ከቀድሞ አሰልጣኛቸው ፋሲል ተካልኝ ጋር ከተለያዩ በኋላ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠሩት ባህርዳሮች አሁን ደግሞ ወደ ዝዉዉሩ ፊታቸዉን በማዞር ሁለት ተጫዋቾችን የግላቸዉ ማድረግ ችለዋል።
የውድድር ዓመቱን በጅማ አባጅፋር ያሳለፈዉ የመስመር ተጫዋቹ ተመስገን ደረሰ በመጨረሻም ማረፊያው ባህር ዳር ከተማ መሆኑ ታውቋል። ምንም እንኳን ክለቡ ጅማ አባጅፋር ወርዶ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ ተመስገን ግን ከመስመር እየተነሳ በፈጣን እንቅስቃሴ ግቦችን ሲያስቆጥር የተመለከትን ሲሆን በዚህም በሊጉ 9ኝ ግቦችን ለክለቡ ጅማ አባጅፋር ማስቆጠሩ ይታወሳል።
በተለይ የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ ካልተሳተፉ እነሱን ለመተካት በተዘጋጀው ዉድድር ላይ ለክለቡ ጅማ አባጅፋር ድንቅ ግልጋሎት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል። ይህ ብቻ ሳይሆን በዉድድሩ ጅማ አባጅፋር ከኮልፌ ቀራኒዮ ጋር በተገናኙበት የ4ኛ ሳምንት መርሀግብር ተመስገን ደረሰ ከርቀት ያስቆጠረዉ አስደናቂ ግብ የተጫዋቹን የብቃት ደረጃ ያስመለከተም ነበር ።
ሌላኛዉ ክለቡን የተቀላቀለዉ ተጫዋች ደግሞ መሳይ አገኘሁ ነው፡፡ ከወላይታ ድቻ የታዳጊ ቡድን የተገኘዉ ወጣቱ ተጫዋች በዘንድሮው የውድድር አመት በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ ችሏል። በዚህም ብዙ ክለቦች የተጫዋቹን ፊርማ ለማግኘት የሞከሩ ሲሆን ወጣቱ ተጫዋች መሳይ አገኘሁ ግን ማረፊያውን ባህርዳር ከተማ አድርጓል።