“ስለ ቅ/ጊዮርጊስ ታሪክ ሲወራ ወይም ሲፃፍ ፋሲል
አሻራው አንድ ቦታ ላይ እንዲኖር ይፈልጋል!”
ፋሲል ተካልኝ በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ታሪክ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠሩ የቀድሞ ድንቅ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡ በዛ የተጨዋችነት ዘመኑ ከአንጋፋው የሀገሪቱ ክለብ ጋር በርካታ ዋንጫዎችን ለመሳም የቻለ ሲሆን ጫማውን ከሰቀለ በኋላም በአሰልጣኝነቱ መስመር የራሱን ታሪክ በማፃፍ ላይ ይገኛል፡፡
በተጨዋችነቱ ያገኘውን የኢትዮጵያ
ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ በአሰልጣኝነቱም ከቅ/
ጊዮርጊስ ጋር ያነሳ ሲሆን ኮከብ አሰልጣኝም
ተብሎ መመረጥ ችሏል፡፡ አሁን ደግሞ
ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ይሄንኑ ክለብ
በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል
ውስጥ እንዲገባ አስችሎታል፡፡
“አሰልጣኝነት ስራዬ ነው፤ ከስራዬ
ባለፈ ግን ጊዮርጊስ ተወልጄ ያደኩ ያህል
የሚሰማኝና ሁልጊዜም ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ታሪክ ሲወራ ወይም ሲፃፍ ፋሲል አሻራው
አንድ ቦታ እንዲኖር አጥብቄ እፈልጋለሁ…”
የሚለው አመለ ሸጋው አሰልጣኝ ፋሲል
ተካልኝ በቻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ድልድል
እና በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ
ዙሪያ ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ማኔጂንግ
ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር
ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡
ሀትሪክ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በኢትዮጵያ
እግር ኳስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲሱ
የውድድር ፎርማት መሰረት የምድብ ድልድል
(16 ውስጥ) መግባቱ ለክለቡም ለሃገርም ያለውን
ጥቅም እንዴት ነው የምትገልፀው?
ፋሲል፡- የክለባችን የዘመናት ህልምና
ምኞት ወደሆነው የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ
የምድብ ድልድል ውስጥ መግባታችን እንደ
ክለብም እንደ አገርም ትልቅ ጥቅም አለው፡
፡ ክለባችን በአህጉሪቱ ውድድር አንድ እርምጃ
መራመድ በጣም ይፈልግ ነበር፡፡ የክለባችን
ደጋፊዎችና የስራ አመራር ቦርድ ቅዱስ
ጊዮርጊስ ከአህጉሪቱ ታላላቅ ክለቦች አንዱ
ሆኖ የማየት ህልማቸው መንደርደሪያው
ወይም ጅማሬው አድርጌ ነው የማየው፡፡ ወደ
ፊት ልናሳካቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች
እንዳሉ ባውቅም እንደ ክለባችን ህልም ግን
አንዱን ስኬት ማሳካታችን የተለየ የደስታ
ስሜት በውስጣችን እንዲፈጠር አድርጓል፡
፡ እንደ ሃገር ስታሰበው ደግሞ ወደ ትልቅ
ደረጃ ለመድረስ መንገድ የሚከፍት ፓዮኔር
(ፈር ቀዳጅ) የሚሆን ክለብ የግድ ያስፈልግ
ነበር፡፡ የምንወክለው ሃገርን እንደመሆኑ
የቻምፒዮንስ ሊግ ምደብ ድልድል ውስጥ
መግባት እንደሚቻል የሚያሳይ ውጤት
ማስመዝገብ ለሃገርም ለክለቦቻችንም ትልቅ
መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብቻ ሳይሆን
ትልቅ ኩራትም እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡
፡ እኛ እዚህ መድረሳችን ሌሎች የአገራችን
ክለቦችም ያነሳሳል፡፡ ለዚህ ስኬትም ሆነ ከዚህ
ከፍ ያለ ውጤት ለማስመዝገብም ጠንክረው
እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡ ይሄ ሲሆን የአገራችን
እግር ኳስ ያድጋል፡፡ ስሟም በውጤታማነት
የሚጠራበት ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል፡
፡ አሁን ያገኘነው ውጤት ትልቅ ኩራትን
የሚያላብስ እንደሆነ ባይካድም እንደ ክለባችን
የዘመናት ልፋት ከሆነ ግን ከዚህ የበለጠ
ይገባው ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- በ21ኛው የካፍ ቶታል ቻምፒዮንስ
ሊግ ውድድር በምድብ ሐ ከደ/አፍሪካው
ሜማሎዲ ሰንዳውስ፣ ከቱኒዚያው ኤስፕራንስ እና
ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው ኤስ ቪታ ጋር
መደልደላችሁ ምድቡን የሞት ምድብ የሚል
ስያሜ እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ አንተስ ድልደሉን
እንዴት አገኘኸው?
