የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና
ከወራት በፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት
ሲጠናቀቅ፤ በእዚያን ዕለትም አሸናፊው
ቡድን ከዕለቱ የክብር እንግዳ ዋንጫውን
ሊቀበል ችሏል፤ ሽልማቱ በተሰጠበት
ቀንም በሊጉ የውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ
ጊዜ ለኮከብ ተጨዋች፣ ለኮከብ አሰልጣኝ፣
ለኮከብ ግብ አግቢ እና ለኮከብ ግብ
ጠባቂም ሽልማት ሳይሰጥ ቀርቷል፤ ያን
ዕለት ሽልማት አለመሰጠቱ ለብዙዎቹ
አግራሞትን ሊፈጥርባቸው ቢችልም
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን
የሊጉን የኮከቦች ሽልማት ከሌላው ጊዜ
በተለየ፣ በአማረና በደመቀ መልኩ ነሐሴ
28 ቀን በሚሊኒየም አዳራሽ ለመስጠት
ቀጠሮን ይዟል፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ፌዴሬሽን የዘንድሮ የውድድር ዘመን
ኮከቦቹን በነሐሴ 28 ቀን የሚሸልመው
በዓመቱ ውስጥ ሲያወዳድራቸው ለነበሩት
አጠቃላይ ውድድሮቹ ሲሆን ከእነዚህም
ሽልማቶች ውስጥ ከሁሉም በላይ ከወዲሁ
ትኩረትን እየሳበ ያለው የኢትዮጵያ
ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን
ኮከብ ተጨዋች ማን ይሆናል በሚለው
ላይ ነው፤ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
የዘንድሮ የውድድር ዘመን ኮከብ ተጨዋች
እንደዚሁም ደግሞ ኮከብ ግብ ጠባቂ ማን
መሆን አለበትና እነማንስ ለመጨረሻዎቹ
እጩ ተፎካካሪዎች መሆን አለባቸው
በሚለው ጉዳይ ዙሪያ የስፖርት ቤተሰቡ
እስካሁን ድረስ ሲነጋገርበት የቆየ ጉዳይ
ሲሆን በእዚሁ የኮከብ ተጨዋችነት ምርጫ
ላይም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በኮከብ
ግብ አግቢነት ያጠናቀቀው የደደቢቱ የአጥቂ
ስፍራ ተጨዋች ጌታነህ ከበደም በምርጫው
ላይ የእሱና የቅዱስ ጊዮርጊሱ የአጥቂ
ስፍራ ተጨዋች የሆነው ሳላህዲን ሰይድ
ለመጨረሻዎቹ እጩ ሆነው አለመቅረባቸው
አግራሞትን እንደፈጠረበትም ተናግሯል፤
ተጨዋቹ ምርጫውን ያከናወነው አካልስ
ማነውም ብሏል?
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ
ተጨዋችነት ምርጫ ላይ ብዙ ጊዜ
በትክክል ለተመራጩ ተጨዋች የተሰጠበት
ጊዜ እንዳለ ሁሉ በምርጫው ላይም
ያወዛገበበት ጊዜ እንደነበር የሚታወስ
ሲሆን የዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ
ደግሞ በኮከብ ተጨዋችነት ምርጫው
ላይ ለመጨረሻዎቹ እጩ ተመራጭነት
መካተት ያላባቸው ተጨዋቾች
አለመመረጣቸውም ብዙዎቹን እያስገረመም
ይገኛል፤ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ
ተጨዋች ሆኖ ለመመረጥ ለመጨረሻዎቹ
እጩነት የቀረቡት ሶስቱ ተጨዋቾች የቅዱስ
ጊዮርጊሶቹ አስቻለው ታመነና ምንተስኖት
አዳነ እንደዚሁም ደግሞ የሲዳማ ቡናው
ሙሉዓለም መስፍን ዴኮ ሲሆኑ ምርጫው
ላይ እኛም መካተት ነበረብን በሚልም
በእጩነት መመረጥ ካልቻሉት ተጨዋቾች
ውስጥ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ
አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው የደደቢቱ የአጥቂ
ስፍራ ተጨዋች ጌታነህ ከበደም አስተያየቱን
ለዝግጅት ክፍላችን ሊሰጥ ችሏል፤ ለጌታነህ
በምርጫው ዙሪያና ሌሎችን ተጨማሪ
ጥያቄዎችንም አንስተንለት ምላሹን
እንደሚከተለው ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
የኮከብ ተጨዋች፣ እንደዚሁም ደግሞ የኮከብ
ግብ አግቢ በመባል ሽልማቱን በተደጋጋሚ
አግኝተሃል፤ የተሸላሚነቱ ስሜት ምን
ይመስላል?
