በእግርኳሱ የፍትህ አካላት ፊት የተወዛገቡትና መደበኛ ፍ/ቤት ድረስ የተፋለሙት ምንተስኖት አዳነና አዳማ ከተማ መስማማታቸው ይፋ ሆነ።
አዳማ ከተማ ተጨዋቹን ወደስራው እንዲመልስ ደመወዙን እንዲከፍል ይህን ካላደረገ እንዲታገድ በፍትህ አካላቱ ዲሲፕሊንና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ከተወሰነ ሰነባብቷል። ሁለቱም አካላት ለማሸነፍ የሚችሉትን አድርገዋል። ነገር ግን ውዝግቡ ለሁለቱም የሚበጅ አይደለም ያለው ፌዴሬሽኑ ሁለቱን ወገኖች ለድርድር ጠርቶ አወያይቷል።
ዛሬ ጠዋት የፌዴሬሽኑ ም/ል ጸሃፊ አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴና የዲሲፕሊን ኮሚቴ ተወካይ የአዳማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አንበስ ተጨዋቹና የሁለቱ ወገኖች ጠበቆች ፌዴሬሽኑ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ከተወያዩና ከተደራደሩ በኋላ ተጨዋቹ አለኝ የሚለውን ክፍያ ለመክፈልና ውላቸውን ለመቅደድ ተስማምተዋል። ያን ተከትሎ ተጨዋቹና ጠበቃው በመደበኛ ፍ/ቤት የተያዘውን ክስ ለማቋረጥ በመስማማት ተለያይተዋል።
አዳማዎች በተደረገው ድርድር መሠረት እስከ የካቲት 30/2014 ድረስ ያለው ደመወዝ 252 ሺህ ብር ከቼኩ 623 ሺህ ብር በአጠቃላይ 875 ሺህ ብር ለመክፈል መስማማታቸው ድርድሩ በስምምነት እንዲጠናቀቅ አድርጓል። ይህም ተጨዋቹ መብቱን ለማስከበር የሄደበት ርቀት ለሌሎች ተጨዋቾችም በአርአያነት የሚታይ መሆኑን ከታማኝ ምንጭ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።