ፋሲል፡- እውነት ነው እኔም ጋር ያለው
ተመሳሳይ ስሜት ነው፡፡ ከእኛ ጋር አብረው
በአንድ ምድብ ውስጥ ያሉት ሶስቱም የአህጉሪቱ
እግር ኳስ ትልቅ የድል ስኬትና ልምድ
ያላቸው ክለቦች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ማማሎዲ
ሰንዳውስን ብትወስድ የወቅቱ ሻምፒዮን ነው፤
የቱኒዚያው ኤስፔራንስም ሁለት ጊዜ (በ1994
እና 2011) የአህጉሪቱን ዋንጫ ከፍ አድርጎ
የሳመ፤ ለ4 ጊዜያት (በ1999፣ 2002፣ 2010
እና 2012) ለፍፃሜ የቀረበ ትልቅ የውጤት
ታሪክ ያለው ክለብ ነው፤ የዲሞክራቲክ
ሪፐብሊክ ኮንጎው ኤስ ቪታም በ1973 ዓ.ም
የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችሏል፡
፡ ከዚህ በተጨማሪ በ1981 እና በ2014
ለፍፃሜ ቀርቦ ዋንጫ የተነጠቀ ክለብ ነው፡
፡ ሶስቱም ክለቦች ትልቅ የውጤትና የልምድ
ታሪክ ያላቸው መሆናቸውን ስታይ ዕውነትም
ምድቡ በጣም የጠነከረና የሞት ምድብ
መሆኑን ትረዳለህ፡፡ እውነት ለመናገር ግን
15ቱም ቡድኖች የአህጉሪቱ ጠንካራ ቡድኖች
በመሆናቸው የትም ምድብ ውስጥ ብንገባ
ከባድ ተጋጣሚዎችን ነው የምናገኘው፡፡ ከዚህ
ውጪ በሌላ ምድብ ብንደለደልም ምድቡ
ከባድ ከመሆን አይድንም፡፡ 16 ውስጥ ገብተህ
ቀላል ምድብን መጠበቅ የማይታሰብ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚህ አንፃር ከኤስፔራንስ፣
ከሰንዳውንስ እና ከኤስ ቪታል ጋር በአንድ
ምድብ መደልደላችሁ ብቻውን የቻምፒዮንስ ሊግ
ዘመቻችሁን አስፈሪ ያደርገዋል?
ፋሲል፡- እውነት ለመናገር አብረውን
የተደለደሉት ክለቦች በአህጉሪቱ እግር ኳስ
ያላቸውን ውጤት ስትፈትሽ የገዘፈ የውጤትና
የልምድ ታሪክ ያላቸው መሆናቸውን
ትረዳለህ፤ ግን ይሄ ወይም ስማቸው ብቻውን
ከጨዋታው በፊት እንድትሸነፍ ያደርግሀል
የሚል እምነት የለኝም፡፡ በውጤትና
በልምዳቸው ልናከብራቸው እንጂ ልንፈራቸው
ይገባል ብዬም አላምንም፡፡ የእኛንም የቅርብ
ጊዜ የውጤት ታሪክ መለስ ብለህ ካየህ
በአህጉሪቱ እግር ኳስ የገዘፈ ስምና ውጤት
ካላቸው ክለቦች ጋር ተጫውተን በከፍተኛ
የጨዋታ ብልጫ ያሸነፍንበት እንዲሁም
በጥቃቅን ታክቲካዊና የልምድ ችግር ውጤት
ያጣንባቸው ሁኔታዎች እንጂ በስማቸው
ወይም በታሪካቸው ብቻ አልተሸነፍንም፡
፡ ከዚህ አንፃር አብረውን የተመደቡት
ክለቦች የፈለገውን ያህል ውጤትና ታሪክ
ቢኖራቸውም በስማቸው ብቻ አንበረግግም፤
ቀድመንም አንሸነፍም፡፡ የምድብ ድልድሉ
ከጠንካራና ውጤታማ ክለቦች ጋር ከማገናኘቱ
ውጭ አዲስ ልምድም ይዞልን እንደመጣም
ነው የሚሰማኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ምን አይነት ልምድ?
ፋሲል፡- ካልተሳሳትኩ በስተቀር
ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄዶ
ሲጫወት እኔ እስከማውቀው ድረስ በታሪኩ
የመጀመሪያ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ወደ ቱኒዚያ
ሄደን ተጫውተን ከኤስፔራንስ ጋር ግን
የመጫወት እድል ያገኘነው ገና አሁን ነው፤
ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመሄድ
እድል አግኝተናል፡፡ ግን ከኤስ ቪታል ጋር
የመጫወት እድሉን አላገኘንም፡፡ ከዚህ
አንፃር የምድብ ድልድላችን አዲስ ልምድ
የምናገኝበት አጋጣሚንም ፈጥሮልናል፡፡
ወደ ፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊርስበት ላሰበው
ስኬት የተለየ የእግር ኳስ ታሪክና ውጤት
ካላቸው ክለቦች ጋር መደልደሉ አዲስ ልምድ
እንድንቀስምበትም ይረዳናል፡፡
ሀትሪክ፡- ከምድቡ መክበድ በተጨማሪ
የቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያው ጨዋታችሁን
ከ2016ቱ ሻምፒዮን ያውም ከሜዳችሁ ውጪ
መሆኑስ ምን ስሜት ይፈጥርብሀል?
