የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዓለም አቀፋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን /ፊፋ/ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ተጨዋቾች ዝውውርን አስመልክቶ ባወጣው መመሪያ መሠረት በቀጣይ በ2012 ዓ.ም ፌዴሬሽኑ በመሚመራቸው ውድድሩሮች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ተጨዋቾች በኢንተርሚደሪ /በሶስተኛ ወገን / ብቻ ምዝገባ እንደሚካሄድ አስታወቀ፡፡
ቀደም ሲል ይህንኑ ሥራ ለመስራት የሚያስችለውን የኢንተርሚደሪ /የሶስተኛ ወገን/ ፈቃድ ለሚፈልጉ በሙሉ
በፌዴሬሽኑ መስፈርት መሠረት የፈቃድ መውሰጃ ፈተና በመስጠት 75 የሚሆኑት ተመዝጋቢዎች የመመዘኛ ፈተናውን ማለፋቸውን የአረጋገጡ በመሆናቸው ፈቃዱን ለመውሰድ የፈቃድ ክፍያ እና የኢንሹራንስ ክፍያ በመፈፀም ቅድመ ዝግጅታቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ ፡፡
ከሐምሌ 25 /2011 እስከ ጥቅምት 12 /2012 እና ከጥር 1 እስከ ጥር 30 ቀን 2012 ዓ.ም በአንደኛ እና በሁለተኛ ዙር የሚከናወኑት የ2012 ዓ.ም የተጫዋቾች ምዝገባን አስመልክቶ ለኘሪሚየር ሊግ ክለቦች፣ ለከፍተኛ እና ለአንደኛ ሊግ ክለቦች ዛሬ ሐምሌ 18/ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ከፌዴሬሽኑ ሕጋዊ የሦስተኛ ወገን ፈቃድ በተሰጣቸው ህጋዊ አካላት ብቻ ማስመዝገብ እንደሚገባቸው እና በፌዴሬሽኑ ህጋዊ የሆኑት አካላትም ስም ዝርዝር በደብዳቤ እንደሚላክላቸው የተገለፀ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፀሐፊ የሆኑት አቶ ሚሊዮን መኮንን ገልፀዋል፡፡
አክለውም “ማንኛውም የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ተጫዋች በተገለፁት የምዝገባ ጊዜያት ለመመዝገብ በሚቀርብበት ወቅት ከፌዴሬሽኑ የሶስተኛ ወገን ፈቃድ ባላቸው እና ሕጋዊ በሆኑት አካላት ብቻ መመዝገብ እንደሚገባቸው” አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም “ይህ አይነቱ አሰራር ለአገራችን እግር ኳስ የራሱ የሆነ በጎ ገጽታ ያለው ሲሆን ለክለቦቻችን በወቅቱ የሚፈጠሩትን የተለያዩ የምዝገባ ስህተቶች በአፋጣኝ ለመፍታት፣ ለፌዴሬሽኑ የገቢ ምንጭ እንዲያገኝ የማስቻል እና ለተጨዋቾች በተደጋጋሚ የሚከሰትን ክስ እና እንግልት ለመቀነስ እንዲሁም የሦስተኛ ወገን ፈቃድ ላላቸው የሥራ እድል መፍጠርን የሚያስችል ነው፡፡ በተጨማሪም የዓለም አቀፋ የእግር ኳስን አሠራር ሂደት የሚከተለውን ዘመናዊ ሥርዓት በአገራችን መተግበሩ በፊፋ እና በካፍ መልካም ገጽታ ለማግኘት የራሱ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ያደርጋል በማለት” አስረድተዋል ፡፡
Via- theeff official page