በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት አንድ ጨዋታ ዛሬ(ቅዳሜ) 11:30 ሲል መከላከያ እና ወላይታ ድቻ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ጃኮ አረፋት ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከሜዳው ውጪ ጣፋጭ 3ነጥብ ይዞ ተመልሷል።
ብዙም ማራኪ እንቅስቃሴ ባልታየበት እና የመሀል ሜዳ ኳስ ማንሸራሸር በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ መከላከያ ሙሉ በሚባል መልኩ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ቢችልም ያገኙአቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ባለመቻላቸው ለመሸነፍ ተገዷል።
10ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ሳሙኤል ሳሊሶ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ አግኝቶ የሞከረውን ኳስ የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቮ በቀላሉ ይዞታል። 15ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ቴዎድሮስ ታፈሰ እንዲሁም 23ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ግርማ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርረው የሞከሩትን ኳሶች የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቮ በግሩም ሁኔታ አውጥቶባቸዋል። 16ኛው ደቂቃ ላይ አወል አብደላ እና 32ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ ተገኝ የሞከሯቸው ኳሶች በግቡ አናት ላይ ወጥተዋል።
አብዛኛውን የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ ራሱ የግብ ክልል አፈግፍጎ አጋጣሚ ሲገኝ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ምርጫው ያደረገው ወላይታ ድቻ 33ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት ያሻማውን የቅጣት ምት የመከላከያው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ በቀላሉ ይዞታል። ከ 2ደቂቃዎች በኀላ የወላይታ ድቻው አብዱልሰመድ አሊ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ የሞከረውን ኳስ የመከላከያው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶበታል።
ከእረፍት መልስ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉት ወላይታ ድቻዎች ቶሎ ቶሎ ወደ መከላከያ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው አጥቂ ጃኮ አረፋት ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት እራሱ ጃኮ አረፋት ሞክሮት በግቡ አናት ላይ ወጥቷል። 57ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ የመከላከያው ሙሉቀን ደሳለኝ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ ተመልሳለች። 59ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ አረፋት እንዲሁም 64ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ ብርሀኑ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊትለፊት ተገናኝተው የመከላከያው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ በድንቅ ሁኔታ አድኖባቸዋል። ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ወርደው የቀረቡት መከላከያዎች 69ኛው ደቂቃ ላይ በይተሻ ግዛው ቅጣት ምት ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 9 ደቂቃዎች ሲቀሩት የመከላከያው ተከላካይ ሽመልስ ተገኝ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ አዲሱ የወላይታ ድቻ ፈራሚ ጃኮ አረፋት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ባለድል ማድረግ ችሏል።
ፕሪምየር ሊጉ ነገ ሲቀጥል መቐሌ ላይ በትግራይ ደርቢ አዲስ አዳጊዎቹ መቐሌ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ በ9 ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። በሌሎች ጨዋታዎች አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ደደቢትን ሲያስተናግድ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ እንዲሁም ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከነማ ከ ወልድያ ከተማ በተመሳሳይ 9ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ድሬድዋ ከተማ ከጅማ አባጅፋር የሚያደርጉት ጨዋታ 10:00 በድሬዳዋ ስታዲየም የሚከናወን ይሆናል።
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ ወላይታ ድቻ የመጀመሪያ 3ነጥቡን ማስመዝገብ ችሏል።
Editor at Hatricksport website