በድራማዊ ክስተቶች ታጅቦ የተካሄደው ጨዋታ በመቐለ 70 እንደርታ አሸናፊነት ተጠናቋል።ከሁለቱም ቡድኖች አንዳንድ ተጨዋቾች በቀይ ካርድ በተሰናበቱበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ኦኪኪ ኦፎላቢ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ወሳኝ ሥስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል።
አሰልጣኝ ገብረመድሃን ሀይለ ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ ከተሸነፈው ቡድን አራት ቅያሬዎች አድርገዋል።አሚን ነስሩ፣ሥዩም ተስፋዬ፣አንተነህ ገብረክርስቶስ፣ኤፍሬም አሻሞ ወጥተው ላውረንስ ኤድዋርድ፣አሸናፊ ሀፍቱ፣አስናቀ ሞገስ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ገብተዋል።ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው በ10ኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ከገጠመው ስብስብ ረመዳን የሱፍን በሸዊት ዮውሀንስ ቀይረዋል።
- ማሰታውቂያ -
ብዙ ሙከራዎች ያልታዩበት ተደጋጋሚ የዳኛ ፊሽካዎች እና ጥፋቶች የተስተዋሉበት የመጀመርያው አጋማሽ ይህሽ ሚባል እንቅስቃሴ ያልታየበት ነበር።በተለይ በ12ኛው ደቂቃ የተፈጠረው ክስተት የጨዋታውን መልክ የቀየረ ነበር።የስሑል ሽረ የመስመር አጥቂ ዲድየ ሌብሪ ከኳስ ውጪ አስናቀ ሞገስን መማታቱን ተከትሎ የዕለቱ ዋና ዳኛ ፌደራል አርቢትር ባህሩ ተካ በረዳት ዳኞቻቸው እገዛ ኮትዲቫራዊውን አጥቂ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል።ከቀይ ካርዱ በኃላ የቁጥር በላይነታቸውን ተጠቅመው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ለመጫወት የሞከሩት መቐለዎች በተደጋጋሚ የስሑል ሽረ ፍፁም ቅጣት ሳጥን ውስጥ ቢደርሱም እንደነበራቸው ብልጫ ብዙ እድሎችን መፍጠር አልቻሉም።በጨዋታው የመጀመርያ 10 ደቂቃዎች ላይ በፍፁም ቅጣት ሳጥን በግራ መስመር በኩል የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ከሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ የተላከለትን ኳስ በመጠቀም መሬት ለመሬት ቢመታውም ጨዋታው ላይ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ወንድወሰን አሸናፊ መልሶበታል።ከዚህ በተጨማሪ በቀኝ መስመር የተሰለፈው ያሬድ ከበደ ከዮናስ ገረመው የተቀበለውን ጥሩ ኳስ በመጠቀም ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ሸዊት ዮውሀንስ ተንሸራትቶ መልሶበታል።በጎደሎ ቁጥር የተጫወቱት ስሑል ሽረዎች አብዛኛውን የመጀመርያ አጋማሽ መከላከል ላይ ያሳለፋ ሲሆን አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል።በምሳሌነት ሊጠቀሱ ሚችሉት ሸዊት ዮውሀንስ ከግራ መስመር አሻምቶት ሳሊፍ ፎፎና ሳይደርስበት የቀረ ኳስ እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ከመሀል ሜዳ አብዱልለጢፍ መሐመድ እና ሳሊፍ ፎፎና በጥሩ ቅብብል ሄደው ኮትዲቫራዊው ሳሊፍ ከበረኛው አናት ለማሳለፍ ሲሞክር ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ ተጠቃሽ የስሑል ሽረ የግብ እድሎች ናቸው።
በሁለተኛው አጋማሽ መቐለዎች ሙሉ ኃይላቸውን ማጥቃት ላይ ትኩረት አድርገው ሲጫወቱ ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው አንድ ነጥብዋን ለማስጠበቅ መከላከልን ምርጫጨው አድርገዋል።የገብረመድህን ሀይለ ተጨዋቾች ከመሀል ሜዳ ወደ ሁለቱም መስመር በሚላኩ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም በሜዳው የመጨረሻ ክፍል ላይ የነበራቸው አለመግባባት የጠራ የግብ እድሎችን እንዳይፈጥሩ አድርግዋቸዋል።በተለይ ቀኝ መስመር ላይ ትኩረት ያደርገው የሁለተኛው አጋማሽ የመቐለ ማጥቃት እንቅስቃሴ በስሑል ሽረ ተከላካይ ክፍል ቁጥጥር ውስጥ ሲገባ ታይቷል።የስሑል ሽረ ተከላካይ ክፍልን ማንኳኳታቸውን የቀጠሉት መቐለዎች በ56ተኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ሳጥን ውስጥ አዳም ማሳላቺ ኳስን በእጅ መንካቱ ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ኦኪኪ ኦፎላቢ ቢመታውም ወንድወሰን አሸናፊ አድኖበታል።
ማጥቃታቸውን የቀጠሉት መቐለዎች በኦኪኪ ኦፎላቢ፣አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ያሬድ ብርሀነ አማካኝነት እድሎችን ቢፈጥሩም አሁንም የስሑል ሽረን ጥብቅ መከላከል ለመድፈር ተቸግረዋል።ሆኖም ጨዋታው ሊጠናቀቅ 9 ደቂቃዎች ሲቀሩት ኦኪኪ ኦፎላቢ ግብ አስቆጥሮ የመቐለ ደጋፊዎችን በደስታ አስፈንጥዝዋል።ከቀኝ መስመር ዳንኤል ደምሱ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ያሻገው ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል በግምባሩ ወደ ኃላ የመለሳት ኳስ ግዙፋ ናይጀርያዊ አጥቂ ኦኪኪ ኦፎላቢ በግምባሩ ገጭቶ ሊያስቆጥራት ችሏል።ኦኪኪ ግብዋን አስቆጥሮ ደስታውን በሚገልፅበት ጊዜ ማልያውን በማወለቁ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል።
ከግብዋ መቆጠር በኃላ ስሑል ሽረዎች ሙሉ ኃይላቸውን ወደ ፊት በማድረግ የአቻነት ግብ ለማግኘት ቢሞክሩም ሙከራቸው ሳይሳካ ቀርቷል።በዚህም መሰረት ጨዋታው በመቐለ 70 እንደርታ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ መቐለዎች ነጥባቸውን ወደ 22 ከፍ በማድረግ መሪነታቸውን ሲያስቀጥሉ ስሑል ሽረዎች ሁለት ደረጃዎችን ወደ ታች ተንሸራትተዋል።