ጌታነህ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ውስጥ መጫወት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ
የሊጉን የኮከብ ተጨዋችነትና የኮከብ ግብ
አግቢነት ሽልማትን በተደጋጋሚ ለማግኘት
በመቻሌ በውስጤ የተፈጠረብኝ የደስታ
ስሜት ከፍ ያለ ነው፤ እነዚህን ሽልማቶችም
ለደቡብ ፖሊስና ለደደቢት ስጫወት ያገኘሁት
ደግሞ ገና በወጣትነት ዕድሜዬም ላይ ስለሆነ
ያ ተሸላሚነቴ የበለጠ ሊያስደስተኝ ችሏል፤
ሽልማቱም ወደፊት ብዙ ስራዎችንም
እንድሰራ የሚያበረታታኝ ነውና አሁንም
ድረስ ጥሩ የሆነው የተሸላሚነቱ ስሜት
አብሮኝ በውስጤም ነው ያለው፡፡
ሀትሪክ፡- ለሁለት ጊዜያት ያህል
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ ተጨዋች
ተብለህ ስትሸለም ኮከብነቱን ጠብቀህ ነበር?
ኮከብ ግብ አግቢ እንደምትሆንስ አስቀድመህ
ትገምት ነበር?
ጌታነህ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ላይ
ለደቡብ ፖሊስም ሆነ ለደደቢት ክለብ
በምጫወትበት ወቅት የኮከብ ግብ አግቢነቱን
ሽልማት ለማግኘት እንደምችል በተለይ
የደደቢት ክለብ ውስጥ እያለው ለራሴ በከፍተኛ
ሁኔታ እገምት ነበር፤ ያንን ግምቴንም ነው
በደደቢት ተጨዋችነቴ በተደጋጋሚ ላሳካው
የቻልኩት፤ ኮከብ በመባሌም ለመደሰት
ችያለው፤ የደቡብ ፖሊስ ተጨዋች እያለው
ደግሞ ከፍተኛ ግቦችን ካስቆጠሩት የሊጉ
ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ እኔ ነበርኩኝ፤
ያኔ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የኮከብ ግብ
አግቢነቱ ሊሳካልኝ ይችላል አይችልም
በሚለው ስሜት ውስጥም ላይ እገኝ ነበር
በጊዜው ኮከብ ግብ አግቢነቱ ባይሳካልኝም
ኮከብ ተጨዋችነቱ ግን ሊሳካልኝ ችሏል፤
በወቅቱ የኮከብ ተጨዋችነቱን ሽልማት
ያገኘሁት ለደቡብ ፖሊስ ምርጥ የሚባል
አቋሜን ላሳይ በመቻሌ ነበር፤ ኮከብነቱን
ግን ብዙ ጊዜ ሻምፒዮና ከሚሆኑ ቡድኖች
ስለሚሸለም በፍፁም አልጠበቅኩም ነበርና
ያ ሽልማት ለእኔ የመጀመሪያዬም ስለነበር
መቼም የማልረሳው ነውና እኔን በጣም
ያበረታታኝም ነበር፤ በደደቢት ቡድን
ተጨዋችነቴ ያሳካሁትን የኮከብ ተጨዋችነት
ሽልማት ግን አስቀድሜም የጠበቅኩት
ነበርና ያንን እውን ላደርገው ችያለው፡፡
ሀትሪክ፡- ለደደቢት ክለብ ባስቆጠርካቸው
በርካታ ግቦች የዘንድሮ የውድድር ዘመን
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ
አግቢ ሆነህ ለማጠናቀቅ ችለሃል፤ የኮከብ
ተጨዋቾች የመጨረሻ እጩዎች ውስጥ
ግን ስምህ አልተካተተም ስምህ መኖሩን
ትጠብቅ ነበር…
ጌታነህ፡- አዎን፤ የኢትዮጵያ
ፕሪምየር ሊግ ላይ የኮከብ ተጨዋች
ሽልማት ብዙ ጊዜ ሻምፒዮና ከሚሆነው
ቡድን እንደሚሰጥ ባውቅም የእዚህ ዓመት
