በ 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የመጀመሪያ ቀን ውሎ የምድብ ሀ 2 ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲሆን በ 8 ሰአት ላይ በተደረገው ጨዋታ ደደቢት ከ አ/አ ከተማ ተገናኝተው አ/አ ከተማ በ 57ኛው ደቂቃ እንዳለማው ታደሰ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል 1 – 0 አሸንፎ መውጣት ችሏል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መሀል ሜዳ ላይ ያተኮረ ሲሆን ደደቢት በተሻለ ጫና ፈጥሮ የተጫወተ ቢሆንም አጥቂዎቹ ያገኙትን የግብ አጋጣሚዎች መጠቀም ባለመቻላቸው ጨዋታውን ለመሸነፍ ተገዷል፡፡ በጨዋታውም ላይ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የቻለው የአ/አ ከተማው ዳዊት ማሞ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ በመመረጡ የተዘጋጀለትን ዋንጫ ከእለቱ የክብር እንግዳ እጅ ተቀብሏል ፡፡
- ማሰታውቂያ -
10:00 ሲል የተገናኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ተጋባዡ ጅማ አባጅፋር ያለምንም ግብ 0-0 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የተጫወቱ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ፍሰት ባለው በአጫጭር ቅብብል እንዲሁም ጅማ አባጅፋር ደግሞ እረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ቡና ጥሩ የግብ እድሎችን ፈጥሮ መጠቀም ባለመቻሉ አቻ ለመውጣት ተገዷል፡፡ በ 15ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው ትዕግስቱ አበራ የመታውን ቅጣት ምት የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡ እንዲሁም ሌላኛው የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ በ35, 45 እና 54ኛ ደቂቃዎች ላይ ያገኛቸውን ግልፅ የግብ አጋጣሚዎች ሳይጠቀምባቸው በመቅረቱ ክለቡን ዋጋ አስከፍሎታል፡፡
በ ጅማ አባጅፋር በኩል 31 እና 52ኛ ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እንዳለ ብርቄ የሞከራቸዉ ኳሶች የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ቡናው ድንቅ አማካይ ክርዚስቶም ንታምቢ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡
የ አ/አ ሲቲ ካፕ ማክሰኞ ሲቀጥል
ቀጣይ ጨዋታዎች
ማክሰኞ መስከረም 30
በ9 ሰዓት
አዳማ ከተማ ከኤሌክትሪክ
በ11 ሰዓት
ቅ/ጊዮርጊስ ከመከላከያ
* * *
ረቡዕ ጥቅምት 1
በ9 ሰዓት
ጅማ አባ ጅፋር ከደደቢት
በ11 ሰዓት
ኢትዮጵያ ቡና ከ አ/አ ከተማ
* * *
ሃሙስ ጥቅምት 2
በ9 ሰዓት
መከላከያ ከአዳማ ከተማ
በ11 ሰዓት
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤሌክትሪክ