“የሕይወት ፈተና ነገን በተስፋ
እንዳልጠብቅ አያደርገኝም”
በይስሀቅ በላይ
ወደኋላ 20 ዓመት፤ በ1993 ዓ.ም በኢትዮጵያ
እግር ኳስ ታሪክ በ12ኛው የዓለም የወጣቶች
ሻምፕዮና ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈለው በአሰልጣኝ
ዲዬጎ ጋርዜያቶ የሚመራውን ብሄራዊ ቡድን
ያስታውሳሉ? በ1994 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ
ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትጵያ ውጪ ዋንጫ ይዞ
የተመለሰውን ብሄራዊ ቡድንስ ልብ ይላሉ? የዛሬው
እንግዳችን በቀለ እልሁ የዚህ ታላቅ ታሪክ አካል
ነው፡፡ በአየር መንገድ፣ በመብራት ኃይል፣ በኒያላ፣
በባንኮች፣ በአዳማ፣ በድሬደዋ ቴሌ፣ በእርሻ ሰብልና
በመጨረሻም በሻሸመኔ ከተማ ውስጥ በአጠቃላይ
ለ20 ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ
የማይረሳ እንቅስቃሴን ያደረገው በቀለ እልሁን
ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ አፈላልጎ የOldies but
Goodies እንግዳ በማድረግ ትናንትን በዛሬ መነፅር
ሊያስቃኘን ተዘጋጅቷል፡፡ በቀለ እልሁ የትናንት
ሕይወቱን ወደ ኋላ ተመለሶ ሳይሰስት በደስታም
በሀዘንም አጫውቶታል፡፡ ፍፁም ትሁት መንፈሰ
ጠንካራ እና ለፈተናዎች ያልተበገረው በቀለ እልሁ
በፌስ ቡክ ስለደረሰበት ሞራላዊ ጉዳት በስኬት
ስለሚያነሳው የጋርዚያቶ ቡድንና የመብራትን
ኃይልና የኒያላ ቆይታው፣ ለ15 ዓመታት ቆይቶ
ስለፈረሰው ትዳሩ እና ነገ ተመልሶ በአንድ ጥላ ስር
ስለመኖር ተስፋው እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች
ዙሪያ ያደረገው ቆይታ ከዚህ በታች ባለው መልኩ
ቀርቧል፡- አብሮነታችሁን አውሱን፡፡
–በእግር ኳስ በጣም የተደሰትክበት ቀን፦ በእግር
ኳስ የተደሰትኩበት ቀን በጣም ብዙ ነው፤ በእግር
ኳስ ትንሽ የማይባሉ ደስታዎችን አግኝቼበታለሁ፡
፡ ከሁሉም ግን የላቀ ቦታ የምሰጠውና በጣም
የተደሰትኩበት ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ
ብሄራዊ ቡድን ከአገር ውጪ ከርዋንዳ ዋንጫ
ይዞ የተመለሰበት፣በ1990 መብራት ኃይል ዋንጫ
ያነሳበት፣ኒያላን ከከፍተኛ ሊግ ወደ ብሄራዊ ሊግ፣
ከብሄራዊ ሊግ ወደ ፕርምዬር ሊግ ያወጣንበት ቀን
በጣም የተለየ ደስታን ያገኘሁባቸው ቀኖች ናቸው
፤ የዚህ ታሪክ አካል በመሆኔም ዛሬም ድረስ
እደሰታለሁ፡፡
–በእግር ኳስ በጣም ያዘነበትና ልቡ የተሰበረበት
ቀን፦በጣም በፍቅር የምወደው ክለቤ ኒያላ በ1996
ዓ.ም ሐዋሳ ከነማ ዋንጫ ያነሳበትና ክለቤ ኒያላ
የወረደበት ቀን ልቤ በሐዘን የደማበት ብቻ ሳይሆን
በቦክስ ሁሉ ተመትቼ ለ8 ደቂቃ ያህል ራሴን ስቼ
የተዘረርኩበትን ቀን ነው በሐዘን የማስታውሰው፡፡
–እግር ኳስ ተጨዋች ባይሆን ኖሮ በምን ሙያ
እናገኘው ነበር፦ቤተሰቦቼ በተለይ አባቴ እግር ኳስ
ተጫዋች ሳይሆን ተምሬ ዶክተር እንድሆንለት
ነበር የሚፈልገው፤ እኔ ደግሞ እግር ኳስ ተጫዋች
መሆንን ነበር አጥብቄ የምፈልገውና ከአባቴ ጋር
በጣም እንጋጭ እገረፍም ነበር፤ አስተምሬ አስተምሬ
ቅሪላ ከምትገፋ ዶክተር አትሆንም እያለ ተጫዋች
መሆኔን ይቃወም ነበር፤ ካልሲ ኳስ ሁሉ አፌ