ፋሲል፡– የመጀመሪያው የቻምፒዮንስ ሊግ
የምድብ ጨዋታችን ከወቅቱ ሻምፒዮን ከሆነው
ማማላዲ ሰንዳውንስ ጋር ደቡብ አፍሪካ ላይ
ነው የምናደርገው፡፡ ተጋጣሚያችን የ2016
ሻምፒዮን፤ እንዲሁም ጨዋታችን ከሜዳችን
ውጪ መሆኑን በመጥፎ ጎኑ ወይም በስጋት
ስሜት ውስጥ ሆኜ አላየውም፤ እንደውም
ይሄ መሆኑን እንደ መልካም አጋጣሚ ነው
ያየሁት፤ ምክንያቱም የመጀመሪያውን ትልቁ
ፈተናችንን ቀድመን ማግኘታችን በጣም
ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ ነው የማስበው፡
፡ ሌላው በጣም ጥሩ ጎን ደግሞ በቀጣይ
የምናደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በሜዳችን
የምናደርግ መሆኑ የሚጠቀስ ነው፡፡ የአምናው
ሻምፒዮን ከሆነው ሰንዳውስ ጋር መገናኘታችን
ብቻውን የተለየ ስሜት እንዲሰማን ወይም
እንድንሰጋ አያደርገንም፡፡ ከሰንዳውስ ውጪ
ከኤስፔራንስም ከቪታል ጋርም ብንጫወትም
ለጨዋታዎቹ የምንሰጠው ተመሳሳይ ግምትና
ክብደት ነው፡፡ በዚህ ውድድር ደካማ ቡድን
ማግኘት አይታሰብም፡፡ ተጋጣሚያችን የአምና
ሻምፒዮን ይሁን የምንጫወተውም ከሜዳችን
ውጪ ይሁን ከእኛ የሚጠበቀው ውጤታማ
ለመሆን ጠንክሮ መስራትና መቅረብ ብቻ
ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ታሪካዊ በሆነው ከሰንዳውንስ ጋር
በምታደርጉት ጨዋታ ምን አይነት ውጤት ይዛችሁ
ለመመለስ ነው አቅዳችሁ የምትሄዱት?
ፋሲል፡- ዛሬ ላይ ሆኖ መናገር በጣም
ከባድ ነው፤ አሁን እኛ ለጊዜው ትኩረት
የምንሰጠው ከፊታችን ላሉት ሁለት
የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነው (የትናንቱን
የሐዋሳ እና የጅማ አባቡና ጨዋታ ማለቱ
ነው)፤ ይሄ እያለ ስለ ሰንዳውንስ ጨዋታ
ዛሬ ላይ ሆኖ መናገር “ችኩል” የሚል
ስያሜ ሊያሰጥ ይችላል፡፡ ያም ቢሆን ግን
ውድድር ውስጥ የገባነው የተሻለ ውጤት
ለማስመዝገብ ነው፡፡ ለተጋጣሚዎቻችን ስምና
የውጤት ታሪክ ክብር ቢኖረንም በስማቸው
ብቻ ሳናካብድና ሳንፈራ ውጤታማ ሆነን
ለመጓዝ ነው እያሰብን ያለነው፡፡ የምድብ
ውድድር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አይደለም፤
በደርሶ መልስ በሜዳህና ከሜዳህ ውጪም
እንደምትጫወተው ጨዋታ ውጤትን
ካሉኩሌት አድርገህ አይደለም የምትገባው፡
፡ የዙር ጨዋታ በመሆኑና ውጤትህ
ተደምሮ ወደ ቀጣይ ዙር የሚያሳልፍህ
በመሆኑ ጠንክሮ መጫወት የግድ ነው፡፡ ወደ
ደቡብ አፍሪካ የምንሄደው በዚህ አስተሳሰብ
ተቃኝተን ነው፡፡ እዛ የምንሄደው ደግሞ ባዶ
እጃችንን ሳይሆን ነጥብ አግኝተን መመለስን
ዋነኛ ግባችን አድርገን በመሆኑ ከደቡብ
አፍሪካ የሆነ ነጥብ ይዘን እንመለሳለን የሚል
የጠነከረ እምነት በውስጤ አለ፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31
ዓመታት በኋላ በተሳተፈበት የአፍሪካ ዋንጫ
ብዙዎችን ባስደመመ ሁኔታ ብሄራዊ ቡድኑ በደቡብ
አፍሪካ ነዋሪ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ድጋፍ
ነበረው፡፡ እናንተስ ያ የኢትዮጵያውያኑን ድጋፍ
በፕሪቶሪያው ጨዋታ ትጠብቃላችሁ?
ፋሲል፡- ወደ ደቡብ አፍሪካ የምንሄደው
የምንጫወተውም ቅዱስ ጊዮርጊስን ብቻ ወክለን
ሳይሆን ኢትዮጵያ የሚለውን ታላቅ ስምም
አንግበን በመሆኑ ኢትዮጵያን ድጋፋቸውን
ያለ ስስት እንደሚሰጡን ጥርጣሬውም
የለኝም፡፡ ከወዲሁ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ
ኢትዮጵያውያን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመደገፍ
የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን መጀመራቸውን
መስማታችን እምነት የመጣሌ ምክንያት
እንደሆነ ማረጋገጫ ነው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ
ተሞክሮ ስታየው በበርካታ ኢትዮጵያውዊያን
መደገፋችን የደጋፊ ደሃ እንዳንሆንና
በራሳችን ሜዳ የምንጫወት ያህል እንዲሰማን
ስለሚያደርግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ
ትልቅ እገዛ ስለሚያደርግልን በደቡብ አፍሪካ
የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በስቴድየም
ተገኝተው ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ጊዮርጊስ
ውጤታማ እንዲሆን በድጋፍ ያግዙናል ብዬ
አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ
ምድብ ድልድል (16 ውስጥ) ገብታችኋል ከዚህ
ሌላስ ህልም አላችሁ? ወደ ቀጣዩ ዙር (8 ውስጥ)
ለመግባት ማሰብስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ድፍረት
ይቆጠራል?
ፋሲል፡- በፍፁም አይቆጠርም፤ ህይወት
ያለ ግብ ትርጉም የለውም፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ
ህልም ወይም ራዕይ አንድ ቦታ አይቆምም
ትናንት እናስብ ነበር፤ ዛሬም ስኬትን
ማለማችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ትናንት
የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድሉ
ውስጥ መግባት አለብን ብለን አልመን
አሳክተናል፡፡ ህልማችን ግን ከዚህ ስኬት
በኋላም አይቆምም፤ 16ቱን ካሳካን በኋላ ዛሬ
ላይ ሆነን 8 ውስጥ መግባትን እያለምን ነው፡
፡ ይሄ ደግሞ የትክክለኛ አስተሳሰብ ውጤት
ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ 8 ውስጥ ለመግባት
ማሰብና መመኘትን እንደ ድፍረት መቆጠር
የለበትም፡፡ ትናንት የካፍ የቻምፒዮንስ
ሊግ ምድብ ድልድል ውስጥ መግባት ነው
ህልማችን ስንል የተጠራጠሩ ወይም እንደ
ቅዠት የቆጠሩ ነበሩ፡፡ ዛሬ ተሳክቶ ሲያዩ
ማለማችን ተገቢ እንደነበር ተረድተዋል፡
፡ አሁን 16 ውስጥ ገብተን ስምንት ውስጥ
ስለ መግባት እናልማለን፡፡ ይሄንን መመኘትና
ማለም የትክክለኛ አስተሳሰብ ውጤት ነው
እንጂ ድፍረት አይደለም ለእኔ፡፡
ሀትሪክ፡- እናንተ ግን በቻምፒዮንስ ሊግ የት
ድረስ እንጓዛለን ብላችሁ ነው የምታስቡት?
ፋሲል፡- የዚህ ጥያቄ መልስም ከላይ ካለው
ጋር ተመሳሳይ ነው፤ የመጀመሪያው ዕቅዳችን
16 ውስጥ መግባት ነበር፡፡ ያ ሲሳካ ረክተን
መቀመጥ ሳይሆን ስምንት ውስጥ ስለመግባት
እያለምን ነው፤ ማለም ብቻ ሳይሆን በስራ
እንደሚመጣም አውቀን ጠንክረን እየሰራን
ነው፡፡ 16 ውስጥም ሆነ ስምንት ውስጥ
መግባት የመጨረሻው ግባችን አይደለም፤
የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችና የስራ አመራር
ቦርድ ከዚህ በፊት እንደሚሉትና አቅደው
እንደሚንቀሳቀሱት አፍሪካ ውስጥ ካሉት
ጠንካራ ቡድኖች አንዱ ሆኖ የማየት ምኞት
አላቸው፡፡ 16 ወይም ስምንት ውስጥ ከዚህም
ከፍ ሲል አራት ውስጥ መግባትና ዋንጫ
ማግኘት ብቻውን አይደለም ግባችን፡፡ ቅዱስ
ጊዮርጊስን ከአህጉሪቱ ሃያላን ክለቦች አንዱ
አድርጎ የማሰለፍ ትልቅ ራዕይ ነው ያለን፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በኤስፔራንስ፣ በዛማሌክ ደረጃ
ማስቀመጥና ከአፍሪካ ሃያላን ክለቦች አንዱ
የማድረግ ህልም ካለን በቻምፒዮንስ ሊግ
ውድድር በተደጋጋሚ መሳተፍና ውጤታማ
መሆን ይጠበቅብናል፡፡ የክለባችን ህልምና
ራዕይ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ካፍ አዲስ ባወጣው ፎርማት መሰረት
ነው ዘንድሮ በካፍ የቻምፒዮንስ ሊግ 16 ቡድኖች
መሳተፍ የጀመሩት፤ ከዚህ አንፃር የውድድሩ
ፎርማት መለወጥ ቅዱስ ጊዮርጊስን የዚህ ዕድል
ባለቤት አድርጎታል ብሎ ማሰብ ይቻላል?
