የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ውድድርና አመራር ስነ-ስርዓት ኮሚቴ የሶስተኛ ሳምንት የ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ መጠናቀቅ ተከትሎ በሶስተኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋተ የቀረቡለትን ሪፖርቶች አጢኖ በተፈጠሩ ሁነቶች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል ።
ወልቂጤ ከተማ በሁለተኛው ሳምንት በ ጅማ አባ ጅፋር ላይ ያስገባው ቅሬታ ተጫዋቾቹ ተገቢ ሆነው በመገኘታቸው የተመዘገበው የ 0 – 0 አቻ ውጤት በውድድር ኮሚቴው መፅደቁ ተገልጿል ። በተያያዘ መረጃ በሶስተኛው ሳምንት በተመሳሳይ ሲዳማ ቡናዎች በሀድያ ሆሳዕና ስፖርት ክለብ ላይ የተጫዋች ተገቢነት ጥያቄ ያቀረቡ መሆኑ ሲገለፅ ከ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምላሽ እስኪያገኝ ውጤቱ እንደማይፀድቅ ይፋ ሆኗል ።
በሶስተኛው ሳምንት መርሀ ግብር ሀያ ጎሎች ከመረብ ሲያርፉ ጌታነህ ከበደ ፣ ያሬድ ታደሰ እና ሀብታሙ ታደሰ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር የቻሉ ብቸኞቹ ተጫዋቾች ሲሆኑ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጋር ሲተያይ የግብ መጠቡ ከፍ ብሎ ታይቷል ።
- ማሰታውቂያ -
ሮቢን ንግላንዴ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ግብ ማስቆጠር የቻለ የመጀመሪያው የውጭ ሀገር ተጫዋች ሲሆን ኢታሙናይ ኬይሙ ሌላኛው ግብ አግቢ ሆኖ በሳምንቱ ማለፍ ችሏል ።
በርካታ ካርዶች በተመዘዙበት ሳምንት አርባ የቢጫ ካርዶች ሲመዘዙ የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ አሸናፊ ከበደ እንዲሁም የድሬድዋ ዋና አሰልጣኝ ፍስሀ ፆመልሳን ከአሰልጣኞች መመልከት ችለዋል ። ከተመዘዙት የማስጠንቀቂያ ካርዶች ከግማሽ በላይ ( ሀያ ሁለት ) የሚሆኑት ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ መሆኑ ታውቋል ። ከዚህ ባለፈ የሀድያ ሆሳዕናው ግብ ጠባቂ መሀመድ ሙንታሪን እንዲሁም የድሬዳዋዎቹ በረከት ሳሙኤል እና ዳንኤል ደምሴ የቀይ ካርድ ሰለባ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው ።
በሶስተኛው ሳምንት የቀይ ካርድ የተመለከተው ግብ ጠባቂው ሙንታሪ የአራት ጨዋታዎች ቅጣት እና የ 4,000 ብር መቆጮ እንዲቀጣ ውሳኔ ተላልፎበታል ። የድሬዳዋዎቹ በረከት ሳሙኤል እና ዳንኤል ደምሴ እያንዳንዳቸው የአንድ ጨዋታ ቅጣት ተላልፎባቸዋል ። ከዚህ በተጨማሪም የሀድያ ሆሳዕና እና ድሬድዋ ከተማ አስራ ሁለት የማስጠንቀቂያ ካርድ በድምሩ ሲመለከቱ ተጨማሪ የ 5,000 ብር መቀጮ ተጥሎባቸዋል ።
በሊጉ ማሸነፍ የተሳናቸው ሐዋሳ ከተማዎች በሶስተኛው ሳምንት 9.25 ነጥብ በማግኘት የስፖርታዊ ጨዋነት ቀዳሚውን ስፍራ መያዝ ሲችሉ ድሬድዋ ከተማ በ 6.00 ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ለመያዝ ተገደዋል ።