ውስጥ ከቶ በጣም ይገርፈኝ ነበር፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ግብ፦የማላበላልጣቸው
የምንጊዜውም ምርጥ ግቦቼ ናቸው የምላቸው
ሁለት ግቦችን ነው፤ አንደኛዋ ከእህል ንግድ ጋር
ስንጫወት ያገባኃት ግብ ስትሆን ሁለተኛው ደግሞ
ከግብፅ ብሄራዊ ቡድን ጋር 2ለ2 አቻ የወጣንባትና
ለአለም ዋንጫ ለማለፍ ብልጭታ ያሳየች ጎል የእኔ
የምንጊዜም ምርጥ ግቦቼ ናቸው፡፡
- ማሰታውቂያ -
–የተሻለ ኮከብ የሚሰጠው የጨዋታ ዘመኑ
ምርጥ ጨዋታ፦ ኒያላ እያለሁ ኢት.ቡናን 3ለ0
በሆነ ሰፊ ውጤትና በምርጥ ጨዋታ ያሸነፍንበትን
ይደገም ቢባል እንዲደገምልኝ የምፈልገው ምርጥ
ጨዋታ ነው፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ አሰልጣኝ ማነው፦
ኦው…! ማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታ ዋናው
ሲሆኑ ሌላው በምርጥነት የማነሳው አሰልጣኝ
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ነው፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ተጨዋች፦ ከኤልያስ
ጁሃር ውጭ ሌላ ምርጥ ተጨዋች አላውቅም፤ከ1-10
በድጋሚ ጥራ ብትለኝ አንድ ኤልያስ ሁለት ኤልያስ
እያልኩ ነው የምዘረዝረው፡፡
-በጨዋታ ዘመኑ ያስቸገረው ተጨዋች፦ የቅዱስ
ጊዮርጊሱ አሸናፊ ሲሳይ ለእኔ በጣም አስቸጋሪ
ተጨዋች ነበር፤ በጣም የሚገርምህ አሸናፊ ሲሳይ
ፍጥነቱ፣ኳስ ሲይዝ ማስጨነቁ አስቸጋሪ እንዲሆን
አድርጎታል፤ ከችሎታው በላይ ደግሞ በታክሉም
በጣም ያስቸግረኝ ነበር፤ አጥቂ ሆኖ ታክል እየገባ
በጣም እየመታም ያስቸግረኝ ነበር፡፡
–በጨዋታ ዘመኑ አብሮት ባለመጫወቱ
የሚቆጨው፦ ከኢትዮጵያ ቡናው ካሳዬ አራጌ ጋር
ለአንድ ቀን እንኳን አብሬው ብጫወት በጣም ደስ
ይለኝ ነበር፡፡ከእሱ ጋር ባለመጫወቴ እቆጫለሁ።
–በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ማየትና
መስማት የማይፈልገው፦ ሁለት ነገሮችን ባላይ
ደስ ይለኛል፤አንደኛው አሁን አሁን የኢትዮጵያ
እግር ኳስ ጠንቅና ገዳይ ካንሰር እየሆነ የመጣው
ጉቦ እየሰጠ የሚገባ አሰልጣኝና ተጫዋችን ባላይና
ባልሰማ በጣም ደስ ይለኛል፤ በእነዚህ የእግር ኳስ
ገዳይ በሆኑ ጉበኞች ምክንያት የሚችል አሰልጣኝና
ተጨዋች ቤት ተቀምጦ የማይችሉት ከክለብ
ክለብ ይገለባበጣሉና ይሄንን ባላይና ባልሰማ ደስ
ይለኛል፡፡ሌላው ከውጪ የሚመጡትን ፕሮፌሽናል
ተጫዋቾችን በተመለከተ ነው፤ብዙ ገንዘብ ፈሶባቸው
ወደ ሃገር ቤት መጥተው ተጠባባቂ ይሆናሉ፡፡
ልምድ እንቀስምባቸዋለን ከተባለ የተሻለ ተጫዋቾች
መምጣት ነው ያለባቸው እንጂ ብዙ ገንዘብ
ፈሶባቸው ከእኛ የማይሻሉ ከሆነ ጥቅሙ ምንድነው?
የምንቀስመው ልምድስ ቤንች መሆንን ነው? ይሄም
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ባይኖር ደስ ይለኛል፡፡
–በቀለ እልሁ ራሱን በ3 የተመረጡ ቃላቶች
ሰገልፅ፦ በቀለ ያው ጭምት ነው አያወራም፣ ሜዳ
ሲገባ ለማልያው ሟች በመሆኑ ወንድሙንም ቢሆን የማይለቅ ስራ ስራ ነው ብሎ ለቤተሰብነቱ ቅድሚያ
የማይሰጥ፣ማጭበርበርን የሚጠላ ሰው ነው በቄ፡፡
–ከእግር ኳስ አጥብቆ የሚጠላው፦አጭበርባሪና
ውሸታም ሰውን አጥብቄ እጠላለሁ፤ምክንያቱም