ፋሲል፡-ቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ውስጥ
የገባው በውድድሩ ፎርማት ብቻ ሳይሆን
ሊዮፓርድስን የሚያክል የአህጉሪቱ ታላቅ
ቡድንን በውጤትም በጨዋታም በልጦ ነው፡፡
ወደ 16ቱ የምድብ ድልድል ውስጥ የገባው
ያለ ውድድር በቀጥታ ሳይሆን ተጋጣሚያችንን
በውጤትም በጨዋታም በልጠን አሳምነን
ከመሆኑ አንፃር ፎርማቱ በራሱ ረድቶናል
ብዬ አላስብም፡፡ የፎርማት ለውጡ ለእኛ ብቻ
አይደለም ለኮንጎው ሊዮፓርድስም ጭምር
ነው፡፡ ሊዮፓርድስ ግን በእኛ ስለተሸነፈ
የፎርማት ለውጡ አልረዳውም፤ የፎርማት
ለውጡ ብቻውን ሳይሆን ማሸነፋችን ነው
የዚህ ዕድል ባለቤት ያደረገን፡፡
ሀትሪክ፡- በአገር ቤት የፕሪምየር ሊግ
ዋንጫን ለማንሳት ብርቱ ትንቅንቅ አለባችሁ፤
በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ የሞት ምድብ ውስጥ
ተደልድላችሁ ውጤታማ ለመሆን ትሮጣላችሁ፤
ይሄ ነገር ቡድኑን በሁለት ሃሳብ ውስጥ የከፈለው
አይመስልህም?
ፋሲል፡- ቀጣዩ ወር ለእኛ አስቸጋሪ ጊዜ
ነው፡፡ ወሳኝና ፈታኝ ውድድሮች ከፊታችን
ቆመዋል፡፡ እነዚህን ውድድሮች በብቃት
ለማለፍ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ቅዱስ
ጊዮርጊስን አንድ ቦታ ማስቀመጥ ወይም
ተለቅ ያለ ቦታ ማድረስ ከፈለግን ትላልቅ
ቡድኖች በሚያልፉበት መንገድ እኛም ማለፍ
አለብን፡፡ እንደ እዚህ አይነት የውድድር
ጫናዎችና ፈተናዎች የአንድ ትልቅ ቡድን
መለኪያም እንደሆነ አድርጌ ነው የምወሰደው፡
፡ በዚህን መሰል መንገድ አልፈህ ፈተናን
በብቃት መወጣት የግድ ነው፡፡ ወደ ትልቅ
ደረጃ ስትሸጋገር በአገር ውስጥም በውጪም
እንደዚህ አይነት ፈተናዎች ይጠብቁሃል፡፡
የውጪውን አነሳህ ካላልከኝ በስተቀር ለምሳሌ
ሪያል ማድሪድን ብትወስድ በዓመት ውስጥ
በአገር ውስጥ የላ ሊጋ ሻምፒዮን ለመሆን፣
የንጉሱን ዋንጫ ለማንሳት እና በአህጉር
ደረጃ ደግሞ የቻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ
ይጠብቀዋል፡፡ በዚህን መሰሉ ውድድር
የጨዋታ መደራረብና የውድድሮች ፈታኝነት
ያጋጥማል፡፡ ፕሬዠሩም ከባድ ነው፤ የቱን
አንስተህ የቱን እንደምትጥል ትጨነቃለህ፤
በመንታ መንገድ ውስጥም ትወድቃለህ፤ ግን
አንድ ማወቅ ያለብን ነገር የፈለገ የጨዋታ
መደራረብ ይግጠመን ቅዱስ ጊዮርጊስን ትልቅ
ማድረግ ከሆነ ሃሳባችንና ግባችን በዚህ
ውስጥ ተፈትነን ፈተናውን ቻሌንጅ አድርገን
(ተቋቁመን) ማለፍ ግን የግድ መሆኑን
አውቀን ለፍልሚያው መዘጋጀት አማራጭ
የሚቀርብለት አይሆንም፡፡
ሀትሪክ፡- የአገር ውስጥ ሻምፒዮን መሆን
ወይስ በቻምፒዮንስ ሊግ ብዙ ርቀት መጓዝ?
በዋናነት የምታስቀምጠው ወይም የምትመርጡት
የትኛውን ነው?
