በ 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅ/ጊዮርጊስ ተገናኝተው ቅ/ጊዮርጊስ በአማካዩ ኢብራሂማ ፎፋና ብቸኛ ጎል አሸናፊ በመሆን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ለአምስተኛ ጊዜ ማንሳት ችሏል።
10:00 ይጀምራል ተብሎ 10:35 ላይ የጀመረው እና እንደሰሞኑን ጨዋታዎች ሁሉ በድንቅ የደጋፊዎች ዝማሬና ጭፈራ ታጅቦ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 45ኛው ደቂቃ ድረስ የረባ የግብ ማግባት ሙከራና ጎል ሳይስተናገድበት ቆይቷል።
አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የመሀል ሜዳ ላይ ሽኩቻ በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ 19ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ሳሙኤል ሳኑሚ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ በኩል ወጥቷል። የመጀመሪያው ግማሽ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ኢብራሂማ ፎፋና በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮት ቅ/ጊዮርጊስን የ12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ባለቤት ማድረግ ችሏል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ከጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቅ በኃላ በካታንጋ መሃል በደጋፊዎች በተፈጠረ ግጭት የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ሳይጀመር ለ45 ደቂቃዎች ያህል ለመቋረጥ ተገዷል። በግጭቱ በርካታ ደጋፊዎች ጉዳት አስተናግደው የህክምና እርዳታ የተደረገላቸው ሲሆን ራሳቸውን የሳቱ እና የህክምና እርዳታ የተሰጣቸው ደጋፊዎች ቁጥራቸው በርካታ ነበር።
ከ 45ደቂቃዎች መቋረጥ በኀላ በድጋሚ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 52ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሳኒ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት የቅ/ጊዮርጊሱ አበባው ቡጣቆ መቶት የኢትዮጵያ ቡናው ቤኒናዊ ግብ ጠባቂ ሀሪትሰን በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። 71ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የኢትዮጵያ ቡናው አክሊሉ ዋለልኝ ከማዕዘን ምት የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ቢሞክርም ኳስ በግቡ አናት ወጥታለች ።
78ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ በተከሰተው የደጋፊዎች ስርአት አልበኝነት ወደሜዳ በተወረወሩ ቁሳቁሶች ምክንያት ጨዋታው በተደጋጋሚ ለመቋረጥ ተገዷል።
በጨዋታው ጥሩ ብቃት ያሳየው የቅ/ጊዮርጊሱ ተከላካይ ሳላዲን በርጌቾ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡
በመጨረሻም የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ሲሸለሙ የኢትዮጵያ ቡናው ወንድይፍራው ጌታሁን አዲስ አበባ ከተማ ላይ ከመሀል ሜዳ መቶ ያስቆጠረው ግሩም ግብ የውድድሩ ምርጥ ግብ፣ በውድድሩ አነስተኛ ቢጫ እና ቀይ ካርድ የተመለከተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የአጥቂ አማካይ አብዱልከሪም ኒኪማ ኮከብ ተጨዋች፣ የኢትዮጵያ ቡናው ሳሙኤል ሳኑሚ እና የጅማ አባጅፋሩ ሳምሶን ቆልቻ በ3 ግቦች ኮከብ ግብ አግቢ፣ የቅ/ጊዮርጊሱ አዲሱ አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ ኮከብ አሰልጣኝ በመባል የተዘጋጀላቸውን የዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት ተቀብለዋል።
የዋንጫ ስነስርዓቱ ፎቶ ምንጭ የፈረሰኞቹ ገጽ ፌስቡክ ገፅ