ከቀድሞ አሰልጣኞቼ ከእነ ጋሽ ሐጎስ እነ ሰውነት
ቢሻውና አስራት ሐይሌ ያሰለጠኑኝ አጭበርባሪነትንና
ውሸታምነትን እንድጠላ አድርገው በመሆኑ
የሚያጭበረብርና የሚዋሽን ሰው እጠላለሁ፤ በጣምም
ያስጠላኛል፤ የእውነት ነገር ደስ ይለኛል፡፡
-እግር ኳስ ተጨዋች ሆኖ በማለፍ ምት ትርፍ
አግኝቷል፦ ከሰው ፍቅር ውጭ ምንም ያገኘሀት ነገር
የለም።
-በእግር ኳሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈለው
ትልቁ ደሞዝ፦ ለአየር መንገድ ስጫወት የተከፈለኝ
ሁለት መቶ ብር ነው፤ በወቅቱ በጣም ብዙ ብር
ብቻ ሳይሆን ከብዛቱ የተነሳ ምን እንደምታደርገው
ሁሉ ግራ ይገባሃል፡፡ መጀመሪያ አየር መንገድ
እንደገባሁ ሁለት መቶ ብር ተከፈለኝ፤በአመቱ ወደ
500 ብር ሲያድግልኝ ጉድ ተባለ፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ
ሰዎች እኔ መብራት ሃይል ውስጥ ከታች ያደግኩ
ይመስላቸዋል፡፡ የእኔ የመጀመሪያ ክለቤ ግን አየር
መንገድ ነው፡፡
–አሁን የአንድ ተጨዋች ደምወዝ በወር 166 ሺህ
ብር አካባቢ ደርሷል፤ ይሄንን ደምወዝ ከእሱ ዘመን
ጋር አነፃፅሮ ምነው በዚህ ዘመን ተጨዋች በሆንኩ
ይላል፦ እድሜ ወደ ኋላ አይመስለም፤ ወደ ኃላ
ተመልሼም የምፀፀት አይነት ሰው አይደለሁም፤ እኛ
ሞተን ለአሁን ዘመን ተጫዋቾች ህይወት ፈጥረናል፤
እኛ መስዋዕትነት የከፈልንበት እግር ኳስ ዛሬ ላሉት
ተጫዋቾች እንደ ፀሐይ በርቶላቸዋል፡፡ የዛሬ ዘመን
ተጫዋች ሆኖ በትንሹ ቪትስ የማይነዳ ቤትና ሌላ
ንብረት የሌለው ተጫዋች ፈልገህ አታገኝም፤ይሄ
በጣም ደስ ይላል፡፡ የእኛ መሞት እነሱን ለዚህ ትልቅ
ስኬት ባያበቃቸውና በዚህ ደረጃ ላይ ባይገኙና እንደ
እኛ ቢሆኑ ኖሮ በጣም ነበር የምቆጨው፡፡እኛ እንደ
ሻማ ቀልጠን ብርሃን ሰጥተናቸዋል፤እነሱ በእዚህ
ደረጃ ላይ በመገኘታቸው በጣም ደስተኛ ነኝ እንጂ
ወደ ኋላ ተመልሼ ከአሁኖቹ ጋር እያነፃፀርኩ በቁጭት
አልብሰለሰልም፡፡
–ከመብራት ኃይል ይልቅ በኒያላ ማልያ
ሰለመታወቁ፦ እውነት ነው ስሜ ከፍ ብሎ መጠራት
የጀመረውና የታወቀው ከመብራት ኃይል ይልቅ ኒያላ
ከገባሁ በኋላ ነው፤ መብራት ኃይል ብቅ እያልኩ
ባለበት ሰአት እድሜ ለሰውነት ቢሻው አማራው
ክልል ተወካይ የለውም ብሎ እኔንና ገነቱ ፀጋዬን
በውሰት ለደብረብርሃን ሊወስደን ሲል በወቅቱ
የነበረው አሰልጣኝ ጉልላት ፍርዴ አይቻልም ሲል
አቶ ከበረ የሚባሉ ኮሚቴ ነበሩ “ለምን መልቀቂያውን
አትሰጠውም” ሲሉት ጉልላትን “ይሄ ልጅ ቤስት
ተስላፊ ውስጥ ያለ ልጅ ነው፤ አንዋርም መጥቶ
መልቀቂያ ቢል ልሰጠው ነው? ቤስት ውስጥ
ለሚጫወት ልጅ እንዴት መልቀቂያ እስጣለሁ?”
ብሎ ሲከራከር አሳምነውት ሰውነትም ጣልቃ ገብቶ
መልቀቅያ ሲሰጠኝ ልክ ከእስር ተፈታሁ ብዬ እየሮጥኩ
የወጣሁት፤ በወቅቱ በጣም ብዙ ነገር የሚሰራበት ጊዜ
ነበር የመብራት ኃይልን ጥሩ ፍቅርና ውጤታማነት
እያጠፉት ነበር፡፡ እነ ኤልያስም ዩዞቢዮም ጨምሮ ወደ
አምስት ልጆች የተባረሩበት ቡድኑ የሚያስጠላበት
ጊዜ ነበር፤ 91 ላይ አራተኛ ነበር የወጣነው፤ በዚያን
ሰአት እኔ ከኤልያስ ጁሀር ጋር ተያይዤ ወደ ኒያላ
ገባሁ፤ እዚያም በጣም ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍነው፡፡
በአመቱ ኒያላን ወደ ከፍተኛ ዲቪዚዮን አወጣነው፤
በዚያው አመት ለብሄራዊ ቡድን ሁሉ ታጨሁ፤
