በጋቦን አስተናጋጅነት በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አራት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ።
በምድብ አራት የተደለደሉት ግብፅ፣ ኡጋንዳ፣ጋና እና ማሊ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ዛሬ ምሽት 1 ሰዓት ላይ በሚደረግ የምድብ አራት የመጀመሪያ ጨዋታ የምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ ተካፋይ የሆነችው ኡጋንዳ ከጥቋቁር ኮከቦቹ ጋና ጋር ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።
እንዲሁም ምሽት አራት ሰዓት ላይ የሚደረግ ጨዋታ ደግሞ የምእራብ አፍሪካዋን ማሊ ከሰሜን አፍሪካዋ ግብፅ ጋር የሚያገናኝ ይሆናል።
- ማሰታውቂያ -
ትናንት ምሽት የምድብ ሶስት ጨዋታዎች የተካሄዱ ሲሆን፥ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ የተደረገው ጨዋታ አይቮሪኮስትን ከቶጎ አገናኝቷል።
ጨዋታውም ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ምሽት አራት ሰዓት ላይ በተደረገ ሌላኛው የምድብ ሶስት ጨዋታ ደግሞ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ከሞሮኮ ጋር ነበር ያገናኘው።
ጨዋታውም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 1ለ0 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዚህም መሰረት አስተናጋጇ ጋቦን የምትገኝበት የመጀመሪያው ምድብ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት በመጠናቀቃቸው ሁሉም 1 ነጥብ ይዘዋል።ከምድብ ሁለት ደግሞ ቱኒዝያን የረታችውሴኔጋል ምድቡን በሶስት ነጥብ እየመራች ነው።
አቻ የተለያዩት ዚምባብዌ እና አልጀሪያ ደግሞ በእኩል 1 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛን ደረጃ ይዘዋል።
ትናንት ምሽት ጨዋታቸውን ያደረጉት ምድብ ሶስት ሀገራት ውስጥ ደግሞ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሙሉ ሶስት ነጥብ ምድቡን በመምራት ላይ ትገኛለች። ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት የተለያዩት አይቮሪኮስት እና ቶጎ በእኩል አንድ ነጥብ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ቀጥለው የተቀመጡ ሲሆን፥ ሞሮኮ በ0 ነጥብ ከምድቡ መጨረሻ ላይ ተቀምጣለች።
ለ23 ቀናት በሚቆየው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ 16 ሀገራት በአራት ምድቦች ተደልድለው 32 ጨዋታዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ ኮትዲቯር፣ሴኔጋል፣ ጋና፣ አልጄሪያ እና ግብፅ ዋንጫውን ያነሳሉ ተብለው ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት ወስጥ ተጠቃሽ ናቸው።