ከአፍሪካውያን የእግር ኳስ ዳኞች በብቃታቸው ስማቸው ቀድሞ ከሚነሱት መካከል አንዱ የሆነው ባምላክ ተሰማ ወይሳ የፊታችን ቅዳሜ ምሽት በግብፁ አል አህሊ እና በአልጄሪያው ኢኤስ ሴቲፍ መካከል በካይሮ አል ሰላም ስታድየም የሚደረገውን የካፍ ቻምፕየንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ እንዲመራ ተመርጧል ።
ሱዳናዊው መሀመድ አብዱላህ እና የቻድ ዜግነት ያለው ኢሳ ያያ ከባምላክ ተሰማ ጋር በረዳት ዳኝነት ተሰይመዋል ።
ከጥቂት ቀናት በፊትም በቻምፒየንስ ሊጉ የሩብ ፍፃሜ የሁለተኛ ዙር ጨዋታ ላይ የደቡብ አፍሪካው ማሚሎዲ ሰንዳውንስ እና የአንጎላው ፔትሮ ዲ ሉዋንዳ ያደረጉትን ጨዋታ በብቃት መርቶ እንደነበር ይታወሳል ።