በሚቀጥለው አመት ለወጣት ቡድን ታጨሁ ለዲያጎ
ጋርዜቶ ቡድን፡፡
–በወጣት ቡድን ስማቸው ስለገነነው አሰልጣኝ
ጋርዚያቶ ምን ይላል፦ኦው…! ጋርዚያቶ ለእኔ
ከአሰልጣኝም በላይም አባቴም ነው ማለት እችላለሁ፤
ለእኔ በጣም ልዩ ሰው ነው፡፡ ዝምድና የለንም
አያውቀኝም፤ ስራ ስለሚወድ ፤እኔም ሰራተኛ
ሰለነበርኩ በጣም ነበር የሚወደኝ፡፡
-ጠንካራ ትሬኒንግ ስለሚሰሩት በወቅቱ
በስማቸው ስለተሰየመው ጋርዚያቶ ጋራ /
ተራራ/፦ጋርዚያቶ ጠንካራ በሆነ ልምምድ
የሚያምን ትልቅ አሰልጣኝ ነው፤በፉቲንግ /
ሩጫ/ እና ጋራ ላይ በመስራት የሚያምን ሰው
ነው፡፡ጠንካራ ትሬይኒንግ በእኛ አገር ያልተለመደ
ነው፤ ጋርዚያቶ ብዙውን ጊዜ ለአርጀንቲናው
ውደድርም ለአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮናም
ስንዘጋጅ የሚወሰደን ኮተቤ ወደሚገኝ ጋራ
(ተራራ)ነው፡፡ ጋርዚያቶ ኮተቤ ወደሚገኘው ጋራ
(ተራራ) በተደጋጋሚ እየወሰደን ስለሚያሰራን
ጋራው(ተራራው) “ጋርዚያቶ ተራራ” የሚል ስም
ወጣለት፤ እዚህ ጋራ (ተራራ) ውስጥ ስንሰራ
መጨረሻ ላይ የማያስመልስ (የማያስታውክ)
ተጫዋች የለም፤ ከከባድነቱ የተነሳ ሁሉም
ተጫዋች ከወገቡ ዝቅ ብሎ እንደጎርፍ ውሃ
ነው የሚለቀው የሚያስመልሰው፤ እኔ ትንሽ
ደህና እባል ነበር አንድ ገዜ ግን ተራራው
ላይ ፉቲንግ ስንሮጥ እኔ ሁሉንም ቀድሜ
ሮጬ ጨረስኩና ሰውነቴን ለማፍታት መሬት
ተኝቼ እግሬን ወደ ላይ ሰቅዬ ሉዚንግ እየሰራሁ
ባለማስታወኬ እየተገረምኩ ድንገት ዞር ስል
ጋርዚያቶ አጠገቤ ደርሶ ቆሟል፡፡ እሱም ተገርሞ
እያየኝ እያለ ከየት መጣ ሳልለው ከውስጥ
ገንፍሎ ወጥቶ ለቀቅኩት (አስመለሰኝ)፤ በዚህን
ጊዜ ጋርዚያቶ አይቶ ምን ቢል ጥሩ ነው እይዞህ
በቄ ከማለት ይልቅ እኔ ሲያሰመልሰኝ እሱ “በቄ
ጉድ ጉድ”በቄ ጥሩ ነው ጥሩ ነው አለኝ፡፡ በጣም
የሚገርምህ የጋርዚያቶን ልምምድ መቋቋም
በራሱ የተለየ አቅም ይጠይቃል፡፡ በተለይ
ከቡና የሚመጡ ልጆች በጣም ይቸገሩ ነበር፤
አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች እኛ ስንሰራ ልምምዱን
ሽሽት የሽንብራ ማሳ ጫካ ውስጥ ተደብቀው
ቆይተው ነው መጨረሻ ላይ የሚቀላቀሉን፤ እኛ
ስላልለመድነው ነው ልምምዱ የከበደን እንጂ
አርጀንቲና ሄደን እንደዛ እንድንጫወት ያደረገን
የጋርዚያቶ ጠንካራ ዝግጅት ነው፡፡
–የአርጀንቲና ትውስታ አርጀንቲናዊያን
ሴቶች ተጨዋቾቹን ስለመወደዳቸው፦የአርጀንቲና
ትውስታ የሚዘነጋ አይደለም፤ ከ1 ወር በላይ
ቆይተን ጥሩ ትዝታ ይዘን ነው የተመለስነው
በተለይ የአርጀንቲናዊያን ሴቶች ጉዳይ ዛሬም
ድረስ ሳስበው ይገርመኛል፤ ምክንያቱን
ባላውቀውም ሴቶቹ በጣም ይወዱን ይፈልጉን
ነበር፡፡ ብዙዎቻችን በእነዚህ ሴቶች ተፈትነናል፡
፡ አንዴ ምን ሆነ መሰለህ ሁሴን ሰማን ጋ
የመጣችው ልጅ እንዲህ ስናልፍ አየችኝና
በምልክት ጠራችኝ፤ ማመን ስላልቻልኩ እኔን
ስላት “አዎን አንተን ብላ” በምልክት አሳየችኝ፤
አረ በቀለ በሰው አገር ጉድ ሆነ አልኩና
ወዲያውኑ አብሮኝ ለነበረው በቀለ ነገርኩት፤
በኋላ ፊቴን ሳላዞር ጠፋሁ፡፡ በጣም የሚገርምህ
ሴቶቹ በጣም ይፈልጉን ነበር፡፡ እነሰለሞንና
እስማኤልን ይዛቸው የጠፋችው እሷ ናት፤
በተለይ ሰለሞን የድሬዳዋ ልጅ ስለሆነ ቋንቋ
ስለሚችል አግባባታቸው እንዲጠፉ ያደረገቻችው
ይመስለኛል፡፡ ከሜዳ ላይ ጨዋታው የበለጠ
