህ የቢዝነሱን አለም እንደተቀላቀልክ
አውቃለሁና እስቲ ስለ ቢዝነስህ አውራኝ?
ዘረሠናይ፡- ሳቅ… እዋይ…!…አሁን ይሄ
ነው… ይሄ ነው… ብዬ የምዘረዝርልህ…
ነገር… የለም፤ …ለጊዜው… ቢዝነስ
ውስጥ… በስፋትም አልገባሁም፤ …አሁን
ባለው ሁኔታ… ግን ቢዝነስ ውስጥ ገብቼ…
የምንቀሳቀስ ነው የሚመስለኝ…፡፡
ሀትሪክ፡- …በአስመራ ጎዳናዎች…
ላይ በምን አይነት መኪና ነው…
የምትንፈላሰሰው…? በፌሬራ፣በሎምባርጊኒ
…ወይም በሌላ …? …ወይስ በሌላ….?
ዘረሠናይ፡- …አሁንም…ቀልደኛ
ሰው ነህ…!… እኔ መኪና አልመርጥም…
ያገኘሁትን ነው የማሽከረክረው…!
ሀትሪክ፡- …ከዚህ በኋላ ማራቶን ላይ
ትኩረት እንደምታደርግ ሠምቻለሁ…፤
ማራቶንን በተመለከተ ምን እያሰብክ ነው…?
…ከዚህ ውጭ የ Nike’s breaking2
(ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት)
የሚሠራው የናይክ ቡድን አባል በመሆንህም
ሪከርዱን በተመለከተ ምን ታስባለህ…?
ዘረሠናይ፡- …ቀጣይ እቅዴ… በማራቶን
የራሴን ሌላ ታሪክ ማፃፍ ነው፤በቅርቡ
በበርሊን ማራቶን 5ኛ ወጥቻለሁ፤ ይሄንን
ማሳደግ እፈልጋለሁ። ሌላው እንዳልከው
Nike’s breaking2 ከሁለት ሰዓት በታች
ለመግባት በሚሠራው ስብስብ ውስጥ
በመካተቴም ትልቅ ኩራት ነው የሚሰማኝ፡
፡ ወደፊት በማራቶን አዲስ ታሪክ የማፃፍ
ህልሙ አለኝ፤ ለዚህም ጠንክሬ የምሰራ ነው
የሚሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- …በኢትዮጵያ ቆይታህ የኃይሌ
ገ/ስላሴን ያያ ቪሌጅንና የቀነኒሳን ማዕከል
መጎብኘትህን ሰምቻለሁ፤ ይሄን ያደረክበት
የተለየ ምክንያት አለህ…?
ዘረሠናይ፡- …ምስጋና ለታላላቆቹ
አትሌቶች ይሁንና ያያ ቪሌጅንና
የቀነኒሳን ማዕከል በገ/እግዚአብሔር ገ/
ማርያም አማካይነት ሱልልታ ድረስ ሄጄ
የመጎብኘት እድል አግኝቻለሁ፤በአካል
ተገኝቼ ስላየኃቸውም በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
የኢትዮጵያ የአየር ፀባይ ለአትሌቶች ምቹና
ተስማሚ ነው፡፡ ወደፊት የኤርትራ አትሌቶች
ወደዚህ መጥተው እንዲሠሩ ለኤርትራ
ፌዴሬሽን ለመንገርም ቋምጨያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ሣይህ በጣም ተጣድፈሃል…፤
…ቤተሰቦችህም አስሬ እየደወሉ እየጠበኩህ
እንደሆነ እየነገሩህ ነው… በኢትዮጵያ
የስፖርት ጋዜጣ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን
ቃለ-ምልልልሰ በመስጠት ስለተባበርከኝ፤
ጀግናው አትሌታችን ገ/እግዚአብሔር ገ/
ማርያምም ውድ ጊዜውን ሰውቶ በማስተርጎም
ስለተባበረኝ ሁለታችሁንም ከልብ አመስግኜ
ከመለያየታችን በፊት ቀረ የምትለው
ማስተላለፍ የምትፈልገው ካለ እድሉን
በመስጠትና በማመስገን እንለያይ…?
ዘረሠናይ፡- በኢትዮጵያ በነበረኝ ቆይታ
ህዝቡ በተለይ ደግሞ ቆይታዬን ያማረ
ያደረጉልኝን ታላላቅ አሌቶች ፍቅራቸውና
ያለስስት የሰጡኝን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ፡
፡ አክብራችሁኛል እግዚብሔር ያክብራችሁ
በሁለቱ ሀገ የታመልው የሰላም አየር
መንፈሱ እፈልገለሁ፡፡ በመቀጠል የኤርትራና
የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄን የመሰለ ደስታን
የሚያጠናሙበት የተራራቁ የተነፋፈቁ
የሚገናኙበትና ፍቅራቸውን የሚሰጡበትን
እድል በማግኘታቸው እንኳን ደስ አላችሁ
በማለ|ት አመሰግሃለሁ፡፡ ለዚህእድል መፈጠር
ለተጉት ሁሉ ከልብ የመጨነ ምስጋና
አቀርብላችኋዋለሁ፡፡ አንተም የሀት ሪክ
ጋዜጣ አዘጋጅ እንግዳ በማድረግ በጋዜጣችሁ
ድልድይነት ከህዝቡ ጋር ስላገናኛችሁኝና
ስላከበራችሁኝ እናንተንም እግዚአብሔር
ይስጥልኝ ለማለት እፈልጋለሁ፤ አመሰ
ግናለሁ፡፡