በይስሀቅ በላይ (ከለንደን ከካላዶሊያን ሮድ)
16ኛው የዓለም አቴሊቲክስ ሻምፒዮና በልዩ ድምቀት ተጀምሮ ልዩ ትዝታውን ትቶ ለመጠናቀቅ የአንድ ቀን ዕድሜ ብቻ ይቀረዋል።
የዛሬው እና የነገውን የ5ሺ ሜትር የሁለቱም ፆታዎችን ፍፃሜ ሳይጨምር ኢትዮጵያ በ1 ወርቅ፣በ1ብርና በ1 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 6ኛ ከአፍሪካ በኬንያ ተበልጣ በ2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
እስከአሁን ባለው ውጤት ደካማ የሚባል ጉዞ እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በዛሬውና በነገው ዕለት በሚደረጉ ውድድሮች ለውጥ ካልመጣ በስተቀር ፌዴሬሽኑ ቤንች ማርክ አድርጌዋለሁ ያለውን ያለፈውን የ2015ቱን የቤጂንጉን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሪከርዱን ለማሻሻል የማይታሰብ ያደርገዋል።
አመርቂ ውጤት ካለመመዝገቡና ከጉዳት ጋር በተያያዘ የተዘበራረቀ ስሜት ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በትናንትናው ዕለት ለንደን በሚገኘውና የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድኑ ባረፈበት ጉማ ሆቴል እዛ ለሚገኙ ጥቂት ጋዜጠኞች ለሁለተኛ ጊዜ በወቅታዊው የቡድኑ አቃምና የተለያዩ ችግሮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም፣አቶ ዱቤ ጂሎና የህክምና ባለሙያዋ ዶክተር ቅድስት በጋራ ሆነው ከሰጡት ጋዜጣዋ መግለጫ ዋና ዋናዎቹ ከዚህ በታች ባለው መልኩ ቀርበዋል።
የገንዘቤ ዲባባ በመጨረሻው ሰዓት ከ5ሺ ሜትር ውጪ መሆናን በተመለከተ …
…የገንዘቤን ጉዳይ መጀመሪያ ፌዴሬሽኑ እና እሳ በተስማሙበት መሰረት አዲስ አበባ ላይ የክረምት ወራት በመሆኑ ወጪዎቻን ችላ ወደ አውሮፓ ሄዳ ዝግጅታን አድርጋለች፤እኛም የዕለት ተዕለት ዝግጅታን በተለያየ መንገድ ስንከታተላት ነበር።ከዚህ በተጨማሪም ለሻምፒዮናው ትልቅ ጉጉትና ዝግጅት ነበራት በ1500 ሜትር ያሳየችው ብቃት እንደዝግጅትዋ አልነበረም፤በተለይ እሳ ስትወዳደር ዝናብ መኖሩ የፈለገችውን ውጤት እንዳታመጣ አድርጋታል።
ከ1500 ሜትር ውድድራ በኃላ የህክምና ምርመራ አድርጋ የወገብ ህመም ስላጋጠማት የIAAF፣የፌዴሬሽኑ የህክምና ውጤቶችንና ሪፓርቶችን መነሻ በማድረግ ፌዴሬሽኑ ገንዘቤ እሁድ በሚደረገው የ5000ሜትር ፍፃሜ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና ብትወዳደር የምታመጣው ነገር እንደሌለ ፌዴሬሽኑ በማመኑ ከፍፃሜ ውድድር ውጪ ሆናለች።
…የቡድን አንድነት (ቲም ስፕሪትን)መጥፋትን በተመለከተ…
..የቡድን አንድነትን በተመለከተ በምንፈልገው መልኩ መጥታል ብለን መናገር ባንችልም የተወሰኑ ምልክቶች መታየት መጀመራቸው የማይካድ ነው፤ያም ቢሆን ግን የተወሰኑ ምልክቶች መታየት ችለዋል።የቡድን አንድነትንና የቡድን ስሜትን የመፍጠር ስራችንን ወደፊት ይበልጥ አጠናክረን የምንሄድበት ሁኔታ ነው የሚኖረው …።