የሴቶቹ ሁኔታ ፈታኝ ነበር፡፡
-ለባንኮች እግር ከስ ክለብ ፊርሞ የፊርማ
ገንዘብ ሰለመከልከሉ፦ ለባንኮች በ15 ሺህ ብር
የፊርማ ክፍያ ዝውውር አድርጌ ነበር፤ በቃ
ህይወቴ ተለወጠ ብዙ ብር አገኘሁ ያልኩበትን
የዝውውር ገንዘብ ምክንያቱን በማላውቀው
ሁኔታ ካዱኝ፤ 15 ሺህ ብሩን መከልከል
ብቻ አይደለም ዓመት ሙሉ እንዳልጫወት
አድርገውኝ ውሌ ሲያልቅ አዳማ ገባሁ፡፡ እውነት
ነው 15ሺህ ብር የፊርማ ገንዘብ ከልክለውኛል፤
እኔም ለፈጣሪ ሰጥቼዋለሁ፡፡
–ከርዋንዳ ዋንጫ ይዘው በማምጣታቸው
የተሸለመውን መሬት ስለመሸጡ፦ አዎን
መንግስት የሸለመኝን መሬት 80 ሺህ ብር
ሸጬዋለሁ፤ በወቅቱ ብሩ በጣም ብዙ ነበር፤ ዛሬ
ቢሆን ደግሞ አስበው፡፡
-ሚኒባስ መኪና ገዝቶ ስለመሰቃየቱ፦እውነት
ነው አንድ ሚኒባስ ነበረችኝ፤መሬቱን እኮ
የሸጥኩት ገቢ የምታስገባ ታክሲ ለመግዛት ነው፡
፡ መሬቱን በሸጥኩበት 80 ሺህ ብር ደላላው
ምላጭ በሆነው ምላሱ አገንትሮኝ ስገዛት
ሚኒባስዋ እዳና እገዳ አለባት፤ ስለመኪና
እውቀቱ ስላልነበረኝ በጣም አሮጌና ብዙ ችግር
ያለባት ነበረች፡፡አሳበደችኝ፤ አተርፍ ባይ
አጉዳይ ሆንኩኝ፡፡ በስንት መከራ እዳና እገዳዋን
ሳስተካክል እየተበላሸች አስቸገረችኝ፤ በዚያ
ላይ የሹፌርና የረዳት ችግሮች አሉ፤በአጭሩ
በሽተኛ ልታደርገኝ ስትል በትንሽ ገንዘብ ሸጬ
ተገላገልኳት፡፡
–ከ15 አመት ፍቅረኛው ጋር ስለመለያየቱ፦
ከልጅነት ፍቅረኛዬ ጋር መለያየቴ ህይወቴ
እንዲዘበራረቅ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች
አንዱ ነው፤ ህይወቴ ላይም ትልቅ ተፅዕኖ
አድርጎብኛል፡፡ ከእሷ ጋር መለያየቴ የህይወቴ
ሃዲድም እንዲሰት አድርጓል፤ የሚገርምህ
እንኳን ያኔ ዛሬም ድረስ ረጅም አመትም
ተለያይተን ህይወቴ ካለእሷ መኖር አልችልም
ነው የሚለኝ፤ የምትወደውን ሰው ማጣት
ከባድ መሆኑን ለመመስከር ከእኔ ውጪ ሰው
መጠራት አለበት ብዬም አላስብም፤ ምክንያቱም
ህመሙን በተግባር አውቀዋለሁ፡፡ የሚገርምህ
ከእሷ ጋር ረጅም አመት ተለያይተን
የሰባት አመት ልጅም ከሌላ ሰው ወልጄ ልቤ
የሚያስበውና የሚፈልገው ዳግም ከእሷ ጋር
አብሮ መኖርን ነው፤ ፍቅሬም ዛሬም ልክ እንደ
ትናንቱ አዲስ ነው፤ የእኔ ባህሪ የተለየ ነው
መዋሸትንና ማጭበርበርን አላውቅበትም፤ አንድ
ሰው ከወደድኩኝ እስከመቃብር ነው፤ የጎዳኝም
ይሄ ባህሪዬ ነው፡፡
–ከዚህ በኋላ ሌላየትዳር አጋር ስለመያዝ
አያስብምከ፦ልቤ ከእሷ ውጪ ከሌላ ሰው
ጋር አብሬ መኖር እንደሌለብኝ ነው ደጋግሞ
የሚነግረኝ፤ የሚገርምህ እኔም የሰባት አመት
ልጅ አለኝ፤ እሷም ከሌላ ሰው ወልዳለች፡፡
እነዚህ ነገሮች ግን አብረን የመኖር ፍላጎቴን
አላደበዘዙትም፤ ያ የበኩር ፍቅሬ ዳግም ነፍስ
ዘርቶ በአንድ ጣሪያ ስር አብረን የምንኖርበትን
ጊዜ ነው የምናፍቀው፤ ይህ ሁኔታ ሌላ
እንዳልመለከትም አድርጎኛል፡፡ ጊዜው
ረጅም ነገሮችም የተለዋወጡ ቢሆኑም እንደ
እግዚአብሄር ፈቃድ ዳግም እንገናኛለን በሚል
ተስፋ ውስጥ ነኝ፡፡
–ለባለውለተኛ ተጫዋቾች ሰለሚሰጠው
ክብር፦ውስጤን በጣም የሚያመኝ ነገር
ለባለውተኛ ተጫዋች የምንሰጠው በጣም የወረደ
ክብር ነው፤ በአንድ ወቅት ለአገር ውጤት
የደከሙ የለፉ ተጫዋቾች የትም ሲወድቁ
የሚያነሳቸው ብቻ ሳይሆን ዞር ብሎ የሚያያቸው
የለም፤ይሄ በጣም ያማል፤ የድሮ ተጨዋች
ባይኖሩ እኮ እኛ አንኖርም ነበር፤ የዛሬዎቹም እኮ
