የፌደሬሽኑ መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ በአንድ ተጠባቂ የቱኒዝያ ሊግ ኢትዮጵያውያን ዳኞች ጨዋታውን እንዲመሩ የቱኒዝያ እግርኳስ ፌደሬሽን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ደብዳቤ መላኩን ጠቁሟል። በአፍሪካ እግር ኳስ በጠንካራ ተፎካካሪነታቸው ከሚጠቀሱት ክለቦች መካከል የቱኒዝያ ክለቦች ይጠቀሳሉ። የቱኒዚያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በቱኒዝያ ሊግ ጥር 6/2012 የሚደረገውን ተጠባቂውን የኢስፔራንስ ዲቱኒዝ እና ኤቷል ዶሳሂል ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባአምላክ ተሰማ እና ሁለት ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኞች እንዲመድብላቸው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በላኩት የትብብር ደብዳቤ ጠይቋል። በቱኒዝያ ሊግ በ2019/20 የውድድር ዘመን ኤስፒራንስ ዲ ቱኒዝ በ25 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ኤቷል ዶሳሂል ደግሞ በ23 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።