በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል 6ቱ ዛሬ የተደረጉ ሲሆን ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል ሀድያ ሆሳዕና ባህርዳር ከተማን በሜዳው ያስተናገደበት ጨዋታ አንዱ ነው። ይህንንም ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ሆሳዕና ላይ በአቢዮ አርኤርሳሞ ስታዲየም ሀድያ ሆሳዕናን ከባህርዳር ከተማ ያገናኘው ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ሀድያ ሆሳዕና እስካሁን በሊጉ ድል ማስመዝገብ ባለመቻሉ እና በሊጉ የመጀመሪያውን ድል ለማግኘት እንዲሁም ባህርዳር ከተማ ደግሞ በ4ኛው ሳምንት ድሬደዋ ከተማ ላይ የተቀዳጀውን የ4-1 ድል በመድገም ከመሪው ወልዋሎ አ.ዩ. ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ በጉጉት ተጠብቆ ነበር።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው መሪነቱን መውሰድ ችለው የነበሩት በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚሰለጥኑት ባህርዳር ከተማዎች ሲሆኑ 31ኛው ደቂቃ ላይ ማማዱ ሲዲቤ ያስቆጠራት ግብ እንግዳዎቹን መሪ ስታደርግ ባለሜዳዎቹን ሀድያ ሆሳዕናዎች ደግሞ ድንጋጤ ውስጥ ከታለች። በዚህች ብቸኛ ግብም የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ሁለቱ ቡድኖች በባህርዳር ከተማ 1-0 መሪነት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል። ከእረፍት መልስ ባለሜዳዎቹ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት 4ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጀባቸው። 49ኛው ደቂቃ ላይ የሀድያ ሆሳዕናው ቢስማርክ አፒያ ግብ አስቆጥሮ ደጋፊዎቹን እፎይ አሰኝቷል።
ሆኖም ይህ እፎይታ የቀጠለው ለ1 ደቂቃ ብቻ ነበር። 50ኛው ደቂቃ ላይ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጥሩ እንቅስቃሴ እና መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው የባህርዳር ከተማው ፍፁም ዓለሙ ግብ አስቆጥሮ የባህርዳር ከተማን መሪነት ማስመለስ ችሏል። ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላም ወደ አቻነት ለመመለስ ሀድያ ሆሳዕናዎች በተደጋጋሚ ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ይህንንም ተከትሎ 67ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ጊቻሞ ግብ ያስቆጠራት ግብ ባለሜዳዎቹን ከሽንፈት ታድጓል። የተገኘው የአቻ ውጤትም ለሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ ሁለተኛ ነጥቡ ሆኖ ተመዝግቦላታል። ውጤቱንም ተከትሎ ባህርዳር ከተማ ነጥቡን ወደ 8 በማሳደግ 3ኛ ደረጃላይ ሲቀመጥ ሀዲያ ሆሳዕና በ2ነጥቦች የሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል።
ሊጉን አንድ ጨዋታ የሚቀረው ወልዋሎ አ.ዩ. በ10 ነጥቦች ሲመራ ሲዳማ ቡና በ9 እንዲሁም ባህርዳር ከተማ በ8ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃ ይዘዋል። የኮከብ ጎል አግቢነቱን ደግሞ የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም፣ የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ፣ የባህርዳር ከተማዎቹ ማማዱ ሲዲቤ እና ፍፁም ዓለሙ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በየነ በእኩል 4 ግቦች ሲመሩ አዲስ ግደይ፣ ዳዋ ሁቴሳ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ይገዙ ቦጋለ እና ሰመረ ሀፍተይ በእኩል 3ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።