እኛ ባንኖር እግር ኳሱን ከእነ ችግሩ ተሸክመን
ባናመጣው ኖሮ እነሱም አይኖሩም ነበር፡፡
አባት ሳይኖር እንዴት ልጅ ይኖራል? እኔ አሁን
በራሴ እግዚአብሃር ይመስገን በጣም ደስተኛ
ነኝ፤ ትናንት የተጨበጨበላቸው ጀግና የተባሉ
ተጫዋቾች ወድቀው ግማሹ በዳስ(በስሊፐር)
ሲሄድ ግማሹ ደግሞ የተቦጫጨቀ ልብስ ለብሶ
በየጫት ቤቱ ሲዞር ስታይ እንባህ ድንገት እንደ
ደራሽ ውሃ ይፈሳል፤ ወይ አቅም ኖሮህ ተስፋ
ሳትሆናቸው ሳትለውጣቸው ስትቀር ደግሞ
ውጪህ ብቻ ሳይሆን ውስጥህም የምር ያነባል፡
፡ የሚያግዝህን ተወውና አይዞህ የሚልህ ሰው
ማጣት ሁሉን ነገር ጨለማ ያላብስብሃል፤
የሚያውቁህ ለሰላምታ እንኳን ሰስተው እንዳላዩህ
ሆነው ያልፋሉ፤ ይሄ በጣም ከባድ ነው፡፡ ውጭ
ያሉትም ሰዎች ባለውለተኛችን ያስታውሳሉ
ይባላል፤ እነሱም ቢሆን የሚወስዱት የራሳቸውን
በቲፎዞ ነው፤ ዲስክ መንሸራተት ከገጠመኝ
በኋላ አይዞህ ወጥተህ ትታከማለህ ብለውኝ
ዞር ብሎ ያየኝ የለም፤ ቲፎዞ ከሌለህ ውለታህ
ብቻ ሳይሆን አንተም የት እንደወደክ የት
እንዳለህ ጭምር የሚያስታውስህ የለም፡፡ ይሄ
አይነቱ አካሄድ መታረም አለበት ለባለውለተኛች
ባንደርስላቸውም ምንም ባናደርግላቸውም
በአንድ ወቅት ደስታን ሰጥተውናልና ቢያንስ
አይዞህ ማለቱ እንኳን ቢለመድ ደስ ይለኛል፡፡
በፌስ ቡክ “በቀለ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ
ችግር ላይ ነው መባሉ ስለፈጠረበት ችግር፦በዚህ
ነገር ባጣም አዝኛለሁ፤ ተጎድቻለሁም፤እንዴት
እንደዚህ ተብሎ ባለቤቱ ሳይጠየቅ የውሸት ወሬ
ይፃፋል? ደግሞስ እኔ የምኖረው ሰሀራ በረሃ
ውስጥ ነው እንዴ? እኔ እኮ ወገን ቤተሰቦች አሉኝ
እኮ፤ ዛሬ ስራ በማጣቴ የማይሰለቹኝ የማይሸሹኝ
ቤተሰቦች እሉኝ ፤ ሌላ ቢጠፋ ኩርማን እንጀራም
ብትሆን የማይነፍጉኝ ቤተሰቦች እያሉኝ
የሚበላው የሚቀምሰው አጥቶ ተቸግሯል
በሚል በፌስ ቡክ ላይ በመፃፍ ሞራላዊም በስራ
ህይወቴ ላይም ትልቅ ጉዳት አድርሰውብኛል፡፡
ብዙ ሰዎች ለእኔ ያላቸው ምስልና አመለካከትም
የተሳሳተ እንዲሆንም አድርጓል፡፡ ስራ ሰርቼ
እንዳልበላም የራሱን ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል፡
፡ ብዙዎች “በቀለ በሽተኛ ነው፤ የከፋ ችግር
ላይ ነው” ብለው እምነት እንዳይጥሉብኝ የስራ
እድልም እንዳላገኝ አድርጎኛል፤በዚህ ወሬ ሰው
በሙሉ አይኔ ማየት እስከመፍራትም ደርሼ
ነበር። እኔ እኮ ሙያተኛ ነኝ፤ ሰርቼ መኖርና
መብላት እችላለሁ፤ አቅሙም አለኝ፡፡ ሰዎች ግን
መለመኛ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሰርቼ እንዳልበላ
ትልቅ ተፅዕኖም ፈጥረውብኛል፤ ሌላ አገር ቢሆን
ከሰህ ፍትህም ካሳም ታገኝ ነበር፡፡ ግን ምን
ታደርገዋለህ…?እኔ የፌስ ቡክ ሰው ስላልሆንኩ
ነው መልስ ያልሰጠሁት እንጂ ሃያ ዓመት ሙሉ
ለፍቼ ያገኘሁትን ስሜን በሃያ ሰከንድ የፌስ ቡክ
ፅሑፍ ገደል ከተውብኛል፤በሙያዬም ሰርቼ
እንዳልበላ አድርገውኛል።በቀለ እልሁ የሚለውን
ስሜን እግር ኳሱ ውስጥ ለማግኘት ሃያ ዓመት
ወስዶብኛል፤እነሱ ግን ይሄን ለማጥፋት ሃያ
ሰከንድ ነው የወሰደባቸው።
–ከፌስ ቡክ ጋር በተያያዘ 500 ሺህ ብር
አግኝቷል ስለመባሉ፦ነገሩ ምን መሰለህ ፕላኔት
ስፖርት የሚባል የሬድዮ ፕሮግራም ላይ እንግዳ
እንድሆን በስልክ ደውለው ጠየቁኝ፤ እውነት
ነው የምልህ ሲደውሉልኝ ማመን አልቻልኩም፤
እንዴት አስታውሱኝ ብዬ በጣም ከመገረሜ
የተነሳ እንባዬ ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም እኔ
የተረሳሁ የተዘነጋሁ ሰው ነኝ ብዬ ስለማስብ
በመደወላቸው ተገረምኩ፡፡ የፕሮግራሙ
አዘጋጆች ምስጋናውና መሸሻ በስልክ በቀጥታ
አስገብተው አነጋገሩኝ፤ ይሄ ፕሮግራም ከተላለፈ
በኋላ ወዲያውኑ በፌስ ቡክ “በቀለ እልሁ
የሚላስ የሚቀመስ አጥቷል፤ በሽተኛም ሆኗል”
ተብሎ ተፃፈ፡፡ እኔ እኮ ገጠመኝ ያልኩት የዲስክ
መንሸራተት ህመም ነው፤ እሱ ደግሞ ለአገሬ
እግር ኳስ ስለፋ የገጠመኝ ህመም ነው፤ ለሻሸመኔ
ከነማ ስጫወት ነው ህመሙን ያወኩት፡፡ ኳስም
ያቆምኩት በዚሁ በዲስክ መንሸራተት ህመም
ነው፤ በሽታው ደግሞ በቂ ህክምና ካገኘ የሚድን
ነው፡፡ ፌስ ቡክ ላይ የተፃፈው ግን መስራት
እንደማልችል ተደርጎ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ
በቀለ የአገር ውለተኛ ነው ገቢ እናሰባስብለት
ተብሎ ፌደሬሽኑን ይጠይቃሉ፡፡ ፌዴሬሽኑም
በሃሳቡ ይስማማና የትብብር ደብዳቤ ይፅፋል፤
“ለተለያዩ ክለቦችና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
ለበርካታ ዓመታት ያገለገለው በቀለ እልሁ
በአሁኑ ጊዜ ባጋጠመው ሕመም ምክንያት
ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልገው በመሆኑ
ለሕክምና የሚሆን ዕርዳታ የሚያሰባስብለት
አስተባባሪ ኮሚቴ የተቋቋመ ስለሆነ ለኮሚቴው
አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግ ይህን የድጋፍ
ደብዳቤ የሰጠን መሆኑን እንገልፃለን” የሚል ነው፡
፡ ፌዴሬሽኑ የፃፈው ይሄንን ደብዳቤ ከፌዴሬሽኑ
ለማውጣት መታወቅያዬን ኮፒ አድርጌ
ለመስጠት ታሰፈልጋለህ ብለው ይደውሉልኛል፤
እነሱ ለእኔ እየለፉ እንዴት እምቢ እላቸዋለሁ
አልኩና ከአገረ ማሪያም በግመል መጫኛ መኪና
ተጭኜ ሌሊቱን በሙሉ ስጓዝ አድሬ አዲስ አበባ
ገባሁ፤ የተባለውን አደረኩና ደብዳቤው አወጣን፡
፡ ከዚያ እኔ ወዲያወኑ ወደ አገረ ማሪያም
ተመለስኩ፡፡ በየፌስቡኩ ብዙ ተፃፈ ተወራ፡፡
አብዛኛውን ሰው በቀለ 500ሺህ ብር አግኝቷል
በሚል ሲያገኘኝ “እንኳን ደስ ያለህ ይሉኛል”
በዚህ በጣም እደነግጣለሁ፤ የምን 500ሺህ ብር
ነው ያገኘሁት? አረ እኔ አላውቅም ስላቸው ፌስ
ቡኩን እኮ ያጣበበው ይሄ ነው ይሉኛል፡፡ ሌሎች
ደግሞ የዲስክ መንሸራተት ህመሜን የተለየ
በሸታ ተደርጎ በፌስ ቡክ ላይ በመፃፉ ግማሹ
ሲያገኘኝ ከንፈሩን ይመጥልኛል ሌሉች ደግም
“አረ እንኳን እግዚአብሄር ለዚህ አበቃህ፤ እንኳን
እግዚአብሄር ማረህ” ሲሉኝ በቃ ዞረብኝ፡፡ የሰው
ነገር ሌላ በሽታ ሆነብኝ፤ እውነት 500 ሺህ
ብር አግኝቼ ወይም ታምሜ በሆን እቋቋመው
ነበር፡፡ በበሬ ወለደ ወሬ ለዚህ ደረጃ መድረሴ
የማልቋቋመው ሌላ በሽታ ሆነብኝ፡፡ ከሶሰት
ወራት በኋላ እነማን ከፌደሬሽኑ የወጣውን
ደብዳቤ የሰጠሃቸውን ሰዎች ለማግኘት ብደውል
ከየት ላምጣቸው፤ ስልክ አያነሱም፤ ብፈልግ
ላገኛቸው አልቻልኩም፡፡ እንኳን 500ሺህ ብር
ከፌደሬሽኑ የተፃፈውን ደብዳቤ የተቀበልኳቸው
ራሱ በሰው በሰው በመከራ ነው ፤ እኔ ከገጠመኝ
የዲስክ መንሸራተት በሽታ በላይ በሽታ የሆነብኝ
ይሄ ብቻ ነው፤ ያም ቢሆን ይሄው አለሁ
እተነፍሳለሁ፤ በአጭሩ እንኳን 500 ሺህ ብር
5 ብርም አላገኘሁም፤ እንደውም በዚህ መልኩ
በመወራቱ በአገሬ ሰርቼ እንዳልበላ አድርገውኛል፡
፡ አሁን ሁሉም እንዲያውቅልኝ የምፈልገው እኔ
ከገጠመኝ የዲስክ መንሸራተት ህመም ውጪ
ሌላ በሽታ የለብኝም፤ዕድሉን አላገኘሁም እንጂ
በሙያዬ ሰርቼ መኖር የምችልበት አቅሙ
እንዳለኝ ነው፡፡
–በስልጠና የመግፋት ህልሙን
በተመለከተ፦እኔ ከላይም ገልጭልሃለሁ እኔ
ጤነኛ ነኝ፡፡ በሙያዬ ሰርቼ መኖር የምችልበት
አቅሙም አለኝ፡፡ በ2006 ዓ.ም አካባቢ
የቢ ላይሰንስ ወሰጃለሁ፤ አሁን እንደውም
ሶስት አመት ስለሞላን የኤ ላይሰንስ ኮርስ
የምንወስድበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ በሙያዬ ከብዙ
አሰልጣኞች ባገኘሁት ልምድ ታግዤ በስልጠና
ውስጥ የበለጠ መሰማራት ነው የምፈልገው፡፡
እኔ በልመና አላምንም፤ ፀጉሬን እያከኩ ሰው
የመቀፈል ተሰጥኦውም የለኝም፤ ድሮ የሌለ ባህሪ
ዛሬ ከየት ይመጣል? አገረማሪያም ውስጥ ቡደን
ይዤ ነበር፤ ግን በተለያዩ ችግሮች ሊያሰሩኝ
አልቻሉም፤ አሁን ደግሞ እንደገና እየጠሩኝ ነው፤
አሁን እንኳን እኛን አዳዲስ ወጣት አሰልጣኞች
ቀርቶ ነባሮቹም ለመስራት የሚቸገሩበት
መጥፎ ጊዜ ነው የመጣው፤ ቡድን መያዝም
ከባድ ሆኗል፡፡ የሚያስጠጋህ በቀላሉ አታገኝም፤
ሁሌ ስለአሸናፊ፣ዮርዳኖስ፣ሙሉአለምና ኤልያስ
ጁሀርና በቀለ እያልክ እያወራህ መኖር ሳይሆን
ሌላ ኮከቦችን መፈጠር ነውና በዚህ ውስጥ
መሰማራትና ሰርቼ ማሳየት እፈልጋለሁ፡
አዲስ አበባ ከተማ ከሃያ በታች ማስታወቂያ
አውጥቶ አመልክቻለሁ፤ የሚሆነውን ማየት
ነው፤ ለስራ የሚሆን አዕምሮ እንጂ ለልመና
የሚሆን አዕምሮ ሰለሌለኝ መስራትና መስራት
ብቻ ነው የምፈልገው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሙያዬ
እንድሰራ እድሉን የፈጠሩልኝን የአገረ ማሪያም
ሰዎችን አመስግናለሁ፤ የአገር ውለታዬንና
አቅሜን አይተው በቀለ ነው መስራት ያለበት
እያሉ እየተሟገቱልኝ ብቻ ሳይሆን ደጋግመው
ጠርተውኛል፤ በዚህ አጋጣሚ የአገረማሪያም
ህዝብን ከልብ አመሰግናለሁ፤ ህዝቡንም
አገሩንም እንደምወድ ግለፅልኝ፡፡
–በችግሩ በፈተና ወቅት ከጎኑ የቆሙትን
በተመለከተ፦እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ በጨዋታ
ዘመኔ እንጂ በችግሬ ወቅት ከጎኔ የቆመ አንድም
ሰው የለም ከቤተሰቦቼ ውጪ፤ እኔ የተረሳሁ
የተዘነጋሁ ሰው ነኝ፡፡ በቀለ ችግር ላይ ነው
የሚለውን ተወውና የአገር ባለውለተኛ ነው
ብሎ የመጣ አንድም ሰው አላጋጠመኝም
ከቤተሰቦቼ ውጪ፤ “አግኘቶ ያጣ ነው፤
ተጎድቷል” ብለው ሳይሰለቹኝ እንኳን እኔን ከእኔ
አብራክ የተገኘውን የሰባት አመት ልጄን እንደ
አቅማቸው ተንከባክበው የያዙልኝ ቤተሰቦቼ
ወንድሞቼና እናቴ ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም እንደ
ሰው ዞር ብለው ባያዩኝ ኖሮ ምን ይውጠኝ
እንደነበር ሳስብ ይጨንቀኛል፡፡ እግዚአብሄር
በዚህ በፈተና ወቅት እነሱን ስለሰጠኝ ከልብ ነው
የማመሰግነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ኖሬ እንድመሰክር
ከጎኔ በመሆን ሳይሰለቹ ሳይታከቱ ለዚህ ያበቁኝን
ቤተሰቦቼን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