የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በሚደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን፥ በመጀመሪያው ጨዋታ ከቀኑ በ9 ሰዓት ላይ መከላከያ አርባ ምንጭ ከተማን ያስተናግዳል።
እንዲሁም 11:30 ላይ ደግሞ መልካ ቆሌ ላይ በወልዲያ ከተማ የተሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ የወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘውን ሀዋሳ ከተማን የሚያስተናግድ ይሆናል።
አሰልጣኙን ማሰናበቱን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ቡና በጊዜያዊነት ክለቡን እንዲያሰለጥኑ በተሾሙት አዳዲስ አሰልጣኞች እየተመራ ወደ ሜዳ እንደሚገባም ይጠበቃል።
ክልል ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ከቀኑ በ9 ሰዓት ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፋሲል ስታዲየም ይጫወታሉ። በተመሳሳይ ከቀኑ በ9 ሰዓት ወላይታ ድቻ በሜዳው ሶዶ ስታዲየም ጅማ አባቡናን የሚያስተናድግ ሲሆን፥ ሲዳማ ቡና ይርጋለም ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያስተናግዳል።
- ማሰታውቂያ -
በሊጉ በጎል ልዩነት ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ በበኩሉ ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀለውን አዲስ አበባ ከተማን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይገጥማል።
ሊጉን በአንደኝነት በመምራት ላይ የሚገኘው ደደቢት በበኩሉ ወደ ድሬ ዳዋ በማቅናት ከቀኑ በ10 ሰዓት ላይ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።
በሊጉ ቀሪ አንድ ጨዋታ በነገው እለት የሚካሄድ ሲሆን፥ በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልዲያ ከነማን 11:30 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳል።