ከዚህ ቀደም እግርኳስን ተጫውተው ባሳለፉ እና በእግርኳስ ከፍተኛ ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች የሚመራው የኦል ኢትዮጵያ የታዳጊዎች እና ወጣቶች እግርኳስ ስልጠና ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት የተመሰረተበትን የአንደኛ ዓመት ክብረበአል በደማቅ ሁኔታ አክብሯል ።
መርሀ ግብሩ በዛሬው ዕለት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ካለው የሰላም ቀን ጋር በማያያዝ ከባህልና ስፖርት ሚኒስትር ጋር በመተባበር በትንሿ ስታድየም ሲደረግ በኢፌዲሪ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተው ታድመዋል ።
ፕሮጀክቱ በስሩ ከ300 የሚልቁ ዕድሜያቸው ከ6 – 16 ዓመት ድረስ ያሉ ተጫዋቾች በመያዝ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ የእግርኳስ ሰልጠናዎትን በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን የነገ ተተኪዎች ከማፍራት አንፃር ጠንካራ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ።
” እግርኳስ ለሰላም ለወዳጅነት እና ለአንድነት ” በሚል መሪ ቃል በተከበረው የአንደኛ አመት በአል ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኞች ስታፍ ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ፤ አርቲስቶች እንዲሁም ጋዜጠኞች የተሳተፉባቸው የፉትሳል ጨዋታዎች ተደርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -