THE BIG INTERVIEW WITH ASRAT HAILE
በይስሀቅ በላይ
ስሙ ለሁላችንም የቤተሰብ ያህል ነው፤ በ51 ዓመታት የእግር ኳስ አገልግሎት በወርቅ ቀለም ያሸበረቁ በርካታ ክብሮችና ስኬቶች፣ መደርደሪያዎችን ያጣበቡ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ዋንጫዎች፣ ዛሬ የሀገራ ችንን እግር ኳስ ያጥለቀለቁ አሰልጣኞችንና ተጨዋቾችን በማፍራት አንቱ የተባለ፣ ከሀገር ውጪ ዋንጫ ማምጣት የሚሰጠውን ደስታ በድሉ ቀድሞ ያጣጠመ፣ ምን ይሄ ብቻ የበርካታ ታሪኮችና ገድሎች ባለቤትም ነው፡፡ የዛሬው እንግዳችን አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው እነዚህ ሁሉ ታሪክ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ትናንት ብዙዎች የእሱን የስልጠና በረከት ለማግኘት እንደልተሻሙ ደጅ እንዳልጠኑ ዛሬ ዞር ብሎ የሚያየው፣ የሚያስታውሰው፣ የሚያከብረው ሰው አጥቷል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ እግር ኳስ በድል ያሸበረቀ የ51 ዓመት ወርቃማ ታሪክ ያለው ባለውለተኛው አሰልጣኝ ከፍቶታል ሆድም ብሶታል፡፡ የእውቅናን ካባ የደረበለት፣ ብዙ የለፋለት፣ የደማለት፣ አካሉን ያጣበት እግር ኳስ “ውለታዬን በልቶ ክዶኛል” በማለት ከእግር ኳሱ መንደር ሳይወድ በግድ መገፋቱን በምሬት ይገልፃል፡፡ “እግር ኳስ ውለታ ቢስ ነው” የሚለው አስራት ኃይሌ “ለሀገሬ በለፋሁ፣ በደከምኩ ዛሬ ምንም እንዳልሰራው ተቆጥሬ ተወርውሬያለሁ፤ በሮች ሁሉ ተከርችመውብኛል” በማለትም ይናገራል፡፡ የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የቀድሞው ባለውለተኛና እንደመፅሐፍ የሚነበብ የድል ታሪክ ያለውን የተረሳውን አሰልጣኝ “ውለታህማ አይረሳም” በማለት አፈላልጎት ስለሚገኝበት ሁኔታና ከእግር ኳስ በመገፋቱ የተሰማውን ስሜት ኮርኩሮ በማናገር ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቅርቦታል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋችነት በአሰልጣኝነት የስንት ዓመት አገልግሎት (Service) ነው ያለህ?
አስራት፡- …በተጨዋችነት፣ በአሰልጣኝነት በክለብና በብሄራዊ ቡድን በውጤትና በስኬት የታጀቡ ድፍን 51 ዓመታትን አሳልፌያለሁ፡፡ 52ኛ ዓመቴን ደግሞ ስራ ፈት በመሆን ቤቴ ቁጭ ብዬ እያሳለፍኩ ነው… (ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ድፍን 51 ዓመት በእግር ኳስ…?…በጣም የብዙ ዓመታት አገልግሎት ነው፤ካልተሳሳትኩ በዚህ ደረጃ እግር ኳሱን ካገለገሉ ግንባር ቀደሙ ወይም ብቸኛው ሰው አንተ ትመስለኛለህ… 51 ዓመታት ሙሉ ያገለገልከው እግር ኳስስ ለዋልከው ውለታ ክሶሃል…?…ወይስ ከፍሎሃል…?
አስራት፡- …ኧረ በፍፁም…!…እንደውም ውለታዬን በልቶኛል…፤…እኔ ለእግር ኳስ ከፈልኩ እንጂ… እግር ኳስ ለእኔ የከፊለው ነገር የለም…፡፡……እኔ ለእግር ኳስ ደማሁለት…፣…ላቤን አፈሰስኩለት፣… ቆሰልኩለት…፣…አካሌን አጣሁበት…፣…አፍንጫዬን ገበርኩለት…እግር ኳስ ግን ውለታዬን በልቶ ወርውሮኛል…ጥሎኛል…።…በቃ የውስጤን የሚገልፀው ቃል…እግር ኳስ ውለታዬን በልቶኛል…፣… ክዶኛል… የሚለው ብቻ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ይሄን…ያህል…? አስራት፡- …ቃላት አጥቼ እንጂ ከዚህም በላይ ብል እመኝ ነበር…፤…በተጨዋችነት…፣… በአሰልጣኝነት…የእግር ኳሱ ታማኝ ባሪያ ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ አካሌንም ሳልሰስት ገብሬያለሁ፣ ደምቻለሁ፣ ተፈንክቻለሁ፤ በአሰልጣኝነትም ሀገሬ የሰጠ ችኝን ተልዕኮ ለማሳካት የጥይት ባሩድ እየዘነበ፣ ታንክ እያጓራብኝ ለሕይወቴ ሳልሰ ስት አገልግያለሁ፡፡ እግር ኳስ ግን ይሄንን ሁሉ ውለታዬን ከቁብ ሳይቆጥር በተቃራኒው እግር ኳሱን እንደበደልኩ ለእድገቱ ሳይሆን ለው ድቀቱ የለፋው ያህል ቆጥሮ ወርውሮኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ እግር ኳስ አጥብቆ ከሚፈልጋቸው…ከሚሻማባቸው ሰዎች አንዱ ነበርክ… ዛሬስ…?
አስራት፡- …ውይ…!…ዛሬማ…የተጣለ…የተረሳ…በሩ የተዘጋበት ሰው ታውቃለህ…?…ዛሬ አስራት እንደዛ አይነት ሰው ነው…፡፡…ዛሬ እንኳን ልፈለግ… ሰዎች ሊሻሙበኝ… ቀርቶ… የት እንዳለሁ…፣… የት እንደወደኩ እንኳን አይታወቅም…፡፡… በአጭሩ ለእግር ኳሱ ሙሉ ሕይወቴን 51 ዓመት ሙሉ ገብሬ ተወርውሬያለሁ…ተረስቻለሁ፡፡ በአጭሩ የተ ረሳሁ… የተጣልኩ… ውለታዬን የተካድኩ…፣ … በሮች ሁሉ የተከረቸሙብኝ…ሰው ነኝ…፡፡
ሀትሪክ፡- …ከስልጠና ጋር ያለህ እህል ውሃ አበቃ…ማለት…ነው…? አስራት፡- …ምን ማለትህ…ነው…እኔ እኮ…በቃ…ለእግር ኳሱ የማላስፈልግ ሰው ነኝ…፤ አታስፈልግም ተብዬ ተገፍቻለሁ…ወጥቻለሁ…፤…አንድ ሲስተም አለ…ሲስተሙ እኔን አይቀበልኝም… “Error” ይላል፡፡ ይሄን ሲስተም በስልጠና ሕይወቴ ስገፋው ስፀየፈው ነው የኖርኩት፤ ስጠየፈው ስገፋው የነበረው ይሄ መጥፎ ሲስተም ዛሬ በተራው ገፍቶ አስወጥቶኛል…፡፡
ሀትሪክ፡- …ይሄ ገፋኝ የምትለው ሲስተም… ምንድነው…?
አስራት፡- …ቀላል ምሳሌ ልስጥህ…ቡድን ያወረዱ፣ሁሌም ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን የሚያሰለጥኑ፣ በውጤት ማጣት በጠዋት ከክለባቸው የተሰናበቱ አሰልጣኞች፣ በዓመት ሁለትና ሶስት ክለብ እንደ ሸሚዝ እየቀያየሩ ሲያሰጠልኑ እኔ ግን ከእነሱ የተሻለ በወርቅ ቀለም የተፃፈ የውጤትና የስኬት ታሪክ፣ አቅሙም እያለኝ እቤቴ ተቀምጫለሁ፡፡ በቃ ሲስተሙ እኔን አይቀበለኝም፤ በእርግጥ ወደ ስልጠና ለመግባት የሚወሰደውን መንገድ ወይም ሲስተም ከመከተል ከሙያው ተገፍቼ ቤቴ መቀመጥን ነው የምመርጠው፡፡ በዚያ መንገድ አለመጓዜ ከእግር ኳስ ጋር ያለኝ እህል ውሃ እንዲቋረጥ አድርጎታል፡፡ ያን ሲስተም አለመከተሌ ወድጄ ሳይሆን ተገድጄ ከስልጠናው እንድርቅ አድርጎኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …“ወድጄ ሳይሆን ተገድጄ…ከስልጠና ርቃያለሁ” ስትል…በዚህ መንገድ ባትገፋ ኖሮ በስልጠናው የመቆየት…ፍላጎቱም…ዝግጅቱም ነበረህ ማለት ነው…?
አስራት፡-…የሚገርምህ…አሁንም ውስጤ ከስልጠና መራቁን አልተቀበለውም…፤ አቆማለሁ ብዬ ሳይሆን ተገፍቼ በሮች ሁሉ ተዘግተውብኝ ነው ያቆምኩት፡፡ ሌላው ቢቀር በማማከር፣ በመርዳት እግር ኳሱን ማገዝ ልምድና ዕውቀቴን ማካፈል የምችልበት አቅሙ አለኝ ብዬ ነው የማምነው፡፡ ያ የተንጋደደ እግር ኳሱን ሳይሆን ግለሰቦችን የሚጠቅመው ሲስተም ገፍትሮኝ እንጂ በዚህ ደረጃ የማገዝ ሃሳቡም የአእምሮ ዝግጅቱም ነበረኝ…ግን ምን ታደረገዋለህ…
ሀትሪክ፡- …እንደ ድፍረት አትቁጠርብኝና ብዙዎች ግን አስራት ጨርሷል…እድሜውም ገፍቷል… ከዘመኑ የስልጠና ሲስተም ጋርም ተቆሯርጧል… የሚሉ አሉና…ይሄን አባባላቸውን ትቀበለዋለህ…?
አስራት፡- …(እንደመሳቅ እያለ)… ይሄ የስልጠና ሲስተም ምናምን የሚባለውን ነገር እንኳን ተወው…፤…የስልጠና ሲስተም እያሉ የሚደሰኩሩት ለማታለል ነው፡፡…እንደዚህ የሚሉ ሰዎችን የስልጠና ሲስተም የሚባለው ምንድነው…?…ብትላቸው አይመልሱልህም…፤…ብቻ ለማደናገርና በአንተ ላይ በሩን ከርችመው ለመዝጋት የዘመኑ የስልጠና ሲስተም እያሉ ያወራሉ…፤…ግን እኔ አንድ እውነት ልንገርህ…እነሱ ከሚያወሩት በላይ ለዘመኑ የስልጠና ሲስተም ቅርብ ነኝ፤ ከእነሱ በተሻለም የተሻለ ነገር የመፍጠር አቅሙ አለኝ፡፡ አሁን አይደለም ድሮም ለዘመኑ በጣም ቅርብ ነበርኩ፡፡ ዛሬ ጅምናዚየም ሠፈሩን ሁሉ ከማጥለቅለቁና ጥቅሙ ከመታወቁ በፊት ጊዮርጊስ እያለሁ እግዚቢሽን ማዕከል በጅምናዚዬም የታገዘ ስልጠና የሰጠሁ የመጀመሪያው ሰው ነኝ፡፡ በወቅቱ እኔ ይሄንን በማድረጌ ግንዛቤ ሌላቸውና ከዘመኑ ስልጠና ጋር የተጣሉ ከእኛ ወዲያ ፉትቦል2 አዋቂ ባዮች “ይሄ ሰውዬ ምን እየሠራ ነው ልጆቹን ቦዲ ቢልደር ሊያደርጋቸው ነው እንዴ? ብረት የሚያሰራቸው” በማለት ይናገሩ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ከዘመኑ ስልጠና ጋር ቅርበት የነበረኝ ዛሬ ከረፊደ ሳይሆን ገና በጠዋቱ እንደነበር ይሄ ማሳያ ነው፡፡ ሁሌም የነበረውን ወይም የምታውቀውን ብቻ ይዘህ አትቀመጥም፤ ዳይናሚክ (ተለዋዋጭ) ከሆነው እግር ኳስ ጋር ራስህን አግባብተህ መጓዝ ግድ ነው፤ ዛሬ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ አለም መዳፋችን ውስጥ ናት፤እቤቴ ተቀምጬ አለምን ማሰስ ያለ አስተማሪ መማርና ከዘመኑ ስልጠና ጋር ራሴን አግባብቼ መራመድ እችላለሁ፡፡ ብዙዎች ለሁለትና ለሶስት ቀን ስልጠና ሄደው መምጣታቸውን ነው እንደ መብቃት የሚቆጥሩት፤ በሁለትና በሶስት ቀን ስልጠና ብቻ የበቃሁ ነኝ ማለት ለእኔ ከባድ ነው፡፡ የሁለትና የሶስት ቀን ስልጠናን በዚህ ደረጃ ከመጥራት ይልቅ ለጉብኝትና ለሽርሽር ነው የሄዱት የሚለው ቃል ይገልፀዋል፡፡ ከዘመናዊ ስልጠና ጋር እኔ አልተጣላሁም፤ እንደውም በቂ ጊዜ ስላለኝ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ወዳጅ ነኝ፡፡ ዘመናዊ ስልጠና የሚሉት አውሪዎቹም፣ አሰሪዎቹም፣ ተናጋሪዎቹም በትክክል አውቀውት ሳይሆን የማይፈልጉትን ሰው ከአካባቢው ዞር ለማድረግ የሚጠቀሙበት ቃል ነው ለእኔ፡፡
ሀትሪክ፡- …ከዕድሜ ጋር…በተያያዘ ላነሳውልህ ጥያቄ መልስ አልሰጠህኝም ምነው ዘለልከው…? …አስራት ጨርሷል…፣…ዕድሜውም ገፍቷል…፣ የአሰልጣኝነት ነገርም…በቅቶታል…የሚሉ አሉና… መልስህ ምንድነው…?
አስራት፡- …(አሁንም ሳቅ)…ብዙ ይባላል…፤ … አስራት አርጅቷል…፣…ሸምግሏል…፣… በቅቶለታል…ይላሉ፡፡ እኔ ይሄንን ነገር ስስማ በጣም እስቃለሁ፤ ለዚህ ክብር መብቃት እኮ መታደል ነው፤ ግን ወደ እውነታው ስትመጣ መታየት ያለበት የዕድሜ ቁጥር ነው ወይስ አቅምህ…?…ማሰልጠን ይችላል…?…አይችልም…?…የውጤት ታሪኩ…ልምዱና እውቀቱ ነው …መታየት ያለበት ወይስ የዕድሜው ቁጥር ነው…?…ደግሞም እኮ የዕድሜ ቁጥር ቢታይም እኮ እኔ 66 ዓመቴ ነው፡፡ ያን ያህል ሸምግዬ መራመድ ያቃተኝ…፣…በሰዎች ተደግፌ የምሄድ ሰው አይደለሁም፤…ይሄ ዕድሜ እኮ ይበልጥ እንደ ወይን የምትጣፍጥበት፣…የምትበስልበት… ስለሆነ ጥሩ ስራ የምትሰራበት ዕድሜ ነው…፡፡…እንዲህ ብዬ በመናገሬ አለመሳሳቴን የሚያሳይ አንድ ቀላል ምሳሌ አሁንም ልስጥህ…
ሀትሪክ፡- …ምን አይነት ምሳሌ…?
አስራት፡- …እስቲ አንዴ የአለምን እግር ኳስ የሚዘውሩትን ሰዎች ተመልከታቸው…፤…ከእኔ የበለጠ እድሜ ያላቸው እድሜ ጠገቦች ናቸው…፡፡ …ለምሳሌ በሩሲያው የዓለም ዋንጫ የኤኳዶር ብሄራዊ ቡድንን ይዘው የቀረቡትን ታባሬዝን ታስታውሳቸዋለህ…?…እሳቸው እኮ የእኔ ታላቅ ናቸው፤ 72 ዓመታቸው ነው።…በዚያ ላይ የሚራመዱት በድጋፍ (በዱላ) ታግዘው ነው፤ የኤኳዶር ፌዴሬሽን ግን ብ/ቡድኑን ያውም በታላቁ የዓለም ዋንጫ ላይ ይዘው እንዲቀርቡ አንስቶ ሲሰጧቸው የዕድሜያቸው ቁጥር 72 ላይ መድረሱን አልያም በክራንች እየታገዙ መራመዳቸውን ሳይሆን ጭንቅላታቸውን ነው ያየው፡፡ …ጭንቅላታቸው መስራት ይችላል አይችልም…? የሚለውን መዝነው…ነው…የሀገር ብ/ቡድን የሰጧቸው፡፡ የክርስታል ፓላሱን አሰልጣኝ ሮይ ሆጅሰን 70 ዓመታቸው ነው፣ የባየር ሙኒኩም ሄይንክስ 72 ዓመታቸው ነው፣ ራኒዬሪም 66 ዓመታቸው ነው፣ቬንገርም አሁን እረፍት ላይ ሆኑ እንጂ እስከ 68 ዓመታቸው ያሰለጥኑ ነበር፡፡ እነዚህ አሰልጣኞች በዝቅተኛ ደረጃ ሳይሆን የዓለማችን ታላቅ ሊግ በሆነው ፕርምዬር ሊግ ላይ በብቃት እንዳይሰሩ ዕድሜ ተፅዕኖ ሲፈጥርባቸው አልታየም፡፡ የትም ባልደረሰው በእኛ ሀገር እግር ኳስ ግን አንተን ከቦታው ዞር ለማድረግ የማይለጠፍብህ የማይደረደርብህ ምክንያት የለም፤እኔን ከስልጠና የገፋኝ ይሄ አይደለም፤ የዝርፊያ ሲስተም ውስጥ አለመግባቴ ብቻ ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …በዚህ ደረጃ መገፋትህ እንደሰው…፤…እንደ ሙያተኛ…በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ይፈጥራል…?
አስራት፡- …ሁለት አይነት ነገር ነው የሚሰማኝ…፤ … የመጀመሪያው…ከስልጠናው የገፋኝ በተበላሸው ሲስተም አልሄድም ማለቴ፣በሚወራው ሙስና ውስጥ ተሳታፊ አለመሆኔ፣ ለቀጣሪዎች አለመመቸቴ በመታወቁ የክለቦች ወይም የኮሚቴዎች ምርጫ አለመሆኔ ከመከፋት ይልቅ ደስተኛ ያደርገኛል፤ ምክንያቱም ይሄ ነገር ስራ ቢያሳጣኝም፣ከሙያው ቢገፋኝም ለሙያው መከበር የከፈልኩትን ዋጋ ስለሚያሳየኝ፣ከህሊና ወቀሳ ነፃ መሆኔን ስለሚያረጋግጥልኝ በዚህ እደሰታለሁ፡፡ በሌላ መልኩ ግን በዝርፊያው ተባባሪ አልሆንም ብዬ መቆርቆሬ ሊያስከብረኝ፣ሀውልት ሊያስቆምልኝ ሲገባ መገፍተሬና መወርወሬን ሳስብ በጣም አዝናለሁ፡፡ እኔ ከያዝኩት የጠነከረ አቋም ይልቅ እግር ኳሱን የማይጠቅም፣ ለውጤት የማይረዳ ነገር ሲከበር ያንን ያደረጉ ከመወገዝ፣ ከሙያው ዞር እንዲሉ ከመደረግ ይልቅ ሲሾሙ ሲሸለሙ ስታይ የበለጠ የሀዘን ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ በያዝኩት አቋም፣ ለእግር ኳሱ በሰጠሁት የረጅም ዘመን ታማኝ አገልግሎት ክሬዲት ሊሰጠኝ ሲገባ በዚህን መሰሉ ሰው ሰራሽ ችግር መገፍተሬ በጣም እንዲሚያበሳጨኝ፣ እንደሚያሳዝነኝ አልሸሽግህም፡፡
ሀትሪክ፡- …ይሄ ሀዘንህስ ምሬት ውስጥ ከቶህ…“…ምን ቀን ነው…እዚህ ሙያ ውስጥ የገባሁት…?”…ብለህስ…የተቆጨህበት አጋጣሚ የለም…?
