በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታቸውን አድርገው አዞዎቹ 2 – 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል ።
አርባምንጭ ከተማዎች በሳምንቱ ከአዳማ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ መላኩ ኤልያስ ፤ ሱራፌል ዳንኤል ፤ ፀጋዬ አበራ እና አህመድ ሁሴንን በተካልኝ ደጀኔ ፤ ሙና በቀለ ፤ ሀቢብ ከማል እና ፍቃዱ አለሙ ምትክ ሲያሰልፉ በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ከአዲስ አበባ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሶስት ለውጦቶችን በማድረግ ፀጋአብ ዮሀንስ ፤ በቃሉ ገነነ እና ዳዊት ታደሰ በማሳረፍ መድኃኔ ብርሀኔ ፤ ሄኖክ ድልቢ እና አብዱልባሲጥ ከማልን በአሰላለፉ በማካተት ጨዋታውን ጀምረዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል በፈጣን ሂድት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የመድረስ ፍላጎቶች የታዩበት ነበር ።
በጨዋታው የነበረው ቀዳሚ የግብ ሙከራም ወደ ግብነት ተቀይሯል ። አርባምንጭ ከተማዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት እንዳልካቸው መስፍን ሲያሻግረው የመሀል ተከላካዩ አሸናፊ ፊዳ በግሩም የግንባር ኳስ ከመረብ አሳርፎታል ። ከግቡ በኋላም አዞዎቹ ተጨማሪ ግብ ለማከል የሀዋሳ ከተማ የኋላ መስመርን ደጋግመው መፈተሽ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በ18ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ በሳጥኑ የቀኝ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ለእንዳልካቸው መስፍን አቀብሎት ተጫዋቹ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን ታድጎታል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ አርባምንጭ ከተማዎች የሀዋሳ ከተማን የኳስ ሂደት በማቋረጥ በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶቾን አድርገዋል ።
ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ሱራፌል ዳንኤል ከቀኝ መሰመር ወደ ግብ ክልል ለማሻገር የላከው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ተመልሷል ።
ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ተቸግረው የቆዩት ሀዋሳ ከተማዎች 24ኛ ደቂቃ ላይ ቀዳሚ የግብ ዕድል ለመፍጠር ችለው ነበር ። በአጋጣሚው ተባረክ ሄፋሞ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ለብሩክ በየነ ለመቀነስ የሞከረው ኳስ በበርናንድ ኦቼንጌ ተጨርፎ ብሩክ አግኝቶ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።
ከውሀ እረፍት መልስ ሀዋሳ ከተማዎች ቀድሞ ከነበራቸው እንቅስቃሴ በተሻለ ወደ አርባምንጭ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ቢችሉም ይስሀቅ ተገኝን የፈተነ የግብ ሙከራ ለማድረግ አልቻሉም ነበር ።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል በተደጋጋሚ ለማጥቃት ሲጠቀሙበት በነበረው የቀኝ መስመር አቅጣጫ ወርቅይታደስ አበበ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ኬንያዊው አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶ ወደ ግብ ሞክሮ የግቡ ቋሚ መልሶበታል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በአርባ ምንጭ ከተማ የ1 – 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
የሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ሀይቆቹ አቻ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል ። ብሩክ በየነ ተከላካዮችን አልፍ ለመግባት ሲጥር ኳሱ የደረሰው ወንድማገኝ ኃይሉ በይስሀቅ ተገኝ መረብ ላይ አሳርፎ የጨዋታውን ውጤት ወደ 1 – 1 ቀይሮታል ።
አጋማሹን በጥሩ መጀመር የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች
ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ቶሎ ቶሎ ወደ አርባምንጭ ከተማንዠ ሳጥን ለመድረስ ችለው ነበር ። በ59ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ በግል ጥረት ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ለኤፍሬም አሻሞ አቀብሎት የነበረ ቢሆንም ኤፍሬም ኳሱን ወደ ግብ ሲሞክር አንዱአለም አስናቀ ተደርቦ አውጥቶበታል ።
አርባምንጭ ከተማዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ሀዋሳ ከተማ የሜዳ ክፍል በሚገቡበት ወቅት ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ጥረው ነበር ።
የግብ ዕድሎች መፍጠራቸውን የቀጠሉት ሀዋሳ ከተማዎች 66ኛ ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ ከወንድማገኝ ኃይሉ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ በግብ ጠባቂው ሲመለስበት ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ኤፍሬም አሻሞ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ አብዱልባሲጥ ከማል በግንባር ወደ ግብ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ይስሀቅ አድኖበታል ።
ከሁለተኛው አጋማሽ የውሀ እረፍት መልስ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉት አርባምንጭ ከተማዎች 79ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ አክለዋል ። ተቀይሮ የገባው በላይ ገዛኸኝ ከእንዳልካቸው መስፍን በግሩም ሁኔታ በተከላካዮች መሀል የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ አርባምንጭ ከተማን ዳግም መሪ ማድረግ ችሏል ።
ከግቡ በኋላ ጨዋታውኖ ተቆጣጥረው መቀጠል የቻሉት አርባምንጭ ከተማዎች ከጨዋታው ሶስት ነጥቦ ይዘው መውጣት ችለዋል ።
ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 30 በማድረስ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በነበረበት 36 ነጥብ እና 4ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል ።
በ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 13 ( ቅዳሜ ) 10:00 ላይ ሀዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ግንቦት 14 ( እሁድ ) ቀትር 7:00 ላይ አርባምንጭ ከተማ ወላይታ ድቻን የሚገጥም ይሆናል ።