ለሻምፒዮንነት እና ላለመውረድ በሚደረግ ጠንካራ ፉክክር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰው እና ሊጠናቀቅ 4 ሳምንታት የቀሩት የኢትዮጵያ ኘሪሚዮር ሊግ ለሻምፒዮንነት 5 ክለቦችን ከፊት አፋጧል፡፡በሌላ በኩል በቁጥራዊ ስሌት ከ6-16ኛ ደረጃ ያሉ ክለቦችን ከመውረድ ስጋት ሳያላቅቅ ሲቀጥል የ27ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታዎች ዛሬ ረፋድ 4:00 ጎንደርና አዲስ አበባ ላይ በሚካሄዱ 2 ጨዋታዎች ሲጀምር በክፍል አንድ ዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል፡፡
ወልዲያ ከተማ ከ ጅማ አባጅፋር
ጨዋታው ትልቅ ትርጉም ያለው እንደመሆኑ ትርፍና ኪሳራ የሚወራረድበት ነው፡ ፡የጨዋታው ውጤት ለሊጉ ክስተት ጅማ አባጅፋር ወደ ታሪካዊው የዋንጫ ጉዞው ለመድረስ የሚቃረብበት ሲሆን በተለይም ለወልዲያ ከተማ ስፖርት ክለብ በቃላትም ከሚባለው በላይ ለክለቡና(ደጋፊዎቹ) ሀዘኔታን የሚፈጥር እንዳይሆን ያሰጋል፡፡በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት ወልዲያዎች ዛሬ በጅማአባጅፋር የሚሸነፉ ከሆነ ከኘሪሚዮር ሊጉ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ከሚወርዱ 3 ክለቦች የመጀመሪያዎቹ ወራጅ ክለብ ይሆናሉ፡፡ጅማ አባጅፋርን ዛሬ የሚፋለሙት ወልዲያዎች ውጤት የሚቀናቸው ከሆነም ወደ ታችኛው ሊግ ከመውረድ ለመትረፍ ያላቸውን ጠባብ ዕድል ለመጠቀም ቀጣይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ የሌሎችን መሸነፍ በተስፋ ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡
በመሀከላቸው ባሉት የ25 ነጥብ ልዩነት በ45 ነጥብ በሊጉ አናት ላይ የሰፈሩት ጅማዎች እና በ20 ነጥብ በሊጉ ግርጌ የተቀመጡት ወልዲያዎች ዛሬ ረፋድ 4:00 በአዲስ አበባ ስታዲዮም የሚያደርጉት ጨዋታ በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ተጠባቂ ጨዋታዎች ቀዳሚው መሆኑ ብዙም አከራካሪ አይሆንም፡፡ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋው መጀመሪያ ደቂቃ አንስቶ እስከ መጨረሻዋ የጨዋታውን መጠናቀቅ ማብሰሪ የዳኛ ፊሽካ ድምፅ ሙሉ ለሙሉ ማጥቃት ላይ ብቻ ያመዘነ አጨዋወት እንደምንመለከት ከጨዋታው ውጤት አስፈላጊነት ባለፈም 1 ጎል ለሻምፒዮናው ጉዞ ያለውን ጥቅም ስንመለከት በዚህ ጨዋታ በርካታ ግቦች እንደሚስተናገዱበት ይገመታል፡፡
- ማሰታውቂያ -
በበርካታ ችግሮችና ፈተናዎች እንዲሁም የቡድኑ አለመረጋጋት ጭምር ተከቦ የቆየው ወልዲያ ከተማ ስፖርት ክለብ የኘሪሚዮር ሊግ ቆይታው አጣብቂኝ ውስጥ የገባ እንደመሆኑ ተጨዋቾች ይህን ጨዋታ በጥሩ ስነ ልቦና ላይ ሁነው ጨዋታውን ለማድረግ ሊቸገሩ የሚችሉበት ዕድል ከፍ ያለ ቢሆንም ለጅማ አባጅፋር በቀላሉ እጅ እንደማይሰጡ ይታመናል፡፡ሁለቱም ቡድኖች የ26ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታቸውን እዚሁ አዲስአበባ ስታዲዮም ያደረጉ ሲሆን ጅማዎች ባለሜዳውን መከላከያ 1-0 ሲያሸንፉ፡ወልዲያዎች በአንፃሩ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ግብ በማስቆጠሩ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም በተቆጠሩባቸው 3ግቦች የ3-1 ሽንፈት ማስተናገዳቸው ይታሳል፡፡