የውድድር ተሳትፎ ላይ ለክለቤ ካበረከትኩት
ጥሩ ግልጋሎት አንፃር እኔን ለምን ከእጩ
ተመራጭ ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ ሆኜ
ለምን ራሴን አልጠብቅም፤ የኢትዮጵያ
ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ሻምፒዮና ላይ
ለክለቤ ደደቢት 25 ግቦችን ከማስቆጠር
ባሻገር ቡድኑን ለሁለተኛ ደረጃ እንዲበቃም
የበኩሌን አስተዋፅኦ አበርክቻለው፤ የሊጉ
ኮከብ ግብ አግቢም መሆን ችያለው፤ ያን
ስታስብ ለኮከብ ተጨዋችነቱ የመጨረሻ
የእጩ ዝርዝር ውስጥ እንዴት ነው ስሜ
የማይኖረው፤ ከእዚያ ውጪ ምን የእኔ ብቻ
የቅዱስ ጊዮርጊሱም ስኬታማ ተጨዋች
ሳላህዲን ሰይድም እኮ እጩ ውስጥ ስሙ
ሳይገባ እንደእኔ ሁሉ በምርጫው ሳይካተት
ቀርቷል፤ ሳላህዲን በዘንድሮ የውድድር
ዘመን ለቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ግቦችን
ከማስቆጠር ባሻገር ወሳኝ ወሳኝ የሆኑ የድል
ግቦችን አስቆጥሯል፤ ከእዚያ ውጪም
በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ለቡድኑ
ተደጋጋሚ ግቦችን በማስቆጠርም ቡድኑን
ለውጤት አብቅቷል፤ የእሱም የኮከብ
ተጨዋችነት እጩ ምርጫ ውስጥ እንደእኔ
ስሙ አለመኖሩ ይገርማል፤ ምርጫውን
ያከናወነው አካልስ ማን ነው? በምን
መመዘኛስ ነው ምርጫው የተከናወነው?
በእውነቱ መራጩ አካል በጣም ያሳዝናል፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ላይ አስቻለው ታመነ፣ ምንተስኖት አዳነና
ሙሉዓለም መስፍን ለኮከብ ተጨዋችነቱ
ተሸላሚነት የመጨረሻ እጩዎች ሆነው
ቀርበዋል፤ ሌሎች እነማን መካተት
ነበረባቸው…የዘንድሮ ኮከብ ተጨዋችስ
በምን መስፈርት ሊመረጥስ ይገባዋል?
ጌታነህ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
የዘንድሮ የኮከብ ተጨዋችነት ምርጫ
እጩ ውስጥ ለክለባቸው ጥሩ አስተዋፅኦ
እንዳበረከቱት እንደእነ አስቻለው ታመነ፣
ምንተስኖት አዳነና ሙሉዓለም መስፍን
ሁሉ እኔና ሳላህዲን ሰይድም ከላይ
እንደገለፅኩት ሁሉ በምርጫው እጩ ውስጥ
መካተት የነበረብን ነን፤ እኛን በምርጫው
አለማካተቱም ፌዴሬሽኑ ስህተትን ሊሰራም
ችሏል፤ የኮከብ ተጨዋች የዘንድሮ
ምርጫን በተመለከተ አሁንም ፌዴሬሽኑ
ስህተትን እንዳይሰራ ሊጠነቀቅ ይገባዋል፤
የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የዘንድሮን የኮከብ
ተጨዋች ምርጫ የሚያከናውነው በራሱና
ከህዝብ በሚሰበሰብ የኤስ ኤም ኤስ ድምፅ
ቢሆንም ምርጫው በፍትህ ሊከናወን
ይገባል፤ የመራጩ አካልም ተጨዋቹ
በውድድር ዘመኑ ለክለቡ ያደረጋቸውንና
የተመለከታቸውን ግጥሚያዎችም ተንተርሶ
ምርጫውን ሊያከናውንም ይገባልና የእኔ
ምኞት ምርጫው ፍትሃዊ እንዲሆን ነው፡፡