ፋሲል፡– ሁለቱን ማነፃፀር ለእኔ በጣም
ይከብደኛል፡፡ ሁለቱም ውድድሮች የየራሳቸው
ታሪክና ትልቅ ትርጉምም አላቸው፡፡ በሁለቱም
መሳተፍና ማሸነፍ የሚያጎናፅፈው ትልቅ
ክብር አለ፡፡ በአጭሩ ሁለቱም የየራሳቸውት
ትልቅ ታሪክና ክብር ያላቸው ናቸው፡፡ የአፍሪካ
ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የአህጉሪቱ ትልቁ
የክለቦች ውድድር እንደሆነ ይታወቃል፤ ነገር
ግን በዚህ ውድድር ውስጥ ስለገባን ብቻ
የአገራችንን ትልቁን ውድድር ዝቅ አድርገን
አናይም፡፡ በየትኛውም መስፈርት የአገራችንን
ሊግ ዝቅ እናከብራለን፡፡ የሊጉን ዋንጫ
በአንፀባራቂ ድል በመዝጋት የአገሪቱ ክለቦች
የበላይ መሆናችንን አስጠብቀን መጓዝም
እንፈልጋለን፡፡ ለአራት ተከታታይ አመታት
የሊጉን ዋንጫ በማንሳት አዲስ ታሪክ የማፃፍ፣
ለደጋፊዎቻችንም የለመዱትን ድል ማጎናፀፍ
ስለምንፈለግ ሊጉን አሳንሰን የምንመለከትበት
ምክንያት አይኖርም፡፡ በመጪው አመትም
የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ትኬትን ለመቁረጥ
የሊጉን ዋንጫ በበላይነት ማጠናቀቅ ግድ
በመሆኑ ሊጋችንን አሳንሰን አንመለከትም፡
፡ የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው በራሱ
ሌላ የውድድር ገፅታ ወይም መልክ አለው፡፡
ቻምፒዮንስ ሊጉ ልንደርሰበት የምንፈልገው፤
ስንመኘው ስንጓጓለት የነበረ የአህገሪቱ ትልቁ
ውድድር በመሆኑ ለእሱም የተለየ ትኩረት
ሰጥተን ነው መሳተፍ የምንፈልገው፡፡ ከእነዚህ
ተጨባጭ ምክንያቶች በመነሳሳት ሁለቱን
ውድድሮች ነጣጥለን የምናይበት ምክንያት
የለም፡፡ አንዱን ከአንዱም አናስበልጥም፡
ሀትሪክ፡- የሁለቱ ውድድሮች መደራረብ
ስጋት አልሆነባችሁም? ተጨዋቾችን እንድትሰስቱስ
አያስገድዳችሁም? ማለትም ለአገር ውስጥ
ተጠባባቂዎችን፤ ለኢንተናሽናል ጨዋታዎች
ዋናዎቹን ተሰላፊዎች እንጠቀም ወደሚል ሀሳብ
አይወስዳችሁም?
ፋሲል፡- የእኛ ተጨዋቾች ካላቸው
ልምድ፣ የአገራችን እግር ኳስ ካለበት ደረጃ
አንፃር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የአገር
ውስጥም የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድርን
ማድረግ ፈተናውን ቀላል አያደርገውም፡፡
ለዚህ መሰሉ ውድድር እንግዳ በመሆናችን
ለእኛም ለተጨዋቾቻችንም ነገሮች አስቸጋሪ
እንደሚሆኑብን እናውቃለን፡፡ ያም ቢሆን
ግን ለአገር ውስጥ ተጠበባቂ ተጨዋቾችንን
ለኢንተርናሽናሉ ዋናዎቹን ብለን የመደብነው
ነገር የለም፡፡ ሁሉንም እንደ የአስፈላጊነታቸው
እንደ የጨዋታው ነው የምንጠቀመው፡
፡ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ሁለቱም
ውድድሮች ለእኛ በጣም አስፈላጊዎች ናቸው፡
፡ አንዱን ከአንዱ ስለማናበላልጥ ለሊጉ
ተጠባባቂዎችን ለቻምፒዮንስ ሊጉ ዋናዎቹን
ብለን የምንደለድለው ነገር የለም፡፡
ሀትሪክ፡- የተጨዋቾቹ ልብስ የት ነው ያለው
በአገር ውስጥ? በውጪ ታሪክ ለመስራት?
ፋሲል፡- በጣም የሚገርምህ ሁለቱም
ጋር ያለው ስሜታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ
የምድብ ድልድል ውስጥ መግባታቸውና
በእነሱ ውጤትና ድል የአገሪቱ ስም በዚህ
መልኩ መነሳቱ፤ እንዲሁም በእነሱ ምክንያት
በአህጉሪቱ እግር ኳስ ትልልቅ ስም ያላቸው
ክለቦች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው
ከፉክክሩና ከውጤቱ ባለፈ ትልቅ ክብር
እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ ብቻ
ሳይገደቡ በታሪክ ላይ ታሪክ ማፃፍም
ይፈልጋሉ፡፡ ከዚህ መነሻነት በቻምፒዮንስ ሊግ
ሌላ አዲስ ታሪክ የማፃፍ ህልም እያለሙ ነው፡
፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ማሸነፍ ለእነሱ
ሁሉም ነገራቸው በመሆኑ በመሪነታችን
ለመጨረስ ትልቅ ጉጉት አላቸው፡፡ የሀገሪቱን
ሊግ ማሸነፍ፤ ሻምፒዮን መሆን ምን ማለት
እንደሆነ፤ ምን ይዞላቸው እንደሚመጣ በደንብ
ያውቁታል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ከላይ ስናወራው
እንደ ነበረው አይነት ስሜት በሁሉም
ተጨዋቾች ላይ አለ ብዬ ነው የማስበው፡፡
ሌላው ደግሞ አንድ መርሳትና ማወቅ ያለብን
ነገር አለ፡፡
ሀትሪክ፡- ምን…?