አስራት፡- …እኔ ባሳለፍኩት የእግር ኳስ ሕይወቴ አልከፋም…፤…አልቆጭም፡፡ ምክንያቱም ስለ ራስ ለመመስከር ወይም ለጉራ ሳይሆን በእግር ኳስ ሕይወቴ ማንም ሊክዳቸው ማንም ሊያጠፋቸው የማይቻል በወርቅ ቀለም ተፅፈው የተቀመጡ ውጤታማ ስራዎችን ሰርቼ ነው ያለፍኩት፡፡በተጨዋችነትም፣በአሰልጣኝነትም ሙሉ ሕይወቴን በስኬት ያሸበረቀ የእግር ኳስ ሕይወት ነው የነበረኝ፡፡ አሁን አሁን ግን የሚሰራው ሰው ሰራሽ ችግር በውጤቴ፣ በዕውቀቴና በልምድ ችግሬ ሳይሆን በተበላሸው ሲስተም ውስጥ ባለመሄዴ ምክንያት መገፍተሬንና መጣሌን ሳስበው ብስጭት እልና ምን ቀን ነው እዚህ ሙያ ውስጥ የገባሁት…ብዬ እማረራለሁ፡፡ እግር ኳሱና ጥቂት ሰዎች ውለታዬን ሲነጥቁኝ ለዚህ ሀገር እግር ኳስ ምንም እንዳልሰራሁ እንዳልለፋሁ ተቆጥሬ ስወረወር ምን ቀን የመጣሁት ብዬ በጣም እቆጫለሁ፡፡ አንተ ይሄን ትላለህ እንጂ እንደውም ወደ ኋላ ተመልሼ ያኔ ምነው በጠፋሁ ሁሉ እስከማለት የደረስኩበት አጋጣሚ ሁሉ አለ…
ሀትሪክ፡- …“ያኔ…ምነው…በጠፋሁ…እስከማለት የደረስኩበት አጋጣሚ ነበር…”…ስትል…?
አስራት፡- እንዴ…የሚሰራው ስራ እኮ…ከዚህ በላይ ብታስብና ብታደርግም አይፈረድብህም…፡፡… እኔ ሀገሬን በጣም የምወድ ሰው ነኝ…፤…”ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ለእኔ የተለየ ስሜት ነው የሚሰጠኝ፡፡ ለዚህ ታላቅ ስም ክብርና ፍቅርም ስላለኝ ነው በአሰልጣኝነት ሙያዬ ለሕይወቴ ሳልሳሳ ጥይት በሚዘንብበት ታንኮች በሚያጓሩበት ቦታ ሁሉ ግዳጄን ስወጣ የነበረው፡፡ በጨዋታ ዘመኔ የተለያየ ሀገር ሄጄ በዛው ሄጄ እንድቀር ሰዎች ሲያግባቡኝ “…ሞኝ አትሁን…”…ሲሉኝ እንዴ…!… ሀገሬ ኢትዮጵያን… ወላጅ እናቴን… ለማን ትቼ…? ብዬ አሻፈረኝ ነው ያልኩት፡፡ “ብዙ ሰዎች ብዙ ነገር እናረግልሀለን ወደ ሀገር ቤት አትመለስ” ብለው ቢያግባቡኝም ሞቼ እገኛለሁ…ከሀገሬ ውጪ የትም መኖር አልፈልግም…መሞትም ካለብኝ እዚሁ በሀገሬ ነው ያልኩት…ለሀገሬ የተለየ ፍቅር ስላለኝ ነው፡፡…አሁን ግን የሰዎች እኩይ ስራ…ሀገርህን የሚያስጠላ ነው…፡፡…ከዚያም አልፌ ወደ ኋላ ብዙ ዓመትን ተመልሼ ምነው ያኔ ጥፋ ስባል ሀገሬ ብዬ በጠፋሁ ብዬ እንድቆጭ ሁሉ እያደረገኝ ነው፤ከሚደረገው አንፃር…ከዚህ በላይም ባስብ አይፈረድብኝም…፤…በሌላ ሀገር ቢሆን እኮ…
ሀትሪክ፡- …በሌላ ሀገር…ስትል…?
አስራት፡- …በሌላ ሀገርማ…እንደዚህ አይነት የ51 ዓመታት በውጤት ያሸበረቀ አገልግሎት የሰጠ ሰው የትም አይጣልም፤…የትም አይወረወርም…።…እኔ ይሄንን አገልግሎት የሰጠሁት፣ የውጤት ታሪክ ያፃፍኩት፣ይሄንን ሁሉ ለሀገር የሚጠቅም ተጨዋች ያፈራሁት…ሌላ ሀገር ቢሆን ኖሮ ቢያንስ አልጣልም…፤…ተከብሬ፣ውለታዬ ተቆጥሮ አኖር ነበር፡፡ ምክንያቱም እኔ አንድ ነገር ብቻ ይዤ ብቅ ያልኩ ሰው አይደለሁም፤ይሄን የምናገረውም ለእኔ ብቻ አይደለም…፤…ባለውለተኞች፣…ለሀገር የለፉ…፣…የደከሙ ሰዎች መከበር እንጂ ውለታቸው ተበልቶ እንደ እኔ መጣል የለባቸውም…፡፡ …መከበሩ ይቅር…ግን…የትም መጣልና መወርወር የለብኝም…፡፡…በዚህ የተነሳ ነው…እግር ኳሱን ውለታ በል…እስከማለት የደረስኩት…፡፡
ሀትሪክ፡- …ከዚህ ከምሬትህ በመነሳት…የመጨረሻው ልጅህ ከፍተኛ ደረጃ መድረስ የሚያስችል ችሎታ እያለው…በኳስ ገፍቶ አንዳይሄድ እስከመመኘት ደርሰሃል…የሚል ነገር ሰምቻለሁ…፤…እስኪ ይሄንን አጫውተኝ…?
አስራት፡- እንዴ…!…ምን…ማለትህ…ነው…?…51 ዓመት ያገለገልኩት…የእኔን ውለታ እንክት አድርጎ የበላው እግር ኳስ…እንዴት ለልጄ ይሆናል…ብዬ ላስብ…?…በልጄ ምርጫ መግባቴን ባላምንበትም…በእግር ኳስ እንዲገፋ ድጋፍ በማድረግ በርታ አይዞህ ማለቱን ውስጤ እሺ አላለኝም፤…ከኳስ ይልቅ ወደ ትምህርቱ እንዲያዘነብል ነው ፍላጎቴ፡፡ ምክንያቱም እኔን የበደለኝ፣ ውለታዬን የበላው እግር ኳስ…በልጄ ላይ መጥፎ ታሪኩን እንዲደግም አልፈልግም…፡፡…አንተ የእኔን ትላለህ እንጂ…የልጄን ፍላጎትና ስሜት ሳየው በስጋት የተከበበ ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ ከስልጠናው ተገፍትሬ ውለታዬ ተረስቶ…ተጥዬ እቤቴ በመቀመጤ በጣም ሲቆጭ ሲያዝን አየዋለሁ፡፡ እንደውም አንዳንዴ ነገሮች ውስጡን በጣም እየረበሹት “ኳስ ለአባቴ ያልሆነ…የአባቴን ውለታ የበላ ኳስ ለእኔ ምን ያደርግልኛል…?”…የሚል መጥፎ ስሜት ውስጡ ተፈጥሮ ወደ ትምህርቱ አዘንብሏል…፡፡…አሁን እግዚአብሔር ይመሰገን በሚቀለው ዓመት ይመረቅልኛል፡፡ ግን በኳሱ ቢገፋ ደግሞ የበለጠ ከፍተኛ ደረጃ መድረስ የሚያስችል አቅም ነበረው፡፡ ቁመቱ፣ የኳስ አያያዙ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚችል ይናገራል፡፡…አሁን…አሁን…በቤተሰቤ፣…በጣም ቅርብ በሆኑ ሰዎች…በእኔ ላይ በደረሰው ነገር በመበሳጨት “…አስራት ኳሱ ላይ ያባከነውን ጊዜ…ምነው በሌላ ሙያ ላይ ቢያባክነው ኖሮ…፤…ምክንያቱም በእሱ ዲስፕሊንና ታማኝነት…ትልቅ ደረጃ መድረስ ይችል ነበር” እስከ ማለት…ሁሉ ደርሰዋል…፡፡
ሀትሪክ፡- …አስራት… አሁን ከስልጠና ከራክ…ዓመታት ተቆጥረዋል… 51 ዓመታ ትን… ለእግር ኳስ የሰዋው አስራት…በምንድ ነው የሚተዳደረው…ምንድነው ገቢው…?
አስራት፡- …በአሁን ሰዓት…ምንም መተዳደሪያም…ገቢም የለኝም…፤…51 ዓመት አገልግዬ…ባዶ እጄን አጨብጭቤ ነው የወጣሁት…፡፡…አሁን የምተዳደረው በመድኃኒያለምና…እኔ ድግሪ ሳይኖረኝ የድግሪ ባለቤት እንዲሆኑ አድርጌ ባስተማርኳቸው ልጆቼ ነው…፡፡ልጆቼ ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ በማስተማር ባልደክምና ለቁም ነገር ባላበቃቸው ኖሮ ዛሬ አስራት የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ሲለምን የሰው እጂ ሲጠብቅ ነበር የሚኖረው፡፡ እግዚአብሐር ይመስገን ልጆቼን ማስተማሬ ድግሪ ሳይኖረኝ የድግሪ ባለቤት በማድረጌ የሰው እጅ ከማየት አድኖኛል፡፡ በፊት በስልጠና ላይ እያለሁ ቤቴን ያስለመድኩት የሞላ ነገር ነው፤…የእኔም ኪስ እንደ አሁኑ ጎደሎ አልነበረም፡፡ ዛሬ ምንም ገቢ ስለሌለኝ ይሄ ታሪክ ሆኖ ቢቀርም በፈጠረኝ አምላኬ ድጋፍና በቤተሰቤ እገዛ ልክ እንደ ድሮው ሙሉ ሕይወት እየኖርኩ ነው፡፡ ጭንቅላቴ ነው የተራበው ወይም ያልጠገበው እንጂ ሆዴ ምግብ አጥቶ ተርቤ አላውቅም፡፡
ሀትሪክ፡- …አሁን ከሙያው ርቀህ መቀመጥህ በቤተሰቦችህ ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዴት ትገልፀዋለህ…?
አስራት፡- …እነሱ ይደብቁኛል እንጂ በሁኔታው በጣም አዝነዋል…፣ተከፍተዋል፤…ግን እነሱ አዝነው ተከፍተው…እኔን ላለማስከፋትና ላለማሳዘን ሲሉ…ምንም ያልተከፉ ያላዘኑ…መስለው እንደሚኖሩ አውቃለሁ፡፡ በፊት በስራ ምክንያት ውጭ ውጭ ስል እንዳልነበር አሁን ከጠዋት እስከማታ እቤቴ መቀመጤን ሲያዩ በጣም ያዝናሉ፤ በጣምም ይቆጫሉ፡፡…ለአስራት የሚገባው እኮ ይሄ አይደለም…ብለው ይንገበገባሉ…፤…ግን እንዳልኩህ… በተለይ ባለቤቴ ወ/ሮ በየነች… በጣም ጠንካራ በፈተና ጊዜ ከጎንህ በመሆን ሁሉን ነገር የማስረሳትና የመለወጥ ጥበብ ያላት ሴት መሆንዋ ነገሮች ሁሉ መልካቸውን ቀይረው በደስታ በፍቅር እንድንኖር አድርጎኛል፡፡ በፊትም በስራ ዘመኔ የስኬቴ ምክንያት እሷው ነበረች፤ ሲከፋኝ፣በውጤት ማጣት ስበሳጭ…አፅናንታኝ የተለያዩ ሴራዎችን አክሽፋ…ለዚህ ያበቃችኝ እሷው ናት…፡፡
ሀትሪክ፡- …በአንተ የስኬታማነት ምስጢር ውስጥ የባለቤትህ ሚና ላቅ ያለ እንደነበር ስትናገር አንድ ነገር ትዝ አለኝ…፤…በቅርቡ በአየር መንገድ አዲሱ ስካይ ላይት ሆቴል በተደረገ ልዩ ፕሮግራም አንተም በተለይ ባለቤትህ ወ/ሮ በየነችም ከተለያዩ ዘርፎች የተመረጡ ባለውለተኞች ሲሸለሙ እሷም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አብራህ ተሸልማለች…ይሄ አጋጣሚ ምን…ስሜት ፈጠረብህ…?
አስራት፡- …ከፍተኛ የደስታ ስሜት…ይሄን ነገር እንኳን አነሳኸው…፤…እው ነት ለመናገር እኔ ከዚህ በፊት በሀገር ውስ ጥም ከሀገር ውጭም የተለያዩ ታላላቅ ሽል ማቶችን አግኝቻለሁ…አንዳቸውም ግን እሷ ስትሸለም የተሰማኝን ልዩ የደስታ ስሜት አልሰጡኝምብልአላጋነንኩም…፤…በጣም ነው የተደሰትኩት…፡፡…ምክንያቱም የእኔ የረዥም ዓመት የስኬታማነት ምስጢር…ዋና መሀንዲሷ እሷ ስለነበረች ይሄ ነገር ከብዙ ጊዜ በኋላ ተገልፆ በአደባባይ በጣም ታላላቅ ሰዎች ባሉበት በተለያየ ዘርፍ ታላቅ ስራ ከሰሩ ሰዎች እኩል ክብርና እውቅና ተሰጥቷት በመሸለምዋ ከእኔ መሸለም በላይ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎታል።…ይሄ እውቅናና ክብር የተሰጣት ደግሞ እንኳን እሷን እኔንም የሚያስታውሰኝ ይኖራል ብዬ ባላሰብኩበት ባልጠበኩበት ሰዓት መሆኑ አጋጣሚውን የተለየ ነገር አድርጎታል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ውለታችንን ቆጥረው አክብረው ያከበሩንን፣ ተረስተናል ብለን ባሰብንበት ሰዓት አክብረው ይገባችኋል ብለው እኔንም ባለቤቴንም በታላላቅ ሰዎች ፊት ያከበሩንን የፕሮግራሙ አዘጋጆችን አብርሃምንና የቡና የጀርባ አጥንትና ደጋፊ የሆኑትን አቶ ወርቅሸትን ጭምር በዚህ አጋጣሚ ከልብ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ የምትሰሩት ስራ ሁሉ ይባረክ፣ ሰው እንዳከበራችሁ…እናንተንም በስራችሁ ተከበሩ ብዬ መመረቅን ነው የምወደው…፡፡…ከእነሱ ውጪ አንድ ትልቅና የተከበረ ሰውም… ማመስገን እወዳለሁ…ከፈቀድክልኝ…?
ሀትሪክ፡- …መድረኩን ለቅቄልሃለሁ…ቀጥል…?
አስራት፡- …በወቅቱ በርካታ አንቱ የተባሉ ሰዎች…ለእኔም በተለይ ለባለቤቴ ልዩ ክብርና ድጋፍ ቢሰጡንም…በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ክብርት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞንን በተለይ ማመስገን እወዳለሁ፡፡ ክብርት አምባሳደር ከባለቤቴ ጋር በመተዋወቅ የተለየ ክብር ነው የሰጧት፤ “…ጀርመን ሀገር…እግር ጥሎሽ ከመጣሽ…የትም ስትሄጂ እኔጋ ነው የምታርፊው…”…በማለት “ከጀግና ወንድ ኋላ ያለሽ ጀግና ሴት ነሽ ብለው ካወደሷት በኋላ ወደ እኔ ዞር ብለው “አንተም ይህቺን የመሰለች ጀግና ሴት አገባሁ ሳይሆን አፈስኩ በል” በማለት ቀልድ ጣል አድርገዋልና እሳቸውም ላሳዩት ክብር በተለይ ሳላመሰግናቸው አላላፍም…፡፡
ሀትሪክ፡- …እስቲ አሁን ግላዊና ቤተሰባዊ ጥያቄ ወጣ ልበልና አንድ ነገር ላንሳልህ…፤…ዛሬ ፎርማቱ ይቀየር እየተባለ የሚብጠለጠለው የፕርምዬር ሊጉን ፎርማት ከመነሻው ሲቃወሙ ከነበሩት ሰዎች አንዱ አንተ መሆንህን ሰማሁ…እውነት የዛሬውን አደጋ ቀድመህ በመፍራት ተቃውመህ ነበር…?
አስራት፡- …እንደው እንደ ትንቢት ተናጋሪ እንዳትቆጥረኝ እንጂ ይሄ ፕሪምየር ሊግ የሚባለው ፎርማት ገና ሲጀመር በመጀመሪያ የተቃወምኩት እኔ ነኝ፤ ዛሬ እግር ኳሱን ከወዲያ ወዲህ እያወዛወዘው የክለቦችን፣ የተጨዋቾችን ብሎም የሀገር አቅምን እያናጋ ከፊፋና ከካፍ ሕግ እየተጣላ ያለውን ፎርማት አያዋጣንም የትም አያደርሰንም አደጋ አለው ብዬ በግልፅ ተቃውሜ ያለሁ፤ በተለይ ቡድኖች በጎሳ፣ የፓርቲ በሚመስል፣ በአካባቢ ስም መሰየማቸውን አምርሬ ተቃውሜያለሁ፡፡ ይሄን በድፍረትና በግልፅ አነ አቶ መላኩ ጴጥሮስ እነ አቶ ተሾመ ቶጋ ባሉበት በመናገሬም ብዙዎች ደንግጠው “አስራት ምን አይነት የዋህ ሰው ነው? ለምን ዝም ብሎ ይጋፈጣል? የበሬ ግንባር ለምን ይሆናል?” ብለው ስጋታቸውን ሁሉ እስከመግለፅ ደርሰው ነበር፡፡ እኔ ግን በወቅቱ ፖለቲካ አይደለም የተናገርኩት፤ ያመነኩበትን በሀገር በሕዝብ ላይ የሚያመጣውን ነው ቀድሜ የተናገርኩት፡፡ በዚያ ሳላበቃ በወቅቱ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩትን አቶ መላኩ ጴጥሮስን ምን እንዳልኳቸው ታውቃለህ…?
ሀትሪክ፡- … ምን አልካቸው….?
አስራት፡-…አቶ መላኩ…ለመሆኑ ኳስ ተጫውተህ ታውቃለህ…? አልኩት… እሱም “በክለብ ደረጃ ባይሆንም በሰፈር፣ በት/ቤት ደረጃ ተጫውቻለሁ” ብሎ መለሰልኝ፡፡ እኔም ወዲያውኑ ለዚህ ነው ራቅ ያለ ቦታ በመኪና ተጉዞ መጫወት የሚያመጣውን ጉዳት ያልተረዳኸው፤ እኔ በተጫዋችነትም በአሰልጣኝነትም አውቀዋለሁ፡፡ በዚህ መልኩ የሚደረግ ጨዋታ በልምምድ፣ በጨዋታ፣ በተጨዋች ብሎም በሀገር እግር ኳስ ላይ ትልቅ ጉዳት ያደርሳል፡፡ በዚያ ላይ በአካባቢና በፓርቲ ስም ቡድኖች መቋማቸው ጉዳቱ ያመዝናል ብዬ በግልፅ ተቃውሜያለሁ፡፡ ዛሬ ይሄንን ያህል ዓመት ውድመት ከደረሰ በኋላ ጥያቄው እየተነሳ ነው፤ እግር ኳሱ ወደ ሰፈርነት ወደ ጎሳነት በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀየረ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እግር ኳስ ሜዳ መሆኑ ቀርቶ የፖለቲካ መናኸሪያ እየሆነ ነው፡፡ እንደምታየው በየቦታው ጨዋታ መቋረጥ፣ ሰዎች በቡድን ተቧድነው መፈነካከት፣ መደማማት፣ መሞት እየሆነ ነው፡፡ ይሄ እግር ኳሱን ከመጥቀም ይልቅ ለውድቀቱ መፋጠን የሚያበረክተውን ነው የሚያሳየው፡፡
ሀትሪክ፡- ስለዚህ ያኔ የተናገርኩት ወይም የፈራሁት እየደረሰ ነው፤ ፎርማቱ አያዋጣም እያል ነው…?
አስራት፡-…ፎርማቱ ይሄን ያህል ዓመት በመካሄዱ የሰጠው ጥቅም ይጠና…፤…ጠቅሞናል… ጎድቶናል…የሚለው በአግባቡ ይፈተሽ፡፡ ከዚያ ትርፍና ኪሳራውን በመለየት አንድ ወሳኔ ላይ መድረስ ይችላል፡፡ የተለየ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች ካልሆኑ በስተቀር እግር ኳሱ አለመጠቀሙ በግልፅ እየታየ ነው፡፡ ጭራሽ አሁን መስፈርቱን ስቶ የእግር ኳስ ሜዳነቱን ስቶ ወደ ጦርነት ሜዳ እየተቀየረ ነው፡፡ የክለቦች ስያሜያቸው አወቃቀራቸው የዘር፣ የማንነት ፖለቲካን ከማቀንቀን መውጣት አለበት፤ በዚህ ደረጃ የተዋቀሩ ከዚህ መስመር እንዲወጡ መደረግ አለበት፤ ምክንያቱም የካፍና የፊፋ ሕግ ይሄን አይፈቅድምና፡፡ ለምሳሌ በእነ አቶ ይድነቃቸው አመራር ዘመን ክለቦች ሀማሴን…እያሉ መሰየማቸው ከካፍና ከፊፊ ሕግ ጋር እንደሚጣላ በማወቅ ስማቸውን እንዲያስተካክሉ ካላስተካከሉ እንደሚታገዱ እንደሚፈርሱ በማስጠንቀቅ ስማቸውን ያስተካከሉበት አጋጣሚ ነው የነበረው፤ አሁንም ይሄ መታሰብ አለበት፡፡ የክለቦች ስያሜ ከዘር፣ ከሀይማኖት፣ ከፓርቲ ስም የፀዳ በማድረግ የስፖርቱን የሰላም አየር መመለስ ይቻላል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ሀትሪክ፡- በሌላ ወገን ደግሞ የፎርማቱ መቀየር ብቻውን ለውጥ አያመጣም፤ ከፎርማቱ ይልቅ ጭንቅላት፣ አስተሳሰብ መለወጡ ላይ መሰራት ነው መቅደም ያለበት ይላሉ… በሃሳቡ ትስማማለህ…? አስራት፡- ፎርማቱ ሲቀየር አኮ ጭንቅላት አስተሳሰብም አብሮ ይቀየራል፤ በዘር፣ በጎሳ ከታጠረ አመለካከት ትወጣለህ፡፡ ቡድናዊ ከመንደር የጠበበ ስሜትና ድጋፍ እንዳይኖርህ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ በጭንቅላት በአስተሳሰብ ላይ የሚሰራው ስራ እንዳለ ሆኖ ስያሜ ላይ ለውጥ ከተደረገ የተሻለ ነገር ይታያል፡፡ በእኛ የጨዋታ አሰልጣኝነት ዘመን እንዲህ እንደአሁኑ ረብሻ፣ የሰው ደም መፍሰስ ሞት የሚባል ነገር የለም፤ምክንያቱም በመንደር የጠበበ በፓርቲ ስም የተዋቀረ ክለብ የለምና፡፡ ስለዚህ ይሄ በደንብ ሊጠና፤ፎርማቱም ሊፈተሽ ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡-…የሀገራችን እግር ኳስ ከማደግ ይልቅ እየወረደ ሀገራችን ያሏት የኢንስት ራክተሮች ቁጥር ወደ 128 ማደጉን የፌዴሬሽኑ ሰዎች አብስረዋል፤ ይሄንን እንዴተ ታዘብ ከው…?
አስራት፡- እኔ የኢንስትራክተሮች መብዛት ላይ ችግር የለብኝም፤ ላላደገው እግር ኳሳችን ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላትና ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው ወጣቱና ታዳጊው ለሆነባት ሀገር ቁጥሩ ያንሰ ይሆናል እንጂ አይበዛም፡፡ ግን ጥያቄው እግር ኳሱ ደክሞ የኢንስትራክተሮች ቁጥር እየበዛ ያለው በትክክለኛው መንገድ ሰርተው የካፍና የፊፋ ሕግ ለኢንስትራክተርነት ያስቀመጠውን መስፈ ርት ቢያንስ በትንሹ ተከብሮ በውስጡ አልፈው ነው ወይ? የሚለው በአግባቡ መመለስ አለበት፡፡ የኢስትራክተሮች ቁጥር መብዛት ከዚህ በተቃራኒ ሆኖ ከሆነ ነው የመብዛቱ ጥያቄ የማይታየኝ፤ የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ የዳይሬክተር የኢንስትርክተሮች ቁጥር ከ120 ወደ 180 ማደጉን ነግረውናል፤ ብዛቱ ላይ ጥያቄ ባይኖረኝም የበዙበት፣ ቁጥሩ ያደገበት መንገድ ግን ግልፅ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡
ሀትሪክ፡- ባልተለመደ ሁኔታ ከሥልጠና ወደ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ (ሬዲዮ) ተሸጋግ ረሃል፤…. ምን አስበህ ነው… ?
አስራት፡- … ምንም አላሰብኩም… ቀደም ሲል በሙያዬ እግር ኳሱን የማገዝ ፍላጎቱ ነበረኝ፤ የሆነ ያልሆነ ምክንያት እየተደረደረ በሮች ሁሉ ተዘጉብኝ፤ ከስልጠናውም ተገፈ ተርኩ። በዚህ ተስፋ ሳልቆርጥ እንደ እኔ የተገፉ በሩ የተዘጋባቸው አሰልጣኞችን ለመታደግ ለሙያውና ሙያተኛው መከበር ለመታገል እንቅፋቶቹን ሁሉ ለመበጣጠስ በፌዴሬሽኑ ውስጥ በሙያዬ ለማገልገል በምርጫ ለመሳተፍ ሞክሬ ብዙዎች “እንዴት ልምድን፣ እውቀትን፣ ከውጤት ጋር አጣምሮ ከያዘው አስራት ጋር እንዴት እንወዳደራለን?” ብለው ለቦታው ከእነሱ በተሻለ ተገቢው ሰው መሆኔን ራሣቸው ተወዳዳሪዎቹ መስክረው ፤ እኔ ከቦታው ዞር ብዬ የመሰከሩት ቦታው ላይ ቁጭ አሉ፡፡ የምርጫው አካሄድ ስላልተመቸኝና ከችሎታ፤ ከእውቀትና ልምድ ውጪ መስፈርቱ ሌላ በመሆኑ ራሴን ከቦታው አገለልኩ፡፡ በንዑስ ኮሜቴ ውስጥ ገብቼ ሙያዬን በተመለከተ እሰራለሁ ብዬ ያለምኩት ህልም በመጨናገፉ ዝም ብዬ ከምቀመጥ ልክ ታላላቅ አሰልጣኞች በቅርቡ እነ ሞውሪንሆ ቬንገር በቢቲ ስፖርት እነ ፈርዲናንድ ጋሪ ሊንከርና ኢያን ራይትን የመሰሉ የቀድሞ ተጨዋቾችና አሰልጣኞች እውቀታቸውን በሚዲያ እንደሚያካፍሉት እኔም በዚህ መልኩ የ51 አመት በተጨዋችነት በአሰልጣኝነት ያካበትኩትን ልምድ እውቀት ለማካፈል ስፖርቱን በሙያዬ ለማገዝ በማሰብ ከተግባር እንቅስቃሴ ተገፋቼ ብወጣም እግር ኳስ የተግባርና የቴዎሪ አካል በመሆኑ የአእ ምሮ (የጭንቅላት) ረሃቤን ለማስታገስ በእግሬ ያጣሁትን እግር ኳሱን የማገዝ እድል በአንደበቴ ለማሰካት የተለያዩ አስተያየት ትንታኔዎች ለመስጠት ነው ወደ እናንተ ሙያ የተጠጋሁት፡፡ በዚህም ምክንያት በአፍሮ ኤፍ ኤም 1ዐ5.3 በሳምንት ሶስት ቀን የተለያዩ ፕሮግራሞችን ከባልደረቦቼ ጋር እየሠራሁ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- አስራት ወደ ሬዲዮ የመጣው ፌዴሬሽኑንም የገፉትንም በሚዲያ ለመበቀል ነው ብለው ለሚሰጉ ምን መልስ አለህ…?
አስራት፡- …(ሣቅ)…እኔ ለሀሜት ብዙም ጆሮ የለኝም…፤…ለበቀል ቢሆንማ ኖሮ በሩን ከርችሞ ለዘጋብኝ ፌዴሬሽን ከውጭ የመጡ የህክምና ባለሙያን አሳምኜ፣ አግባብቼ ስልጠና እንዲሰጡ ሁኔታውን አላመቻቸም ነበር፡፡ የገፉኝና ውለታዬን የረሱት ግለሰቦች እንጂ ፌዴሬሽኑ አይደለም፡፡ እኔ ሙያው ለሀገሬ የሚሰጠውን ጥቅምና ትርፍ እንጂ የግለሰቦችን ተንኮል አይደለም የማየው፤በቀጣይም የሀገ ራችን ሙያተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራሁ ነው፤ይሄ ጊዜው ሲደርስ የሚታይ ነው፡፡ ሚዲያ ደግሞ ማስተማሪያ እንጂ መበቀያ አይደለም፤እኔም የበቀል ሰው ስላል ሆንኩ ሚዲያን ለዚህ ሰይጣናዊ አላማም እንደማላውለው ሀሜተኞቹ እንዲያውቁ እፈል ጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ነባር አሰልጣኞች በልምዳችሁ፣ በስኬታማነት ሚስጥራችሁ ፌዴሬሽኑም ሆነ እግር ኳሱ ሊጠቀምባችሁ ሲገባ ገሸሽ ተዳርጋችኋል…፤…ለእግር ኳሱ የማይዘነጋ ትልቅ ውለታ ውላችሁ ለህክምና እንኳን ተለምኖላችሁ ነው የምትታከሙት ይሄስ …?
አስራት፡- …ሁሌም በጣም የሚያንገበግበኝና የሚቆጨኝ ይሄ ነው፤ ለዚህም ነው ደግሜ ደጋግሜ የባለውለተኛ አያያዛችን ደካማ ነው የምለው። ምንም ጥቅም በሌለበት፣ ለእግር ኳሱ ራሣችንን እንደ ሻማ አቅልጠን ብርሃን ሰጥተን ዞር ብሎ የሚያየን እንኳን የለም፡፡ እኔ ህንፃ ኮንስትራክሽን ሳሰለጥን ደሞዜ 400 ብር ነበር፤ ጊዮርጊስ ስገባ መጀመሪያ 300 በኋላ ነው ወደ 1500 ብር ያደገልኝ፡፡ በዚያ ላይ ብንጎዳ አፍንጫን ቢሰበር እግዚአብሄር በቸርነቱ ምህረቱን ካልሰጠህ ወይ ጠማማ አሊያም ወልጋዳ ሆነህ ነው የምትቀረው፡፡ በእግር ኳስ የተሰበረው አፍንጫዬ ይሄው አብሮኝ ከእነ ትዝታው አለ፡፡ የቀድሞ ባለውለተኞች ምንም በሌለበት ሰዓት ሀገርን ማልያን ብለን ከመልፋት ውጪ ምንም የያዝነው ቅሪት የለም፤ ለዚህም ነው ትንሽ ህመም ሲገጥመን እንኳን ሰው ፊት የምንሮጠው፡፡ አሁን የስዩም አባተ ሞት የሁላችንም የአሰልጣኞች ሞት ነው፤ ስዩም የሞተው በሙያው ነው፡፡ ትንሽ እንኳን ትንፋሹን ያቆየነው ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ለምነን ባገኘነው ገንዘብ ነው፤ የረዱን እግዚአብሔር ይሰጣቸውና ለሀገር ውለታ ውለህ በዚህ መልኩ ተቸግረህ አስታዋሽ አጥተህ መሞት ሁለት ሞት ነው፡፡ ስዩም ተሰቃይቶ ቀኑ ደርሶ አለፈ ሌሎቹስ…? አሁን ወንድማገኘ ከበደ አልጋ ላይ ከወደቀ ቆይቷል፡፡ ወንድማገኘ ከበደ በክለብም በብ/ቡድንም በተጨዋችነትና በአሰልጣኝነት ለሀገር ብዙ ያበረከተ ነው፤ ውጪ ሄዶ መታከሚያ ገንዘብ እንኳን ባለማግኘቱ እየተሰቃየ ነው፤ ይሄ ሁላችንንም ያማል፤ለሀገር ውለታ መዋል ትርጉሙም ይጠፋብናል፡፡ በሌላ ሀገር እኮ ባለውለተኞች ይከበራሉ፡፡ እኛ ጋር ግን እንደ ሸንኮራ መጥጦ ጣዕሙ ሲያልቅ መጣልን የተካንን ይመስለኛል፡፡ ሀትሪክ፡- ፌዴሬሽኑስ ልምድ፣ እውቀትና ውጤት ያላቸው አሰልጣኞችን በማስጠጋቱ በኩል በተለይ ሙያችሁን ትኩረት ባደረገ ነገር ላይ…? አስራት፡- እዚያም ለይስሙላ እንዲህ አድርገናል ለማለት ለስብሰባ ካልሆነ በስቀተር በራችው ዝግ ነው፤ ራሣቸውንም ሰውንም ለማታለል ይጠሩሃል፤ በስብሰባው ላይም እግር ኳሱን የሚለውጠው ኃይል እዚህ ነው ያለው ብለው ይሸነግሉሃል፤ ታስፈልጉናላችሁ ይሉናል በኋላ ግን ዞር ብለው አያዩንም፡፡ አመራሩን ከጨበጡት በላይ በስፖርቱ ልምድም እውቀቱም ውጤቱም ያለን እኛ ሆነነ መግቢያው በር ተከርችሞብናል፡፡ ባለፈው እኔ በምርጫው መሳተፉ የፈለኩት ይሄንን መሰናክል ለመበጣጠስ ነበር፡፡ ለሙያተኞች የሚታገል ሰው በማጣታችን የተከረቸመውን በር ማስከፈት አልቻልንም፤ ሙያተኞች ቦታው ላይ አልገባም ብለን ጮኸን ሙያተኞች ከገቡ በኋላ ምን ሠሩ? በሙያው ውስጥ ሆነው ሲማረሩበት ሲወቅሱበት የነበረውን ችግር ውስጥ ከገቡ በኋላ ለሙያተኛ ምን ያህል ተቆርቋሪ ሆነው ቀረቡ?… ሙያተኛው እንዲሰራስ ምን ያህል ድጋፍ ሰጡ? ብለህ ስትጠይቅ መልስ ታጣለህ፡፡ በትክክል ለአሰልጣኝ የሚቆረቆር የሚታገል እስካልመጣ የተከረቸውን በር ማስከፈት አይቻልም…