…አብዛኛው አትሌቶች የሚሰለጥኑት ፌዴሬሽኑ በመደበላቸው ሳይሆን በግል አሰልጣኞቻቸው፤ፌዴሬሽኑ እነ ሻምበል ቶሎሳ፣ሱፐር ኢንቴንዳንት ሁሲን ሸቦ፣ሱፐር ኢንቴንዳንት አበበ መኮንን በሃላፊነት ሾማል ውጤት ቢመጣ ዕውቅናና ሽልማት የሚሰጠው ለማን ነው ?በሚል ለቀረበው ጥያቄ …
…በመሰረቱ በዚህ በኩል ዕውቅና የሚሰጠው ዕውቅና ሰጥቶ ለሾማቸው አሰልጣኞች ነው የሚሆነው እነሱንም ነው ለዕውቅና የሚያቀርበው…።
…በግል አሰልጣኛቻቸው የሚሰለጥኑ ከሆነ ዋና በሚል የተሾሙት አሰልጣኞች ሚናቸው ምንድነው?…
…የግል አሰልጣኞቻቸውን በተመለከተ ተነጋግረንበት የወሰነው ውሳኔ ነው፤እነዚህ የግል አሰልጣኞቻቸው ቢመጡና አብረው ቢሰሩ ጉዳቱ ምንድነው?ጥቅሙስ? የሚለውን አይተን ፈትሸን የግል አሰልጣኞቻቸው መኖር ጉዳት እንደሌለው በማመን አብረው እንዲሰሩ የተወሰነ ነው…።
…ዛሬ እና ነገ ስለሚደረገው የ5000 ሜትር ፍፃሜና የሚጠበቀውን ውጤት በተመለከተ…
በሁለቱም ፃታዎች ትልቅ ተስፋ አለን፤በማጣሪያው ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ተስፋ ያለው ነገር ከማየታችን አንፃር ትልቅ ውጤት ነው የምንጠብቀው፤የተሻለ ነገርም እናያለን…።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከፌዴሬሽኑ መግለጫ ውጪ ወዳለ ሌላ ዜና ስናልፍ አትሌት ገንዘቤ በዘንድሮው የዓለም ሻሚፒዮና ላይ ውጤታማ አለመሆና ከክብርም ከገንዘብም ውጪ እንደሚያደርጋትና በተለይ በገንዘብ በኩል በትንሹ ከ200ሺ ዶላር በላይ ኪሳራ እንደሚያጋጥማት ነው ለአትሌታ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እየገለፁ ያሉት።
ለአትሌታ ቅርብ እንደሆኑት የዜና ምንጮቻችን ገለፃ ከሆነ አትሌታ በውድድሩ ውጤታማ ለመሆንና በሰው ሀገር ከፍተኛ ገንዘብ አውጥታ መዘጋጀትዋ ለከፍተኛ ኪሳራ የዳረጋት ሲሆን በውድድሩ በማሸነፍዋ ከምታገኘው የገንዘብ ሽልማትና አሸናፊነትዋን ተከትሎ ከሚመጡ የውድድር ግብዣዎችና የተሳትፎ ክፍያዎች አንፃር ውጤታማ አለመሆንዋ ከተጠቀሰው ቁጥር በላይ ብዙ ገንዘብ እንደሚያሳጣት ነው እየገለፁ ያሉት።
አትሌትዋ የዘንድሮውን ውድድር ለማሸነፍ በሰው ሀገር ላደረገችው ዝግጅት ያወጣችውን ከፍተኛ ወጪ ጨምሮ ከ200ሺ ዶላር ወይም ከሚሊዮን 600ሺ የኢትዮጵያ ብር በላይ ኪሳራ ላይ እንደሚጥላት ነው ታማኝ ምንጮች የገለፁት ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከህክምና ባለሙያዎች በቀረበልኝ ሪፖርት መሰረት አትሌታ ከዛሬው የፍፃሜ ውድድር ውጪ የሆነችው በጀርባ ህመም ነው ቢልም ከዚህኛው ዋና ምክንያት በተጨማሪ አትሌታ በ1500ሜትር ውጤት ማጣታን ተከትሎ በማህበራዊ ድረ-ገፃች የሚደርሱባትን ጠንከር ያሉና መስመር የሳቱ ተቃውሞዎችን መቃቃም ባለመቻልዋና በስነ-ልቦናው በኩል በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳትዋም ሳይሆን እንዳልቀረ ምንጮቻችን ያላቸውን ጥርጣሬ ያስቀምጣሉ ።