በ24ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለተኛ ጨዋታ ባህርዳር ከተማን ከአዳማ ከተማ አገናኝቶ ለበርካታ ጨዋታዎች ከድል ርቆ የነበረው ባህርዳር ከተማ በተመስገን ደረሰ የአምስተኛ ደቂቃ ግብ ጨዋታውን አሸንፎ መውጣት ችሏል ።
ባህርዳር ከተማዎች በ23ኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ አለልኝ አዘነን በፍፁም አለሙ ምትክ ሲያሰልፉ በአዳማ ከተማ በኩል በሳምንቱ ከአርባምንጭ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ በዮናስ ገረመው እና አቡበከር ወንድሙ ምትክ ታደለ መንገሻን እና አብዲሳ ጀማልን አሰልፈዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የደረሱበት እና ግብም የተስተናገደበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በአዳማ ከተማ በኩል 2ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ መናፍ ዐወል መቆጣጠር የተሳነውን ኳስ ነጥቆ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ነፃ ለነበረው ዳዋ ሆቴሳ አቀብሎት ዳዋ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑሪ ወጥቶ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
ከሶሰት ደቂቃዎች በኋላ መናፍ ዐወል ከራሱ የሜዳ ክፍል ለአሊ ሱሌማን ከተከላካዮች ጀርባ የጣለለትን ኳስ የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ግቡን ለቆ ወጥቶ ኳሱን ለማስጣል ባደረገው ጥረት ፋአድ ፈረጃ አግኝቶ ለተመስገን ደረሰ በማቀበል ተመስገን ባህርዳር ከተማን መሪ ያደረገ ግብ እንዲያስቆጥር አስችሎታል ።
ከአንድ ደቂቃ በኋላ ዳዋ ሆቴሳ የመናፍ ዐወልን ስህተት ተጠቅሞ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ኳሱ በአቡበከር ኑሪ ተጨርፎ ፈቱዲን ጀማል አውጥቶታል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ አዳማ ከተማዎች በባህርዳር ከተማ ላይ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለው ነበር ። ቀጣዩ ሙከራቸውም 15ኛው ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን አብዲሳ ጀማል ከቶማስ ስመረቱ በረጅም ተሻግሮ በዳዋ ሆቴሳ ግንባር ተገጭቶ የደረሰውን ኳስ እየገፋ በግራ የሳጥኑ አቅጣጫ ገብቶ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።
በባህርዳር ከተማ በኩል ፊት መስመር ላይ ላሉት ተመስገን ደረሰ እና አሊ ሱሌማን በረጅም ይደርሷቸው የነበሩ ኳሶች አደጋ መፍጠር የቻሉ አልነበሩም ።
ባህርዳር ከተማዎች ከውሀ እረፍት መልስ ኳሱን በተሻለ ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በ30ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነ ከርቀት የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ በግብ ጠባቂው ሳኩባ ካማራ ተይዟል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሶስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት አሊ ሱሌማን ከአህመድ ረሺድ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ በሳኩባ ካማራ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። የማዕዘን ምቱም በፉአድ ፈረጃ አማካኝነት ወደ ግብ ተሻግሮ አምበሉ ፍቆረሚካኤል አለሙ በግንባር ገጭቶት ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ታደለ መንገሻን በማስወጣት በምትኩ ፀጋአብ ዮሴፍን አሰገብተው የጀመሩት አዳማ ከተማዎች በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም የመጨረሻ ቅብብሎቻቸው ጥሩ አለመሆን የግብ ሙከራዎችን ከማድረግ አግዷቸዋል ።
በባህርዳር ከተማ በኩል ኳስ በእግራቸው ስር በሚገባባበት ጊዜ በፈጣን ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶቾን አድርገው ነበር ። በሌላ መልኩም ለተመስገን ደረሰ በረጅም ኳሶች ሲጣሉለት የነበረ ቢሆንም በቀላሉ ለአዳማ ከተማ ተከላካዮች ሲሳይ ይሆኑ ነበር ።
በአጋማሹ ሁለቱን ግብ ጠባቂዎች የፈተነ ምነም አይነት ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ አዳማ ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ወደ ግብ ለመቀየር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎም ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 29 በማድረስ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አዳማ ከተማ በበኩሉ በ27 ነጥብ ወደ 11ኛ ደረጃ ተንሸራቷል ።
በ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 14 ( ዕሁድ ) ረፋድ 4:00 ላይ አዳማ ከተማ ሰበታ ከተማን ሲገጥም በተከታዩ ቀን በተመሳሳይ ረፋድ 4:00 ላይ ባህርዳር ከተማ ሲዳማ ቡናን የሚገጥም ይሆናል ።