የወልዲያው ሰለሞን ገ/መድህን እና የጅማ አባጅፋሩ ሄኖክ ኢሳያስ በጉዳት በዚህ ጨዋታ ለቡድናቸው ግልጋሎትን የማይሰጡ ሲሆኑ ለረጅም ጊዜ በፌዴሬሽኑ ቅጣት የተጣለበት አማካኙ ብሩክ ቃልቦሬ በወልዲያ በኩል የማይኖር ሲሆን በጅማ በኩል ከቅጣት ጋር የተያያዘ ዜና የለም፡፡
በመጀመሪያው ዙር ሁለቱ ቡድኖች ጅማ ላይ በተገናኙበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ 1-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ፌደራል ዳኛ ጌቱ ተፈራ ይህን ተጠባቂ ጨዋታ በመሃል ዳኝነት ይመራዋል፡፡
ፋሲል ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
በስነ ልቦናው በኩል ባለፈው ሳምንት ካስመዘገቡት ውጤት አንፃር በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙት ፋሲልና ሲዳማ በአፄ ፋሲለደስ ስታዲዮም የሚያደርጉት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚስተናገድበት የሚጠበቅ ነው፡፡እንግዳዎቹ ሲዳማ ቡናዎች ባለፈው ሳምንት በፍቼ ጨምበላላ ዓመታዊ በዓለል ምክንያት የሜዳቸውን ጨዋታ ወደ ሀዋሳ ወስደው ድሬድዋ ከተማን 1-0 የረቱ ሲሆን :ባለሜዳዎቹ ፋሲሎች አዲስ አበባ ላይ ከመቀለ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ነጥብ ቢጋሩም በጨዋታው ያሳዩት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ከመሆኑም ባሻገር ነጥብ መጋራታቸውም ለዚህ ጨዋታ መነቃቃት እንደሚፈጥርላቸው ይታመናል፡፡
የዚህ ጨዋታ ውጤት ለሁለቱም ክለቦች አስፈላጊ ቢሆንም ከመውረድ ስጋት በጊዜ ለመላቀቅ እንጂ ወደ ሻምፒዮናው ፉክክር የሚያደርስ አይደለም፡፡ ቀስ በቀስ ከሻምፒዮናው ፉክክር እየራቀ የመጣው ፋሲል ከነማ አሁን ደግሞ በቁጥራዊ ስሌት ከወራጂ ስጋት ነፃ ለመሆን 5 ነጥቦች ያስፈልጋቸዋል፡፡በተለይም ዛሬ ከበታቹ ያለውን ሲዳማ ቡናን በሜዳው ማሸነፍ ለአፄዎቹ ለቀጣይ ጨዋታዎች እፎይታን የሚሰጥ እንደመሆኑ በሜዳቸውና በደጋፊዎቻቸው ፊት ለማሸነፍ የሚጫዎቱ ሲሆን በቀጥታ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋዎትን ሜዳ ላይ እንደሚተገብሩ ይጠበቃል፡፡
በ32 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ከወራጂ ቀጠናው በ4 ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ከዚህ ጨዋታ የግድ ነጥብ የሚያስፈልጋቸው እንደመሆኑ ከሜዳቸው ወጥተው የሚጫዎቱ ቢሆንም ጥንቃቄ ያመዘነበት ግብ ለማግኘት በተሻጋሪ ኳሶች ለአፄዎቹ ፈተና መሆናቸው አይቀርም፡፡መጠንኛ ግብ እንደሚስተናገድበት የሚገመተው ይሄው ጨዋታ በ35 ነጥብ 6 ኛ ደረጃ ላይ ለተቀመጡት አፄዎቹ የጨዋታው ውጤት ደረጃቸውን ለማሻሻል ባያስችላቸውም ነጥባቸውን 38 በማድረስ እፎይታን የሚፈጥሩበትና ከወራጅ ስጋት የሚላቀቁበት ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡
በፋሲል ከተማ በኩል አይናለም ሀይለ በጉዳት ለጨዋታው የማይደርስ መሆኑ የተነገረ ሲሆን የግራ መስመር ተከላካዩ አምሳሉ ጥላሁንና የመሀል ተከላካዩ ያሬድ ባዬ ከጉዳት መመለሳቸው ተነግሯል፡፡በሲዳማ ቡና በኩል የጉዳት ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት አርቢትር ኢብራሂም አጋዥ እንደሚመሩት ታውቋል፡፡