በዘጠነኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ የመጨረሻ መርሐግብር በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛዉ የሚመራዉ ባህርዳር ከተማ ተከታታይ ሶስተኛ ድሉን አዳማ ከተማ ላይ ተቀዳጅቷል።
ወደ ድሬዳዋ ከተጓዙ በኋላ በሂድት ከጨዋታ ጨዋታ ራሳቸዉን በማሻሻል ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ መጠጋት የቻሉት የጣና ሞገዶቹ በዛሬዉ ዕለት በዘጠነኛዉ ሳምንት የመጨረሻ መርሐግብር አዳማ ከተማን በዱሬሳ ሹቢሳ ብቸኛ ግብ አንድ ለዜሮ በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። ከዚህ ቀደም የጣና ሞገዶቹ በተከታታይ በሰባተኛዉ እና በስምንተኛው የጨዋታ ሳምንት ጠንካራዉን ኢትዮጵያ መድን እና የተመስገን ዳናዉን ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ሶስት ለአንድ በሆነ ዉጤት ማሸነፋቸውም ይታወሳል።
- ማሰታውቂያ -
በተቃራኒው በእስካሁኑ የሊጉ የዘጠኝ ሳምንታት ጉዞ ሰባት ነጥቦችን ብቻ ማሳካት የቻለዉ አዳማ ከተማ ከዚህ መካከል ስድስቱን ነጥቦች በባህርዳር ስታዲየም በተደረጉ የመጀመሪያ ሶስት ጨዋታዎች ላይ መሆኑ የክለቡን አሁናዊ አቋም ለመገመት ቀላል ያደርገዋል። በተለይ ከቀናት በፊት በስምንተኛው ሳምንት እጅግ ደካማ አጀማመርን እያደረገ በሚገኘዉ ወላይታ ዲቻ ሁለት ለአንድ በሆነ ዉጤት ከተሸነበት ጨዋታ ለማገገም የዛሬውን ጨዋታ በድል ይወጣል ተብሎ ቢጠበቅም ጨዋታውን በሽንፈት ደምድሟል።
ወጤቱን ተከትሎም ባህርዳር ከተማ በስምንት ጨዋታዎች አስራ ሰባት ነጥቦችን በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በምሽቱ ጨዋታ ሽንፈትን ያስተናገደው አዳማ ከተማ ደግሞ በስምንት ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ ብቻ በመሰብሰብ አስራ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በቀጣይ በአስረኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብርም በዛሬዉ ጨዋታ ድል የቀናዉ ባህርዳር ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ሲገናኙ የይታገሱ እንዳለ አዳማ ከተማ ደግሞ ከመሳይ ተፈሪዉ አርባምንጭ ከተማ የሚገናኙ ይሆናል።