የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቀጥለው ሲውሉ በክልል ስቴዲየሞች 6ጨዋታዎች ተደርገዋል። ሁሉም ጨዋታዎች 9:00 ላይ የተደረጉ ሲሆን ከነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱ ያለግብ የተጠናቀቁ ሲሆን በአራቱ ጨዋታዎች 6ግቦች ተቆጥረዋል።
ወልቂጤ ላይ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ያሸነፈውን እና በ2011 የዋንጫ ተፎካካሪ የነበረውን ፋሲል ከነማን ያስተናገደው ወልቂጤ ከተማ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ የመጀመሪያ 3 ነጥቡን ማሳካት ችሏል። ለወልቂጤ ከተማ ብቸኛና የማሸነፊያውን ግብ ጃኮ አራፋት 5ኛው ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ችሏል። ይህም በሊጉ ታሪክ ወልቂጤ ከተማ ያስቆጠረው የመጀመሪያ ግብም መሆን ችሏል። በሌላ የሊጉ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ባህርዳር ከተማን አስተናግዶ ብሩክ በየነ 32ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ጣፋጭ 3ነጥብ ማስመዝገብ ችሏል። ይህ ውጤት ለሀዋሳ ከተማ ሁለተኛ ድሉ ሲሆን 7ኛ ነጥቡን ማሳካት ሲችል ባህርዳር ከተማ በአንፃሩ በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈቱ ሆኖ ተመዝግቧል።
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱንም ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ አድርጎ ሁለቱንም ጨዋታዎች በሽንፈት የተመለሰው እና ጫና ውስጥ የነበረው በአሰልጣኝ ስምዖን አባይ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ አዲስ አዳጊውን ሀድያ ሆሳዕና ድሬዳዋ ላይ አድርጎ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ችሏል። ለድሬዳዋ ከተማ የማሸነፊያውን ግብ በሪችሞንድ ኦዶንጎ እስኪያገኝ 79ደቂቃዎች ፈጅቶበት ነበር።
- ማሰታውቂያ -
በተመሳሳይ ሰዓት ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከ ቅ/ጊዮርጊስ ተጫውተው ያለግብ አቻ ተለያይተዋል። አሁንም ቅ/ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ ግብ ማግባትም ሆነ ድል ማስመዝገብ ተስኖታል። በውበቱ አባተ የሚሰለጥነው ሰበታ ከተማ አዳማ ከተማን አስተናግዶ በተመሳሳይ ያለግብ 0-0ተለያይቶ የውድድር አመቱን የመጀመሪያ ነጥብ ማግኘት ችሏል።
ሊጉ ነገም ሲቀጥል ሲዳማ ቡና ከጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ ከኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ 9:00 ሲል ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።
ሊጉን ሦስቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለውና በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው ወልዋሎ አ.ዩ. በ9 ነጥብ እና በ6 ንጹሕ ግብ መሪነቱን ሲይዝ ሐዋሳ ከተማ በ7ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ቅ/ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ በእኩል 5ነጥብ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል። ኢትዮጵያ ቡና፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ሰበታ ከተማ በእኩል 1 ነጥብ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም እና የወልዋሎ አ.ዩ. ሰመረ ሐፍተይ በእኩል 3ግቦች የኮከብ ግብ አግቢነቱን ሲመሩ ሽመክት ጉግሳ፣ ካርሎስ ዳምጠው፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ አዲስ ግደይ ፣ ዲዲየር ሊብሬ እና ጁኒያንስ ናጋንጂቡ በእኩል 2ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።