በ2009 የውድድር ዓመት የወንዶች እና የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተብለው የተመረጡት ተጫዋቾች በዛሬው እለት በካፒታል ሆቴል በተደረገ ስነስርዓት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። በውድድር አመቱ ድንቅ ብቃት ያሳዩ ወንድ 3 ፣ ሴት 3 ተጫዋቾች እና በሁለቱም ፆታዎች 3 3 ግብ ጠባቂዎች እጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ከነዚህ 12 እጩዎች መካከል አሸናፊ የሆኑት 4 ተጫዋቾች የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ወስደዋል። በሴቶቹ ኘሪምየር ሊግ በውድድር ዓመቱ ለክለቧ 33 ግቦችን ያስቆጠረችው ሎዛ አበራ 816 ነጥብ በማግኘት አሸናፊ መሆን ችላለች።
በተመሳሳይ በዓመቱ ድንቅ ብቃቷን ማሳየት የቻለችው የሀዋሳ ከነማ ግብ ጠባቂ ትዕግስት አበራ 477 ነጥብ በማስመዝገብ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመባል የ40,000 ብር ተሸላሚ መሆን ችላለች።
በወንዶቹ መካከል በተደረገው ተመሳሳይ ፉክክር አቤል ማሞ ከመከላከያ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሲባል የቅ/ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ ኮከብ ተጨዋች በመባል ተሸላሚ ሆነዋል። በግብ ጠባቂዎች በኩል
አቤል ማሞ ከመከላከያ፣ ሮበርት ኦዶንካራ ከ ቅ/ጊዮርጊስ እንዲሁም አምና በሲዳማ ቡና ድንቅ ብቃቱን ያሳየውና በዘንድሮው ዓመት ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የተዛወረው ለዓለም ብርሀኑ እጩዎች ሆነው የቀረቡ ሲሆን በተሰበሰበው ውጤት መሰረት አቤል ማሞ 379 ነጥብ በማግኘት አሸናፊ መሆን ችሏል።
በወንዶቹ ሌላ የሽልማት ዘርፍ አስቻለው ታመነ እና ምንተስኖት አዳነ ከቅ/ጊዮርጊስ እንዲሁም አምና በሲዳማ ቡና ድንቅ ብቃቱን ያሳየው አዲሱ የቅ/ጊዮርጊስ ፈራሚ ሙሉአለም መስፍን እጩ ሆነው መቅረብ የቻሉ ሲሆን የቅ/ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ 844 ነጥብ በማስመዝገብ አሸናፊ መሆን ሲችል የቡድን አጋሩ ምንተስኖት አዳነ ከ አስቻለው በ 354 ነጥብ ዝቅ በማለት 490 ነጥብ አግኝቶ ሁለተኛ ለመውጣት ችሏል። ሌላኛው እና አዲሱ የቡድን አጋራቸው ሙሉአለም መስፍን(ዴኮ) 472 ነጥብ አግኝቶ ሶስተኛ መውጣት ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዝግጅቱ ላይም የቀድሞው ድንቅ እና ተወዳጅ አጥቂ ዮርዳኖስ አባይ ልዩ ተሸላሚ በመሆን የተዘጋጀለትን ሽልማት ከእለቱ እንግዶች ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እና ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ እጅ ተቀብሏል።