ፋሲል፡- ብዙዎቹ የክለባችን ተጨዋቾች
በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በኢትዮጵያ እግር
ኳስ ላይ በተሰሩ ወይም በተመዘገቡ የውጤት
ታሪኮች ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡ ያም ቢሆን
ግን አንድ ጎዶሎ ነገር አላቸው፡፡ በብሄራዊ
ቡድን ያላቸውን ታሪክ በክለባቸውም መድገም
ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ አዳነ ግርማን እና
ደጉ ደበበን ውሰድ፡፡ ብሄራዊ ቡድናችንን
ወደ አፍሪካ ዋንጫ በመመለስ አዲስ ታሪክ
አፅፈዋል፤ በኮንፌደሬሽን ካፕም ተሳትፈዋል፤
አሁን ደግሞ በቻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ
እድል ማግኘታቸው የእግር ኳስ ህይወታቸውን
የተሟላ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በላይ ከተራመዱ
ደግሞ የእግር ኳስ ህይወታቸው ይበልጥ
እንደሚያሸበርቅ ስለሚያወቁ ይሄ ውድድር
ለእነሱ የተለየ ትርጉም አለው፡፡ ይሄንን
ወርቃማ እድል የሚያገኙ በጣም የተወሰኑ
ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ይሄንን የበለጠ ከፍ
ለማድረግ ዝግጁዎችም ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በአገር ውስጥ
ውድድር አሁንም በ49 ነጥብ መሪ ቢሆንም ዘንድሮ
ወጥ አቋም አላሳየም፤ ባልተለመደ ሁኔታ ዘንድሮ
የተሸነፈባቸውና ነጥብ የተጋራባቸው አጋጣሚዎችን
በማየት በቻምፒዮንስ ሊግ ዘመቻችሁ ላይ ስጋት
ያላቸው አሉ፡፡ አንተ በዚህ ላይ ምን ትላለህ?
ፋሲል፡– እውነት ነው ይሄ የሚካድም
አይደለም፡፡ በቡድናችን ላይ በአንዳንድ
ጨዋታዎች ላይ ወጥ አቋም ያለማሳየት
የመዋዥቅ ሁኔታ ታይቷል፤ ምንም እንኳን
በጊዜ ሂደት እያረምን ለመሄድ ብንሞክርም፡
፡ ለዚህ ግን ከራሳችን ድክመትና ስህተት
በተጨማሪ ሌሎች ውጪያዊ ችግሮች
እንዳለብን ግን መካድ አልፈልግም፡፡ ከዚህ
ውስጥ በዋናነት ከሌሎች ጊዜያት በተለየ
ጉዳት የቡድናችንን አቋም ተፈታትኖታል፡
፡ ከዚህ በተጨማሪ ምክንያት ለመደርደር
ሳይሆን ሌሎች ክለቦች ያገኙትን የማገገሚያ
(ሪከቨር የማደረጊያ) ጊዜ እኛ አግኝተናል ብዬ
ለመናገር ይቸግረኛል፡፡ አራት የቻምፒዮንስ
ሊግ ጨዋታ ከሌሎች ክለቦች በተለየ
መልኩ እኛ ተጫውተናል፡፡ የጨዋታው
ክብደት፣ ረጅም ጉዞ በመኖሩ የተፈጠረው
ውጣ ውረድና ድካም ችግሮቻችንን ከፍ
ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሌሎች ክለቦች
ከእኛ የተሻለ አድቫንቴጅ አግኘተዋል፡፡
እነዚህ ችግሮች ተደራርበውብንም ምክንያት
ሳንደረድር፣ ችግሮቻችንን ወደሌላ ሳንገፋ፣
በማንም ሳናሳብብ በዚህ ውስጥ ሆነን ጥሩ
በተጫወትንባቸው ጥንካሬያችንን ይዘን
በመቀጠል፤ በደከምንባቸው ድክመታችንን
ነቅሰን እያወጣንና እያረምን እስከ አሁን
መሪነታችንን ላለመልቀቅ እየታገልን ነው፡፡
ይሄ ደግሞ የዋንጫውን እጀታ ከፍ አድርጎ
እንከማንሳትና እስከ መጨረሻው ጨዋታ
ይቀጥላል፡፡
ሀትሪክ፡- የዘንድሮው ፉክክር በአገር ቤት
ከሌላው ጊዜ በተለየ ጠንከር ብሏል፡፡ ይሄ መሆኑ
ዋንጫውን ለማንሳት ፈተና አይሆንም?
ፋሲል፡- እውነት ነው የዘንድሮው ፉክክር
ከሌላው ገዜ በተለየ መልኩ የጠነከረ ነው፤
የነጥብ ፉክክራችንም በጣም የተቀራረበ ነው፡
፡ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት እንደዚህ
አይነት ጨዋታዎችን ሲቀሩን ከሌሎች ክለቦች
ጋር ያለን የነጥብ ልዩነት በጣም ሰፊ ነበር፡፡ ብዙ
ቀሪ ግጥሚያዎች እያሉን ሻምፒዮንነታችን
ቀድመን የምናውጅበት ሁኔታዎች ሁሉ
ነበሩ፤ አሁን ግን በጣም ተቀራራቢ ነጥብ ነው
ያለን፡፡ አንድ ጨዋታ ብዙ ነገር ይቀይራል፡፡
የፉክክሩ መጠንከር ለአፍታም እንዳናንቀላፋ
አድርጎናል፡፡ እያንዳንዱን ጨዋታ በማሸነፍ
ወደ ተለመደው ድላችን ለመንደርደር
የማንከፍለው መስዋዕትነትም አይኖርም፡፡
ሀትሪክ፡- ዘንድሮ የተለየ ሆኖ ስለቀረበው
የቅድስ ጊዮርጊስ ደጋፊስ ምን ታዝበሃል?
