ለካሜሮኑ 2021 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኮትዲቯር፣ ኒጀርና ማዳጋስካር ጋር የተመደበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከማዳጋስካር ጋር ብሔራዊ ቡድን ጋር በአንታናናሪቮ ያደርጋል፡፡ ሃያ ተጫዋቾችን በመያዝ ወደሥፍራው ያቀናው የአብርሃም መብራህቱ ቡድኑ ወደአንታናናሪቮ የተጓዘው ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ሲሆን ትናንት አርብ ምሽት የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ ጨዋታውን በሚያደርግበት ማሃማሲያ ስታዲየም አድርጓል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡድኑ ጋር ምንም የፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አብሮ ያልተጓዘ ሲሆን የፌዴሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርና የብሔራዊ ቡድኖች አስተባባሪ ከቡድኑ ጋር አብረው ተጉዘዋል፡፡
ከብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምድ በኋላ ስለጨዋታውና ስለቡድናቸው የተናገሩት ኢንስትራክተር አብርሃም ቡድናቸው የማሸነፍ ዓላማ ብቻ ይዞ ወደማዳጋስካር እንደመጣ ገልጸው ለማሸነፍ የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ እና ይህን ለማድረግ ደግሞ አቅም ያለው ቡድን መያዛቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሶሥት በውጭ ሃገር የሚጫወቱ ልጆችን በያዘው የአብርሃም ቡድን ምንም ዓይነት የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ስታዲየሞች ሁሉ ለአቅመ-ዓለም ዓቀፍ ጨዋታ አይበቃም ክስ ከካፍ የሚቀርብበት የማሃማሲያ ስታዲየም 22 ሺህ ሰው ብቻ ይይዛል፤ ለዚህ ጨዋታ ትኬቶች በሙሉ ረቡዕ ዕለት ተሽጠው ያለቁ ሲሆን ሰሞናዊው ዝናባማ አየር ጨዋታውን እንዳያስተጓጉለው ተፈርቷል፡፡ ከሶስት ቀናት በፊት የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ሜዳውን አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር የተነገረ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ከጣለ ጨዋታውን ለሁለቱም ቡድኖች አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
እንደኢትዮጵያ ሁሉ ትናንት የመጨረሻ ልምምዳቸውን ያደረጉት የማዳጋስካር ቡድን አባላት ማምሻውንም በሃገሪቱ ፕሬዝዳንት በቤተመንግስት የእራት ግብዣ ተደርጎላቸዋል፡፡ የዛሬውን ጨዋታም አስመልክቶ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ፈረንሳያዊው ኒኮላ ዲዩፕዊ እና የቡድኑ አምበል አቤል አኒሴ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ቡድናቸው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አሰልጣኝ ኒኮላ ዛሬ በማይሰለፉት በተከላካዩ ባፓሲ እና በማርኮ ያማሃሪታ ቦታ የሚተኩ ልጆች በሚገባ ማዘጋጀታቸውንና ለጨዋታው በደንብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
አሰልጣኝ ኒኮላ እንዳሉት በፈረንሳይ ለሁለተኛ ዲቪዚዮኑ ክለብ ፓሪ ኤፍ.ሲ. የሚጫወተው ላላይና ኖሜንጃናሃሪ እግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው ብለዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ላሊ ከልምምድ በኋላ እግሩን የህመም ስሜት የተሰማው ቢሆንም መሰለፍ አለመሰለፉን ግን ከሃኪሞች እንሰማለን ብለዋል፣ ዛሬ ከኢትዮጵያ ጨዋታ በኋላ ወደኒያሚ አቅንተው የኒጀር ብሔራዊ ቡድንን የሚገጥሙት ማዳጋስካሮች ላሊን ለማሰለፍ እንደማይቸኩሉ አሰልጣኙ ገልጸዋል፡፡
አሰልጣኙ ጨምረው እንደገለጹት « የሰሞኑ ዝናብ ለጨዋታው ስጋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ ከትናንት በስተያ በጣለው ኃይለኛ ዝናብ ምክንያት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው መለማመድ የቻልነው፡፡ ከዝናቡ ባሻገር በጣም ጭጋጋማ ስለነበር እርስ በርስ መተየየትና መሥራት እንኳ አልቻልንም ነበር፡፡ ሜዳው ውሃ አይመጥም እንደዚህ አይነት ሜዳዎች ደግሞ ለእግር ኳስ በጣም አስቸጋሪ ናቸው፣ ዛሬ ከዘነበ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆንብን ብለዋል፡፡ »
የቡድኑ አዲሱ አምበል ለቡልጋሪያው ሉዶ ጎሬትዝ የሚጫወተው አቤል አኒሴ በበኩለ « የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን በደንብ አናውቀውም ስለዚህ ለነሱ ብለን የተለየ ዝግጅት አላደረግንም ነገርግን ልክ እንደአፍሪካ ዋንጫው እያንዳንዱን ጨዋታ በትኩረት እንጫወታለን፡፡ » « ቀላል ጨዋታ የሚሆን አይመስለኝም እኛም በከፍተኛ ትኩረት እንጫወታለን ብሏል፡፡ »
በተያያዘ ዜና ትናንት ምሽት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ኦንድሪ ራጆሊና በአምቦሂትሶሮሂትራ ብሔራዊ ቤተመንግስት ለብሔራዊ ቡድኑ የእራት ግብዣ በማድረግ ቡድኑን በራሳቸውና በህዝባቸው ስም አበረታትተዋል፡፡
መንግስታቸው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ሁልግዜም ከቡድኑ ጋር እንደሚቆም የገለጹት ፕሬዝዳንቱ « ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ባመጣችሁት ውጤት ለሙሉ የማዳጋስካር ህዝብና መንግሰት ኩራት እንደነበራችሁ ሰንደቃችንን ከፍ አድርጋችሁ እንዳውለበለባችሁ ሁሌም ለዚች ሃገርና ህዝብ ኩራት እንደምትሆኑ ተስፋዬ ነው መንግስትና ህዝብም በምትፈልጉት ሁሉ ሁሌም ከጎናችሁ ነው » ብለዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ፕሬዝዳንቱ ብሔራዊ ቡድኑን ለረዥም ዓመታት በአምበልነት የመራውና ዛሬ የመጨረሻ ጨዋታውን የሚያደርገውን ፋኔቫ ኢማ ኦንድሪያሲማን ላደረገው ነገር ሁሉ በመንግስታቸውና በህዝባቸው ስም ያመሰገኑ ሲሆን ለአዲሱ አምበል አቤል አኒሴ፣ ሮመ ሜታኒርና ንዢቫ ሮኮቶሃሪማላላ የሃገሪቱን ትልቁን ኒሻን ሸልመዋል፡፡
የኢትዮጵያና የማዳጋስካር ጨዋታ በሃገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ዛሬ ከቀኑ አስር ሰዓት ላይ ደረጋል፡፡