በመጪው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በኮትዲቯር ለሚደረገው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሚሆኑ 24 ሀገራትን የሚለዩት የማጣሪያ ጨዋታዎች ከግንቦት መጨረሻ ጀምሮ እንደሚደረጉ ይታወቃል ።
በምድብ 4 ኢትዮጵያ ፤ ግብፅ ፤ ጊኒ እና ማላዊ የተደለደሉ ሲሆን በመጀመሪያ ጨዋታ ግንቦት 25 ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የሚያስተናግደው የማላዊ ብሄራዊ ቡድን በሀገር ውሰጥ ለሚጫወቱ 25 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ በዛሬው ዕለት ዝግጅቱን ጀምሯል ። ብሄራዊ ቡድኑ አራት በቱርክ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያሉት ሲሆን ክለቦቻቸው በሚለቋቸው ጊዜ ብሄራዊ ቡድኑን የሚቀላቀሉ ይሆናል ።
ነበልባሎቹ በሚለው ተቀፅላ ስም የሚታወቀው ብሄራዊ ቡድኑ በስታድየም እገዳ ምክንያት ከአንድ አመት በላይ በሀገሩ ምንም አይነት ጨዋታዎች ማድረግ ያልቻለ ቢሆንም 41,000 በላይ ተመልካች በሚይዘው ዋና ስታድየሙ ቢንጉ ብሄራዊ ስታድየም ላይ በካፍ የተጠየቁትን የተወሰኑ ማስተካከያዎችን በማደረጋቸው ይህን ጨዋታ በደጋፊው ፊት እንዲያደርግ ፈቃድ አግኝቷል።
ጥር ላይ በካሜሩን በተዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የነበረው የማላዊ ብሄራዊ ቡድን ከምድቡ ማለፍ ችሎ የነበረ ሲሆን በጥሎ ማለፉ በሞሮኮ 2 – 1 ተሸንፎ ከውድድሩ መሰናበቱ ይታወሳል ።