ፋሲል፡- ምናልባት በ1987 እና 88 ከቢ
ወደ ዋናው ቡድን ባደግኩበት ወቅት የቅዱስ
ጊዮርጊስ ደጋፊ እንደዚህ አይነት ድባብ ነበረው፡
፡ በጣም ብዙ ደጋፊ ወደ ሜዳ ይመጣ ነበር፡
፡ ታስታውስ እንደሆነ የአዲስ አበባ ስቴድየም
ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ሜዳ
ውስጥ የምታየው የቅዱስ ጊዮርጊስን ደጋፊ
ነበር፡፡ ያንን ዘመን የሚያስታውስ ክስተት
ነው አሁን የተፈጠረው፡፡ የደጋፊዎቻችን
ሁኔታ ወደዚያ ዘመን በትዝታ መልሶኛል፡
፡ በእውነት ለመናገር የእኛ ደጋፊዎች
ስቴድየም ውስጥ በሚያሳዩት ነገር ኮርቻለሁ፡
፡ አሁን አሁን ደጋፊዎቻችን እንደ ቡድናችን
ተጨዋቾች ያህል እየተሰማን ነው፡፡ በዚያ
ላይ ድጋፋቸው በዕውቀትና ፍፁም ጨዋነት
በተሞላበት ሁኔታ ዘመናዊ የድጋፍ አሰጣጥን
መከተላቸው የበለጠ እንድታከብራቸው
ያደርግሃል፡፡ እኔ አንድ ለየት ያለ የራሴ የሆነ
እምነት አለኝ፤ ስቴድየሞች ለሰዎች የመዝናኛ
ቦታዎች መሆን አለባቸው የሚል፡፡ ህፃናቶች፣
ሴቶች፣ የተከበሩ ሰዎች በነፃነት ወደ ስቴድየም
ሊመጡና ሊደሰቱ ይገባል ብዬ የማስብ ሰው
ነኝ፡፡ ይሄ የእኔ እምነት ብቻ ሳይሀን ፍላጎቴም
ነው፡፡ የቅድስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ግን ይሄንን
በስቴድየም ውስጥ መፍጠር ችለዋል ብዬ
አስባለሁ፡፡ በዚህም በጣም አከብራቸዋለሁ፡
፡ ሁልጊዜም እነሱን በደስታ ባህር ውስጥ
ለማስመጥና የለመዱትን ድል ለማስጨበጥ
የምንችለውን ሁሉ እንደምናደርግና በዚህ
እንደምንክሳቸው ነው ማረጋገጥ የምፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ተካልኝ አዲስ ታሪክ ያፃፈው
የዚህ ቡድን አካል በመሆኑ በውስጡ የተፈጠረው
ስሜት ምንድነው የሚለው ጥያቄ የእኔና የአንተ
መለያያ ቢሆንስ?
ፋሲል፡- አሰልጣኝነት ስራዬ ነው፡፡
ከስራዬ ባለፈ ግን ጊዮርጊስ ተወልጄ ያደኩ
ያህል የሚሰማኝና ሁልጊዜም ስለ ቅዱስ
ጊዮርጊስ ታሪክ ሲወራ ወይም ሲፃፍ ፋሲል
አሻራው አንድ ቦታ እንዲኖር አጥብቆ
ይፈልጋል፡፡ በተጨዋችነት ዘመኔ ለዚህ ታላቅ
ክለብ ታላቅነት የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ
ብዬ አስባለሁና ፋሲልን ብትፈልገው
የሆነ ቦታ ታገኘዋለህ፡፡ በአሰልጣኝነቴ
ደግሞ ያንን መድገም ትልቁ ምኞቴ ነበርና
በተለይ በኢንተርናሽናል ውድድር ክለቡ
በሚያስመዘግበው ደማቅ ታሪቅ ላይ የእኔን
ትንሽዬ አሻራ እንድትኖር እፈልግ ነበር፡፡ ያ
ምኞቴ በመጠኑም ቢሆን እየተሳካ እንደሆነ
ይሰማኛል፡፡ ከዚህ በፊት ያልነበሩ ታሪኮች
በእኛ የአሰልጣኝነት ዘመን ተሳክተው ማየቴ
ህልሜን መኖር የጀመርኩ ያህል እንዲሰማኝ
እያደረገ በመሆኑ ደስታ ብቻ ሳይሆን ኩራትም
ተሰምቶኛል፡፡ ከዚህ በፊት በኮንፌደሬሽን ካፕ
ተሳትፈናል፡፡ አሁን ደግሞ በቻምፒዮንስ ሊግ
ምድብ ድልድል ውስጥ በመግባት አዲስ ታሪክ
አፅፈናል፡፡ በአጠቃላይ ወደፊት እኔ ለቅዱስ
ጊዮርጊስ ምን ሰራሁለት ብዬ የሚወራ ነገር ስላገኘሁ የተለየ ኩራት በውስጤ ፈጥሯል፡፡