ከሳምንታት በፊት የፈረሰኞቹ ገጽ ፓርቹጋላዊው ቫዝ ፒንቶ ቀጣዩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ ሊሆኑ እንደሚችሉ የተለያዩ ምንጮቹን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል። አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ለመጪዎቹ 2 አመታት መሾማቸውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ይፋ አድርጓል።
አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ ማን ናቸው?
ቫዝ ፒንቶ በአገራቸው የፖርቹጋል ሊግ ውስጥ ከ1985/86 እስከ 2006/07 ድረስ በተጨዋችነት ቆይተዋል። እንዲሁም ከ2007/08 አንስቶ እስከ 2011/12 ድረስ በፖርቹጋል ውስጥ የሚገኙ ከ19 ዓመት በታች ያሉ ቡድኖችን በምክትል አሰልጣኝነት አሰልጥነዋል። እኚህ አሰልጣኝ በ2012 ወደ አንጎላ በማቅናት ዝነኛውን የአንጎላ ክለብ የሆነውን ሪክሬቲቮ ካላን ለ2 አመታት ከ4 ወራት ያህል በምክትል አሰልጣኝነት አሰልጥነዋል። እንዲሁም ከ2014 እስከ 2016 ድረስ በአንጎላ የኤሲ ሎቢቶ ክለብ ቴክኒካል ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል።
አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ በ2016 በፖርቹጋል 2ኛ ዲቪዚዮን የሚወዳደረውን ክለብ ፋማሊቻኦን ማሰልጠን ችለዋል። በቀጣይ በ2017 የአንጎላ ክለብ የሆነውን ሪክሬቲቮ ዶ ሊቦሌን ተረክበው እስከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ድረስ በዋና አሰልጣኝነት ሲያሰለጥኑ ቆይተዋል።
- ማሰታውቂያ -
አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ «ጊራቦላ» ተብሎ በሚጠራው የአንጎላ የሊግ ውድድር ላይ በያዝነው የውድድር ዓመት ሪክሬቲቮ ሊቦሌን ይዘው 21 ጨዋታዎችን ማድረግ ሲችሉ 10 ጨዋታዎችን በድል ተወጥተዋል። እንዲሁም በ7 ጨዋታዎች ላይ አቻ ሲለያዩ በ4 ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግደው በሊግ ውድድሩ 5ኛ ደረጃን ይዘዋል። በሊግ ውድድር ላይ 34 ጎሎችን አስቆጥረው 15 ጎሎች ተቆጥረውባቸዋል።
አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ በ2017 የካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ ውድድር ላይ በክለቡ ደጋፊዎች እንዲወደዱ ያስቻላቸውን ታላቅ ስራ ሰርተዋል። ይህም በክለቡ በታላቅ ጉጉት ይፈለግ የነበረውን የካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ድልድል ውስጥ መካተትን ማሳካት ነው። አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ በ2017 የቶታል ካፍ ኮንፈደሬሽን ውድድር ክለብ ሪክሬቲቮ ሊቦሌን በምድብ ድልድል እንዲካተት ያስቻሉ ሲሆን በምድብ ድልድል ጨዋታዎችም 7 ነጥብ በመሰብሰብ 3ኛ ሆነው ማጠናቀቅ ችለዋል።
የምስል ምንጭ:– St.George Fc
source -የፈረሰኞቹ ገፅ