የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ አጋማሽ የሚደረጉ ሲሆን ሰባት ጨዋታዎች ነገ (ረቡዕ) ሲደረጉ ቀሪ አንድ ጨዋታ ደግሞ ሀሙስ የሚደረግ ይሆናል። በነገው እለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል መቐለ 70 እንደርታ ከ ስሑል ሽረ የሚያደርጉትን ጨዋታ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: መቐለ 70 እንደርታ ከ ስሑል ሽረ
የጨዋታ ቀን: ረቡዕ ጥር 20/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌደራል አርቢትር ባህሩ ተካ
የጨዋታ ቦታ: ትግራይ ስታድየም
ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ የተሸነፋት የሊጉ መሪዎች መቐለ 70 እንደርታ 7 ተከታታይ ጨዋታ ላይ ሽንፈት ያላስተናገዱትን ስሑል ሽረዎችን በትግራይ ስታድየም ያስተናግዳሉ።በመሀከላቸው የ3 ነጥብ ልዩነት ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ነገ ሚያደርገት ጨዋታ ጠንካራ ፋክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
- ማሰታውቂያ -
የሻምፒዮንነት ክብራቸውን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ፋክክር ሚጠብቃቸው መቐለዎች በ10ኛው ሳምንት ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ከነገው ጨዋታ ሥስት ነጥብ ይዞ መውጣት ግድ ሚላቸው ይሆናል።እንደተጋጣሚያቸው አቀራረብ ተቀያያሪ የሆነ የጨዋታ ስልት ይዘው ሚቀርቡት ምዓም አናብስቶቹ በነገው ጨዋታ መስመር ላይ መሰረት ያደረገ አጨዋወትን ምርጫጨው ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይገመታል።በተለይ ወላይታ ዲቻን ሲገጥሙ ያልነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ከጉዳቱ አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ መቐለዎች ከግዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣውን የስሑል ሽረን ተከላካይ ክፍልን ለማስከፈት እንዳይቸግሩ ሊያግዛቸው እንደሚችል ይገመታል።በተጨማሪ ከጨዋታ ጨዋታ ጥሩ ጥምረት እየፈጠሩ ሚገኙት ኦኪኪ ኦፎላቢ፣አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ያሬድ ከበደ በነገው ጨዋታ የመቐለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ሀላፊነት እንደሚሰጣቸው መገመት ከባድ አይሆንም።
7 ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ያልተሸነፋት ስሑል ሽረዎች ከመሪዎቹ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ከእንደዚህ ዓይነት ጨዋታዎች ነጥብ ይዞ መውጣት ግድ ሚላቸው ይሆናል።ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ካላቸው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቡድኖች መካከል በቀዳሚነት ሚጠቀሱት ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ መስመር ላይ ትኩረት ያደረገ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን ይዘው ሊቀርቡ እንደሚችሉ ይገመታል።ካለፋት 7 ጨዋታዎች አምስቱ ላይ ግብ ያላስተናገዱት ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ የመቐለ ፈጣን አጥቂዎች እንቅስቃሴን በንቃት መከታተል ግድ ይላቸዋል።በተለይ ወደ መሀል ሜዳ ተጠግተው በሚከላከሉበት ጊዜ የመቐለን መልሶ ማጥቃት መቆጣጠር ካልቻሉ ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ።
ምዓም አናብስቶቹ በነገው ጨዋታ ከሚኪኤል ደስታ ውጪ በጉዳት ሚያጡት ተጨዋች አይኖርም።ከወላይታ ድቻ በነበረው ጨዋታ በጉዳት ያልተሰለፈው አማኑኤል ገብረሚካኤል ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው ለሙከራ ወደ ቱርክ ካመራው ምንተስኖት አሎ ውጭ ከጉዳት ነፃ የሆነ ቡድናቸውን ይዘው ወደ ሜዳ ይገባሉ።
መቐለ 70 እንደርታዎች በደጋፊያቸው ፊት አምስት ጨዋታዎችን አካሂደው አራቱም ላይ ሲያሸንፋ አንዱ ላይ አቻ ተለያይተዋል።በአምስቱ ጨዋታዎች ላይ 8 ግቦችን ሲያስቆጥሩ በተቃራኒው 3 ግቦችን አስተናግደዋል።
ከሜዳቸው ወጥተው 4 ጨዋታዎችን ያደረጉት ስሑል ሽረዎች ሊያገኙት ከሚችሉት 12 ነጥቦች አምስቱን ማሳካት ሲችሉ፤ከአራቱ ጨዋታዎች ሥስቱ ላይ ምንም ግብ ሳያስተናግዱ ወጥተዋል።